1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የገጠማቸዉ ፈተና

ሐሙስ፣ ጥር 15 2017

ካለፈዉ መፀዉ ወዲሕ ደግሞ የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ኢትዮጵያዉኑ ለንግድ መደብሮቻቸዉ ፈቃድ እንዲያወጡ መመሪያ አዉጥቷል።ፈቃዱን ለማዉጣት መጀመሪያ የተሰጣቸዉ ቀነ-ገደብ እስከ ታሕሳስ ነበር።በቅርቡ እስከ የካቲት ማብቂያ ተራዝሟል።አቶ ይርጋለም እንደሚሉት ችግሩ ፈቃዱን ማዉጣት-አለማዉጣት አይደለም።የቢሮዉ ዉጣ ዉረድ እንጂ።

https://p.dw.com/p/4pXuM
የደቡብ አፍሪቃ መንግስት በቅርቡ ባወጣዉ ትዕዛዝ መሠረት በአነስተኛ ሱቅ የሚተዳደሩ ሰዎች ለየሱቆቻቸዉ ፈቃድ ማዉጣት ወይም መመዝገብ አለባቸዉ
ደቡብ አፍሪቃ የሚኖረዉ አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ በአነስተኛ ንግድ በተለይ «Tuck Shop» በሚባሉ ሱቆች ሸቀጦችን በመቸርቸር ይተዳደራል። ምስል Chris McGrath/Getty Images

ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የገጠማቸዉ ፈተና

ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የሥራ ፈቃድ ለማግኘት የሐገሪቱ መንግስት አዲስ ያወጣዉን መመሪያ ለማሟላት መቸገራቸዉን አስታወቁ።የደቡብ አፍሪቃ መንግስት ከጥቂት ወራት በፊት ባወጣዉ መመሪያ መሠረት በተለይ በሱቅ ንግድ የሚተዳደሩ ኢትዮጵያዉያን ተመዝግበዉ ሕጋዊ ፈቃድ ማግኘት አለባቸዉ።ይሁንና ባለሱቆች፣ የማሕበራት ተጠሪዎችና የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ፈቃዱን ለማግኘት መንግስት የዘረዘራቸዉን ቅድመ ግዴታዎች ባጭር ጊዜ ማሟላት አይቻልም።
                             
የስደት ኑሮ ከባድ ነዉ።ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ደግሞ ከባዱን ኑሮ ለመግፋት ከዉጪ ተወላጅ ጠል ፖለቲከኞች፣ ከማጅራት መቺዎች፣ ከወርሮ በሎች፣ ከጉቦኛ ባለሥልጣናት፣ከአጭበርባሪ ደላላ ጋር ዕለት በዕለት መጋፈጥ ግድ አለባቸዉ።

«ታታሪና ከልቡ የሚደክም» ማሕበረሰብ የገጠመዉ ፈተና

 

ያም ሆኖየቅን ልቦች በጎ አድራጎት ሕብረት መሪይርጋለም ትክሌ እንደሚሉት ኢትዮጵያዊ «የወትሮ» የሚባሉ ፈተናዎችን በዘዴም፣ በፅናትም በብላሐትም አልፎ ሕይወቱን ለመለወጥ አልሰነፈም።«ከልቡ ታታሪ« ይሉታል።
 «የሥራ ቦታ አለ።እንዲሁም የሌላ ጎረቤት ሐገራት ዜጎች የሚሰሩት ሥራ አለ።ይሕ ታታሪና ከልቡ እየደከመ ያለ ወገናችን እዚያ ቦታ አለ።----»

የጁሐንስበርጉ ነዋሪ ዳዊት ደገሎ እንደሚለዉ ከ«ታታሪዉ ወገን» አብዛኛዉ በአነስተኛ ንግድ በተለይ « Tuck Shop» በሚባሉ ሱቆች ሸቀጦችን በመቸርቸር ይተዳደራል።
«ምን ያሕል ብሎ መገመት እንኳን ይከብዳል።ብቻ እዚሕ ያለዉ ኦልሞስት ኦል ማለት ይቻላል ትናንሽ ቢዝነሶችን፣ ስታዛ ሾፖችን፣ ራን በማድረግ ነዉ የሚኖረዉ፣ የሚተዳደረዉ።»
ከዚሕ ቀደም የዉጪ ተወላጅን የሚጠሉም፣ ለትላልቅ የገበያ አዳራሾች የሚወግኑም፣ ዘራፊዎቹም ጉበኞቹም ኢትዮጵያዉያኑን ንፅሕናቸዉን ያልጠበቁ፣ በቅጡ ያልተያዙ፣ ጤናን የሚጎዱ የምግብና የመገልገያ ሸቀጦችን ይቸረችራሉ፣ ሕገ ወጥ ናቸዉ እያሉ ሲገፉ፣ሲያሳጡ፣ ሲዘርፉ፣ ሲያፈራሯቸዉም ነበር።
ካለፈዉ መፀዉ ወዲሕ ደግሞ የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ኢትዮጵያዉኑ ለንግድ መደብሮቻቸዉ ፈቃድ እንዲያወጡ መመሪያ አዉጥቷል።ፈቃዱን ለማዉጣት መጀመሪያ የተሰጣቸዉ ቀነ-ገደብ እስከ ታሕሳስ ነበር።በቅርቡ  እስከ የካቲት ማብቂያ ተራዝሟል።አቶ ይርጋለም እንደሚሉት ችግሩ ፈቃዱን ማዉጣት-አለማዉጣት አይደለም።የቢሮዉ ዉጣ ዉረድ እንጂ።
«አቅርቡ የተባለዉን ፈቃድ ለመመዝገብ ከአምስት የሚበልጡ ዲፓርትመንቶች አሉ።አብዛኛዉ ማሕበረሰባችን በዚሕ ጉዳይ ላይ እየተንገላቱ ይገኛሉ።አሁን የማብቂያዉም ጊዜ እየደረሰ ነዉ።ፍብርዋሪ 28 ነዉ ዴድ ላይኑ።አብዛኛዉ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቻችን በዚሕ ጉዳይ ላይ ተጨንቀዋል።»
ከአምስቱ ቢሮዎች የጤና፣ የቦታ፣ የካፒታል ወዘተ ፈቃድ ለማግኘት ረጅም ጊዜ ይጠይቃል።«ቀላል አይደለም» ይላል ዳዊት።ረጅሙን ሒደት ለመጀመር ደግሞ የመኖሪያ ፈቃድ ወሳኝ ነዉ።
«ፌብሪዋሪ 28 ነዉ የተባለዉ።ግን ተብሏል እንጂ ፕሮሰሱ እየሔደ አይደለም።(ለምንድነዉ?ዶክመንት ነዉ።አንዳዴ የመኖሪያ ፈቃዶች እየታደሱ አይደለም።ዶክመንቱ ኖሯቸዉም ፈቃድ ለማግኘት የሔዱት እዚያ ያለዉ ፕሮሰስ ቀላል አይደለም።»

ደርባን ደቡብ አፍሪቃ።እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2022 በጎርፍ አደጋ በተጥለቀለቀች ወቅት ኢትዮጵያዉንና ኤርትራዉያን ችግረኞችን ረድተዋል
ደርባን።ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንና ኤርትራዉያን ከዚሕ ቀደምም የተለያየ ጥቃት፣ዘረፋና የተፈጥሮ አደጋም ያጋጥማቸዉ ነበር።አቅም ሲኖራቸዉ ደግሞ የተቸገሩትን ይረዳሉ።ምስል Cosmos Michael

የኢትዮጵያዉያን ማሕበራትና ተቋማት ጥረት

ዳዊት አክሎ እንደሚለዉ የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት የሚያደርግባቸዉ ጫናእንዲቃለል ኢትዮጵያዉያኑ በተናጥልም፣ በመሰረቷቸዉ የተለያዩ ማሕበራት፣ እድሮችና  በመገናኛ ዘዴ ተቋማት አማካይነትም ግፊት እያደረጉ ነዉ። ኢትዮጵያዉያኑም ጉዳዩን በቅጡ እንዲረዱት፣ እርስ በርስ እንዲተባበሩም ማሕበራቱ እየጣሩ ነዉ።

«ኢትዮጵያን ኮሚኒቲዎች በተቻለ መጠን የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት፣ በተለያየ ሚዲያ፣ በዕድር፣ከኛ እሚጠበቀዉን ለማሟላት በተለያየ መንገድ ጥረት እያደረጉ ነዉ።ሰዉ ባለበት አካባቢ ካለዉ ከሕግ አካልም፣ ከማዘጋጃቤትም ጋር በምን ዓይነት መንገድ መሥራት እንዳለበት---» 
አቶ ይርጋለም የሚመሩት የቅን ልቦች ማሕበር ከተመሠረተ አምስት ዓመቱ ነዉ።ቀዳሚ አላማዉ የጤና፣የሥራ ማጣት፣ የኑሮ ቀዉስ የገጠማቸዉን ኢትዮጵያዉያንን መርዳት ነዉ።
                                   
«በራሳቸዉ ችግር ምክንያት፣ ወይም ባንዳንድ ችግር ምክንያት ጎዳና የወጡ ወንድሞቻችንን እያነሳ ሕክምና እንዲያገኑ፣ ከታከሙ በኋላ ሥራ እንዲሠሩ፣ ወደ እናት ሐገራቸዉ መግባት የሚሽቱን ደግሞ ወደ ሐገር ቤት በመላክ----»
ይሁንና ኢትዮጵያዉያን አሁን ከመንግሥት የሚደረግባቸዉን ጫናም ለመቋቋም በሚደረገዉ ጥረትም ተሳታፊ ነዉ።«የሕዝብ ማሕበር እንደመሆኑ መጠን« ይላሉ አቶ ይርጋለም።
«የሕዝብ ማህበር እንደመሆኑ መጠን ይሕ ጉዳይ ይመለከተናል።እኛንም የሚያስጨንቀን ጉዳይ ነዉ።»
ችግሩ መፍትሔ የሚያገኝበት ብልሐት እስካሁን በግልፅ አይታወቅም።ጥረቱ ግን በየመስኩ ቀጥሏል።ደቡብ አፍሪቃ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን እንደሚሉት ቁጥራቸዉ ከአንድ ሚሊዮን አያንስም። 

Logo Äthiopische Community in Südafrika

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ