1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ሀገራዊ ምክክር

ሰኞ፣ ግንቦት 26 2016

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና እናት ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ በሆነችበት፣ የታሰሩ ንቁ ሰዎች ባልተፈቱበትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባልተነሳበት ሁኔታ በምክክር መሳተፉ ትርጉም የለውም በሚል ራሳቸውን ከምክክሩ እንደሚያገሉ አስታወቁ።

https://p.dw.com/p/4ga5x
ኢትዮጵያ፤ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን
ኢትዮጵያ፤ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ምስል Solomon Muchie/DW

መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ሀገራዊ ምክክር

መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ስለ ሀገራዊ ምክክር

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና እናት ፓርቲዎች ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ በሆነችበት፣ የታሰሩ ንቁ ሰዎች ባልተፈቱበት እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባልተነሳበት ሁኔታ በምክክር መሳተፉ ትርጉም የለውም በሚል ራሳቸውን ከምክክሩ እንደሚያገሉ አስታወቁ።

ቅዳሜ ዕለት "ኢትዮጵያ ውስጥ ከእንግዲህ በኋላ የሽግግር መንግሥት አይኖርም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው መንግሥታቸው "ይህንን እድል ሳናበላሽ ሁላችንም አሸናፊ በሚያደርግ አግባብ ልንጠቀምበት ይገባል" የሚል እምነት እንዳለው ገልፀዋል። 

"ኢትዮጵያ ውስጥ ከእንግዲህ በኋላ የሽግግር መንግሥት አይኖርም" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አርብ ግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ለሀገራዊ ምክክሩ የአዲስ አበባ አጀንዳ የማሰባሰብ ውይይት በግዮን ሆቴል ሲደረግ አንድ ተሳታፊ "የሽግግር መንግሥት ይቋቋም፤ የወከልኹትን ሕዝብ የውይይት አጀንዳ ሀሳብ ነው የማቀርበው" ሲሉ ዶቼ ቬለ አድምጧል። 

በማግስቱ ቅዳሜ ግንቦት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በአድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በሀገራዊ ምክክር ውይይት ላይ "ኢትዮጵያ ውስጥ ከእንግዲህ በኋላ የሽግግር መንግሥት አይኖርም" ሲሉ ተናግረዋል። በምርጫ፣ በሕዝብ ውሳኔ የተመረጠ መንግሥት ብቻ እንደሚኖር የገለፁት ዐቢይ ይሄው እድል እንዳያመልጥ ሲሉ ጥሪ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ምስል Office of Prime minister of Ethiopia

"ኢትዮጵያ ውስጥ እንመካከር ብለው ሲለምኑ የነበሩ ሰዎች እሺ፣ ኑ እንመካከር ስንላቸው ዛሬ ፈቃደኛ መሆን ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደስታ መቀላቀል ይኖርባቸዋል" 

ራሳቸውን ከሀገራዊ ምክክሩ ያገለሉ ፓርቲዎች

ለሁለት ቀናት የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አድርጎ ከተወያየ በኋላ ከሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ተሳትፎ ራሱን ማግለሉን ያስታወቀው ኢሕአፓ ያንን ሲወስን ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ጭምር መሆኑን የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ተናግረዋል።

"ራሱን ሙሉ በሙሉ ከሀገራዊ ምክክር አግልሏል። ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል። ጦርነት እስካልቆመ ድረስ፣ ሁሉም የፖለቲካ፣ የኅሊና እሥረኞች እስካልተፈቱ ድረስ እና ገለልተኛ እስካልሆነ ድረስ ራሳችንን ከዚህ ውይይት አግልለናል"

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሠብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ "እኛ ላይ[ፓርቲዎች ላይ] ራሱ እየደረሰ ያለው ጫና እየከበደን ነው፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ጋር መተባበሩ ፋይዳው ምንድን ነው? በሚል ጥያቄ የሚያነሱ ፓርቲዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ነገር ግን አብዛኞቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ምክክሩ ችግር መፍታት የሚችል ከሆነ "ይሞከር" በሚል ድጋፍ መስጠታቸውን ከሰሞኑ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ምስል Solomon Muchie/DW

የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ ግን አሁንም ከሂደቱ ውጪ መሆኑን የሕብር ኢትዮጵያ ሊቀ መንበር አቶ ግርማ በቀለ ገልፀዋል። "የኮሚሽኑ አመሠራረት እና የኮሚሽነሮች አሰያየም አግባብ አይደለም። በዚህ መሠረት የሚከናወን የትኛውም ሂደት ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ተዓማኒ ሊሆን አይችልም ነው" 

ፓርቲዎች ምክክር ለማድረግ ችግር አድርገው የሚጠቅሷቸው ሀገራዊ ጉዳዮች

እናት ፓርቲ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ተሳትፎ እና አጀንዳዎች ማቅረብን አስመልክቶ በፃፈው ደብዳቤ ሀገር ከእርስ በርስ ጦርነት ሳትወጣ፣ በየእሥር ቤቱ ንቁ ዜጎች በታጎሩበት፣ ሀገር በአስችኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር ባለችበት ሁኔታ በምክክሩ ለመሳተፍ የሚቸገር መሆኑን አስታውቋል። የኢሕአፓ ምክትል ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስለ ሽግግር መንግሥት የሰጡትን አስተያየት እንደ ችግር ጠቅሰውታል።

"ምናልባት የሀገራዊ ምክክር ውጤት የሽግግር መንግሥት ጥያቄ የሚያመጣ ሊሆን ይችላል። ሕዝብ እስከተስማማ ድረስ። እንዲህ የማይታሰብ ነገር ነው እያሉ መድረክ ላይ እያስጨበጨቡ ፣ አቅጣጫ እያስቀመጡ ይሄ ውይይት ውጤት ያመጣል ብልን አላሰብንም" 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሥልጣን ጊዜው ከማብቃቱ በፊት ዋናውን የምክክር ጉባኤ ለመጥራት ጥረት እንደሚያደርግ ባለፈው ሳምንት አስታውቋል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሰ