1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀሙን ለፓርላማው አቀረበ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 22 2016

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መንግሥት ለምክክሩ "አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር" ጠየቀ። ኮሚሽኑ የ2016 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸሙን ከመደበኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጉባኤ አዳራሽ ውጪ ሆቴል ላይ ባቀረበበት ወቅት ነው መንግሥት ለምክክሩ "አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር" ሲል የጠየቀው፡፡

https://p.dw.com/p/4hfQd
Äthiopien | Bericht Ausschuss für nationalen Dialog
ምስል Solomon Muchie/DW

መንግሥት ለምክክሩ አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር ተጠየቀ

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዓመታዊ የሥራ አፈፃፀሙን ለፓርላማው አቀረበ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መንግሥት ለምክክሩ "አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር" ጠየቀ።

ኮሚሽኑ የ2016 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸሙን ከመደበኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጉባኤ አዳራሽ ውጪ ሆቴል ላይ ባቀረበበት ወቅት ነው መንግሥት ለምክክሩ "አስቻይ ሁኔታዎችን እንዲፈጥር" ሲል የጠየቀው፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ምስፍን አርአያ በዚሁ ወቅት "አድካሚ፣ ሀብት የሚፈጅ፣ ብዙ ሥራ ሊሠራበት የሚገባ ተምሳሌታዊ የምክክር ሂደት ነው የተዘጋጀው" ብለዋል። 

ግጭት ጦርነት ያጠላበት ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ

ሥራው "በችኮላ የሚሠራ አለመሆኑን ተገንዝበናል" ያሉት ኃላፊው፣ ከምክክሩ ራሳቸውን አግልለው ከቆዩ የፓርቲዎች ስብስብ መካከል ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ስድስቱ "የስምምነት ማዕቀፍ" መፈረማቸውን ገልፀዋል።

መንግሥት ለምክክሩ አስቻይ ሁኔታዎችን ይፍጠር- ኮሚሽኑ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ትናንት የዓመቱን የሥራ ክንውኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል። በዚሁ ጊዜ ኮሚሽኑ ሠራሁ ያላቸውንና ድጋፍ ያስፈልገኛል በሚል የገጠሙትን ችግሮች ዘርዝሯል። ዋና ኪሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ለመንግሥት ጥያቄ አቅርበዋል።

ስለ ሀገራዊዉ ምክክር የተሰበሰበ የህዝብ አስተያየት

"አሁንም ለመንግሥት ይሄ ምክክር በትክክል እንዲሳካ ከተፈለገ አስቻይ ሁኔታዎች ይፍጠርልን የሚለውን ጥያቄ ዛሬም በኮሚሽነሮቼ ስም አቀርባለሁ፣ ወደፊትም የምናቀርበው ነው"።

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተሳታፊዎች
አሁንም ለመንግሥት ይሄ ምክክር በትክክል እንዲሳካ ከተፈለገ አስቻይ ሁኔታዎች ይፍጠርልን የሚለውን ጥያቄ ዛሬም በኮሚሽነሮቼ ስም አቀርባለሁ፣ ወደፊትም የምናቀርበው ነው"ምስል Solomon Muchie/DW

ሥራው በችኮላ የሚሠራ አይደለም

ኢትዮጵያ ውስጥ በልሂቃን መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመኖሩ፣ በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደቱን ፈታኝ አድርጓል በሚል ለዚህ መፍትሔ ፍለጋ ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን "ሥራው አድካሚ እና በችኮላ የሚሠራ አለመሆኑን" ተገንዝበናል ሲሉ የተቋሙ የበላይ ኃላፊ ተናግረዋል።

"አድካሚ፣ ሀብትም የሚፈጅ፣ በይድረስ ይድረስ፣ በችኮላ የሚሠራ እንዳልሆነ በትክክል ተገንዝበናል"።

መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ሀገራዊ ምክክር

ኮሚሽኑ የሥልጣን ጊዜው ሊጠናቀቅ ከዘጠኝ ወራት ያነሰ ጊዜ ይቀረዋል። ችግር ውስጥ የሚገኙ ክልሎችን ነባራዊ ሁኔታ በመጥቀስ ሥራው በዚህ ጊዜ ሊያልቅ እንደማይችል ፕሮፋሰር መስፍን ተጠሪ ለሆኑለት ምክር ቤት ተናግረዋል።

"ይሄ ሥራ እንደተባለው አንድ ልጅ በሚወለድበት ዘጠኝ ወር ውስጥ ተወልዶ የሚወጣ ነገር አይኖርም" 

የቀጠሉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተግባራት

በውይይቱ ግጭት እና ጦርነት የሚካሄድባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎችን በተመለከተም ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ ቀርቦ ነበር። በትግራይ ክልል ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ጀምረናል ያሉት ኮሚሽነሩ ነገር ግን "ጠንክሮ ወደፊት አልሄደም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የአማራ ክልሉ ሁኔታ ግን የከፋ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ ስድስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ አባላት "የስምምነት ማዕቀፍ" መፈራረማቸውንና ወደ ውይይት ማዕቀፉ መግባታቸውን ፕሬፌሰር መስፍን አርዓያ ተናግረዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ