1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀጠሉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተግባራት

ሐሙስ፣ ግንቦት 22 2016

"የጋራ ምክር ቤቱ የሚወክላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኛዎቹ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር "እንተባበራለን፣ ይሞከር፣ ችግር መፍታት የሚችል ከሆነ በማለት ለመተባበር ፈቃደኛ የሆኑ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ችግር ፈቺ ሊሆን አይችልም በሚል ጊዜያችን እና ጉልበታችንን አናባክንም የሚል አቋም ነው የያዙት"

https://p.dw.com/p/4gSIb
ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የክልላዊ የምክክር ምዕራፉን በአዲስ አበባ ከተማ ካሄድ
ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የክልላዊ የምክክር ምዕራፉን በአዲስ አበባ ከተማ ካሄድምስል Solomon Muchie/DW

የቀጠሉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተግባራት

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የክልላዊ የምክክር ምዕራፉን ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ ጀምሯል።

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ተሳታፊዎች ትናንት በተጀመረው ሂደት ላይ የተገኙ ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ በግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ምክክር እያደረጉ ነው።
ይሄው መድረክ በተሳታፊዎች የአጀንዳ ግብዓት ይዘጋጅበታል፣ በሀገራዊ ጉባኤው ከተማዋን የሚወክሉ ተሳታፊዎች ይመረጡበታል።
አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ድርጅቶች ጥረቱ ችግር መፍታት የሚችል ከሆነ "ይሞከር" በሚል ለሥራው ድጋፍ የሰጡ ሲሆን፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ ግን ሥራው "ነፃ፣ ገለልተኛ እና ተዓማኒ ሊሆን አይችልም" በሚል አሁንም ከምክክር ሂደቱ ውጪ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የተሳታፊዎች አስተያየት 

ትናንት በተጀመረው የአዲስ አበባው ክልላዊ የምክክር ምዕራፍ 119 ወረዳዎችን የወከሉ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል። ከየካ ክፍለ ከተማ መመህራንን የወከሉት ተሳታፊ ለመምህራን የሚገባ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለትውልድ ሕልውና ወሳኝ መሆኑን በማመን ሊነሱ ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ ይህ ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል።
"እንደ ሀገር መምህራን በምን ደረጃ ላይ እንደሚኖሩ ይታወቃል። እነሱ ላይ በደንብ ቢሠራ" 
ሌላኛው ከአራዳ ክፍለ ከተማ መምህራንን ወክለው የተገኙት ግለሰብ፤ ከዚህ በፊት ባደረጉት ውይይት ከአካባቢያቸው ነዋሪዎች አንድነት እና ሕዝብን የሚሠማ አስተዳደር ሊኖር ይገበል የሚል ጉዳይ መንፀባረቁን ነግረውናል።
"ብሔር ብሔረሰቦች በሚለው አስተሳሰብ ላይ ኢትዮጵያ አንድ ናት የሚል፤ ክልሎች መኖር የለባቸውም የሚል እንደዚህ አይነት አስተሳሰቦች የሚመጡ አሉ" ብለዋል።

"አዲስ ውጤት ለማግኘት፣ በአዲስ መንገድ መሄድ አስፈላጊ ነው" - ዋና ኮሚሽነር 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ "አዲስ ውጤት ለማግኘት፣ በአዲስ መንገድ መሄድ አስፈላጊ እንደመሆኑ" ሁሉም እኩል ተሳትፊ የሚደረግበት ታሪካዊ ያሉት መድረክ መፈጠሩን ገልፀዋል።
"በልዩነታቸው አንድ የሆኑትን ሕዝቦቻችንን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያበጡ በመጡ የሀሳብ ልዩነቶች ሀገራችንን ከልቀት ወደ ድቀት፣ ከፍቅር ወደ ጥላቻ፣ ከአንድነት ወደ መነጣጠል፣ ከሰላም ወደ ጦርነት እየጎተቷት የመጧትን ምክንያቶች ነቅሶ በማውጣት፤ በሰከነ እና በተረጋጋ እንዲሁም ከበሬታ ባለበት ሁኔታ ተቀራርቦ በመመካከር ወደ መግባባት መድረስ ምንም አማራጭ የሌለው ብቸኛ ሀገራዊ መፍትሔ መሆኑን ግንዛቤ ወስደናል ብየ አምናለሁ"

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የክልላዊ የምክክር ምዕራፉን በአዲስ አበባ ከተማ ካሄድ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የክልላዊ የምክክር ምዕራፉን በአዲስ አበባ ከተማ ካሄድምስል Solomon Muchie/DW

በሀገራዊ ምክክሩ ዙሪያ የተለያየ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች አስተያየት

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ምክክሩ ችግር መፍታት የሚችል ከሆነ "ይሞከር" በሚል ድጋፍ መስጠታቸውን ገልፀዋል።

"የጋራ ምክር ቤቱ የሚወክላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አብዛኛዎቹ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር "እንተባበራለን፣ ይሞከር፣ ችግር መፍታት የሚችል ከሆነ በማለት ለመተባበር ፈቃደኛ የሆኑ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ ችግር ፈቺ ሊሆን አይችልም በሚል ጊዜያችን እና ጉልበታችንን አናባክንም የሚል አቋም ነው የያዙት" ብለዋል።

ዘጠኝ አባላት ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ ግን አሁንም ከሂደቱ ውጪ ነው። ምክንያቱ ደግሞ ለኮከሱ መቋቋም መነሻ የሆነው ጉዳይ መሆኑን የሕብር ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር አቶ ግርማ በቀለ ገልፀዋል።

"የአዋጁ [የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን] አወጣጥ ሥርዓት የተከተለ አይደለም፣ የኮሚሽኑ አመሠራረት እና የኮሚሽነሮችም አሰያየም አግባብ አይደለም በሚል በነዚህ ሁለት [ምክንያቶች] ነው" ኮከሱ የተቋቋመው። "በዚህ መሠረት የሚከናወን የትኛውም ሂደት ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ተዓማኒ ሊሆን አይችልም ነው" በሚል በሂደቱ ከመሳተፍ ራሳቸውን ማግለላቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ በአሁኑ ወቅት በይፋ ከምክክር ሂደቱ የወጡ ተጨማሪ ፓርቲዎች ባይኖሩም፤ ቅሬታ የሚያሰሙ መኖራቸውን ግን ገልፀዋል።

"እኛ ላይ ራሱ እየደረሰ ያለው ጫና እየከበደን ነው፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር መተባበሩ ፋይዳው ምንድን ነው? ስለዚህ መልሰን የምናይበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን" እያሉ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ አቋምም ሲይዙ እያስተዋልን ነው" በማለት ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መስሪያቤት
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መስሪያቤትምስል Solomon Muchie/DW


የኮሚሽኑ የሥልጣን ጊዜ 
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በምክክር ሂደቱ ተሳታፊዎች በሚናገሩት፣ በሚያፈልቁት ሀሳብ፣ በሚሰጡት አስተያየት ምንም ችግር እንደማይገጥማቸው ዋስትና እንደሚሰጥ፣ በዚህ ዙሪያ ከመንግሥት ጋር ስምምነት እንዳለውም አስቀድሞ አስታውቋል። ኮሚሽኑ የሥልጣን ጊዜው ሊጠናቀቅ ዘጠኝ ወራት ይቀሩታል።
ሰሎሞን ሙጬ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ