1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ: ጥምር መንግሥት ያስፈለገዉ ANC

ቅዳሜ፣ ግንቦት 24 2016

በፕሬዝዳንት ሲረል ራማፎሳ የሚመራው የደቡብ አፍሪቃ ገዥ ANC ፓርቲ አብላጫ ድምፅ ሳያጣ አይቀርም፤ ጥምር መንግሥት መመስረት ይኖርበታል፤ የሚል የሕዝብ አስተያየቶች የተሰሙበት ምርጫ፤ የድምፅ ቆጠራዉ እየተካሄደ ነዉ። ባለስልጣናት ከፍተኛ መራጮች የታዩበት ምርጫ ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/4gWJo
የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ
የደቡብ አፍሪቃ ምርጫምስል Themba Hadebe/AP Photo/picture alliance

የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ: ጥምር መንግሥት ያስፈለገዉ ANC

በፕሬዝዳንት ሲረል ራማፎሳ የሚመራው የደቡብ አፍሪቃ ገዥ ANC ፓርቲ አብላጫ ድምፅ ሳያጣ አይቀርም፤ ጥምር መንግሥት መመስረት ይኖርበታል፤ የሚል የሕዝብ አስተያየቶች የተሰሙበት ምርጫ፤ የድምፅ ቆጠራዉ እየተካሄደ ነዉ። በምርጫ ማዕከሎች ረጅም የምርጫ ሰልፎች ማስተናገዳቸዉን የታዘቡ ባለስልጣናት ከፍተኛ መራጮች የታዩበት ምርጫ ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰጥተዋል።   

የምርጫ ጣብያ ሠራተኞች ድምፅ መቁጠር የጀመሩት ባለፈዉ ረቡዕ ከምሽቱ 3 ሰዓት የምርጫ ጣብያዎች ከተዘጉ በኋላ ነበር። የደቡብ አፍሪቃ ነፃ የምርጫ ኮሚሽን (IEC) በህጉ መሰረት በሰባት ቀናት ውስጥ ውጤቱን ማሳወቅ ይኖርበታል። ይሁን እንጂ የደቡብ አፍሪቃ ነፃ የምርጫ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሳይ ማቦሎ ሰባት ቀናት ሳይሞላዉ ይፋ ሊደረግ  እንደሚችል አመላክተዋል።

የምርጫ ጣብያዎች በይፋ ተዘግተዉ የድምፅ ቆጠራዉ ጀምሯል

የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ ድምፅ ቆጠራ 2024
የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ ድምፅ ቆጠራ 2024ምስል Phill Magakoe/AFP/Getty Images

ረቡዕ እለት በወጡ የመጀመርያ ደረጃ ዉጤቶች መሰረት፤ የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) 42.3 በመቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመምራት ላይ ይገኛል። ዴሞክራቲክ አሊያንስ (DA) ፓርቲ ከተያዙት ድምጾች 23.9 በመቶ ድርሻ ይዞ በርቀት ይከተላል። በዚህ የግማሽ የድምጽ ቆጠራ የመጀመርያ ዉጤት መሰረት በርካታ ተንታኞች በሀገሪቱ ከሚገኙ ዘጠኝ ክፍለ ሃገራት በሰባቱ እየመራ የነበረዉ ገዥው ANC ፓርቲ ከ50 በመቶ በታች ዉጤት እንደሚያገኝ  ተንብየዋል።  የፖለቲካ ተንታኝ ሳንድሌ ስዋና ANC በመጀመርያ የድምፅ ቆጠራ ዉጤት ከፍተኛ ቢሆንም የገዥዉ የ ANC ፓርቲ የመጨረሻ  ውጤት ከ50 በመቶ በታች ሲሉ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ።

"የ ANC ን ታሪካዊ ርምጃ  በማየት  እና የ MK ን መሰንጠቅ  ብናቀናጅ፣ ገዥዉ የ ANC ፓርቲ በምርጫዉ 42 በመቶ ገደማ ዉጤት ላይ ሊያበቃ እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል"

የአምስት ወራት እድሜ ያለዉ (MK) ፓርቲ ማለትም ዩምኮንቶ ዌሲ ዝዌ ይፋ በሆነዉ የመጀመርያ መዘርዝር  ትልቁና አስገራሚ ዉጤትን  አሳይቷል። (MK )ፓርቲ  በመጀመርያ ዉጤት መዘርዝር ከ11 በመቶ በማግኘት በአገሪቱ የምርጫ ሰሌዳ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል። ፓርቲዉ በክዋዙሉ ናታል ግዛት ትናንት አርብ በታየዉ የግማሽ ዉጤት መሰረት በሰፊ ልዩነት እየመራ ነዉ።

የ MK ዋና ሊቀመንበር ሲህሌ ንጉባቤን ለDW እንደገለፁት በሃገሪቱ ፓርቲ ባከናወነው ተግባር ለመጀመሪያ ጊዜ የተደነቀ ብለዉታል።

«በእዉነቱ ደስ ይላል፤ በጣም ደስ ይላል። ያም ሆነ ይህ፤ ይህን ዉጤት እንጠብቅ ነበር። የምርጫ ዘመቻዉን ስናካሂድ መሬት ላይ ምን እያደረግን እንደሆነ እናውቅ ነበር። ለነዋሪዎች ስለ MK ፓርቲ እውነቱን እየነገርን ለምን MK ን መምረጥ እንዳለባቸዉ አስረድተናቸዋል። አሁን ስላለው መንግሥትም እውነቱን ነግረናቸዋል።»

የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ 2024
የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ 2024ምስል Emilio Morenatti/AP Photo/picture alliance

ውጤቱ ይፋ የሚሆነዉ መቼ ይሆን?

ምንም እንኳ በርካታ መራጮች የድምፅ ቆጠራዉ አዝጋሚ እንደሆነ ቢገልጽም፣ ውጤቱ አጠያያቂ እንዳይሆን ለማረጋገጥ እና የተሟላ ሆኖ እንዲቀርብ እየተሰራ መሆኑን የደቡብ አፍሪቃዉ የነፃ ምርጫ ኮሚሽን አስታዉቋል። ሁሉም የድምፅ ቆጠራ የሚካሄደው ድምፅ በተሰጠባቸዉ በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያዎች ነዉ።  ይህ የሚከናወነዉ ደግሞ በፓርቲ ወኪሎችና ታዛቢዎች ፊት ነዉ። ከዚያም ቆጠራዉ ሲጠናቀቅ ውጤቱ ወደ ጎቴንግ ግዛት ሚድራንድ ወደ ሚገኘው ብሔራዊ የምርጫ ማዕከል ዋና መስርያቤት ከመተላለፉ በፊት በእያንዳንዱ የምርጫ ጣብያ ቅፅር ጊቢ ፊት ለፊት በሚገኝ ሰፊ ሰሌዳ ላይ ለሕዝብ በይፋ ይቀርባል።

በምርጫ እለት የሚያጋጥሙ ፈተናዎች

በብሔራዊው የነፃ ምርጫ ማዕከል ከተለያዩ ግዛቶች የመጡ የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት በአንድነት ይደመራል። ይህን ዉጤት የምርጫ ኮሚሽን ይፋ ከማድረጉ በፊት በኮሚሽኑ የቀመር ቡድኖች እንደሚመረመር እና የመጨረሻዉ ዉጤት ምርጫዉ በተካሄደ በሰባተኛዉ ቀን ይፋ እንደሚሆን የኮሚሽኑ ተለዋጭ ኃላፊ ዴቪድ ማንዳሃ ተናግረዋል።

"በእኛ እምነት ቅዳሜና እሁድ ውጤቱን ለማሳወቅ ዝግጁ ነን፤ ለማለት መቻል አለብን" 

ረቡዕ ዕለት የተካሄደው የምርጫ ሂደት በአንዳንድ ጣብያዎች ባጋጠሙ የተበላሹ የኤሌክትሮኒክ የምርጫ መሳርያዎች፤ እና ባጋጠመ የመብራት መቋረጥ፤ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከደቡብ አፍሪቃውያን ከፍተኛ ቅሬታ እና ትችት ተሰምቷል።

በተለይ በጆሃንስበርግና በደርበን ዉስጥ በሚገኙ በርካታ የምርጫ ማዕከሎች የምርጫ ጣብያዎች ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ከተዘጋም በኋላ ተጨማሪ ረጅም ሰልፎች ታይተዋል። የጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነውችዉ ቻርሜን ሻባላላ የምርጫ ጣብያዉ ከተዘጋ ከ2 ሰዓት በኋላም ተስፋ አልቆረጠችም ነበር።

"በደቡብ አፍሪቃ እየተፈጸሙ ባሉ ብዙ ነገሮች ደክሞናል። የምንፈልገዉ ለውጥ ብቻ ነዉ። ስለዚህ ድምፅ መስጠት እንፈልጋለን"

የደቡብ አፍሪቃ የምርጫ
የደቡብ አፍሪቃ የምርጫምስል Michele Spatari/AFP/Getty Images

ጥምር መንግስት የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ ዉጤት ግምታዊ አስተያየቶች

በምርጫዉ 50 በመቶ በታች ዉጤትን እንደሚያገኝ ተተንብዮ የነበረዉ የደቡብ አፍሪቃዉ ገዥ ፓርቲ ANC፤ በወጡት የመጀመርያ ዉጤቶች መሰረት ትንበያዉ እዉን እየሆነ ይመስላል። በዚህም በአሁኑ ወቅት ምናልባትም የጥምር መንግሥት ለመመስረት የሚሉ ዉይይቶች እየተካሄዱ ነዉ።  በምርጫዉ የተሳተፉ ፓርቲዎች የመጨረሻዉ ዉጤት ይፋ እስኪሲደረግ ካርዳቸውን ደረታቸዉ ኪስ አድርገዉ ለጥምር መንግሥት ዉሳኔ እየተዘጋጁ መሆኑን ይገልፃሉ።

ምንም እንኳ ብዙ ፓርቲዎች ከገዢው ANC ፓርቲ ጋር ምንም ዓይነት ጥምረት ላለመፍጠር ቃል ቢገቡም፣ ANC  መንግሥት ለመመስረት የሚያስፈልገውን 50.1 በመቶ ድምፅን ለማግኘት ከሌላ ትልቅ ተቃዋሚ ፓርቲ ጋር ጥምረት እንደሚያስፈልገው አሁን መገመት እንደሚቻል ብዙዎች ይናገራሉ።  

የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ
የደቡብ አፍሪቃ ምርጫምስል Rajesh Jantilal/AFP/Getty Images

የደቡብ አፍሪቃ የምርጫ ታዛቢዎች ምርጫዉ ያለምንም እክል አልፏል ሲሉ የእጅ አዉራጣታቸዉን ከፍ አድርገዉ አሳይተዋል። የምርጫ ተቋም ለአፍሪቃ ዘላቂ ዴሞክራሲ የተባዉን ድርጅት የሚመሩት እና የደቡብ አፍሪቃ ምርጫ ታዛቢ የነበሩት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጉድለክ ጆናታን የደቡብ አፍሪቃዉ ነፃ ምርጫ ኮሚሽን ከአህጉሪቱ የመጀመርያዉ እና ጠንካራዉ በመሆኑ በስራዉ እምነት አለኝ ብለዋል። 

«በደቡብ አፍሪቃ የምርጫ ኮሚሽን ላይ እምነት አለኝ። በአፍሪቃ ምርጥ ከሚባሉ የምርጫ ኮሚሽኖች አንዱ ነዉ። በጣም ጥሩ ሥራ እየሠሩ ነው ። አዎ፤ ሊመለከቷቸው የሚገቡ አንዳንድ ነጥቦች አሉ። እስካሁን ግን ጥሩ እየሰሩ ነው"

ቱሶ ኩማሎ / አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ