ማሕደረ ዜና፣ የICJ ዉሳኔ፣ የደቡብ አፍሪቃ ድልና የፍትሕ እንዴትነት
ሰኞ፣ ጥር 20 2016
መንግሥታት እራሳቸዉ ያረቀቁ-ያፀደቁትን ደንብ ወይም ሕግ ማክበር-መጣሳቸዉ እንደ እስከዛሬዉ ሁሉ ወደፊትም ማወዛገብ፣ ማከራከር ማነታረኩ አይቀርም።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፍትሕ ፍርድ ቤት (ICJ በምሕፃሩ) ግን በአይሁድ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል የተፈፀመበት 79ኛ ዓመት በሚዘከርበት ዋዜማ የአይሁዳዊቱ ሐገረ-መንግስት እስራኤልን የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳትፈፅም በይኗል።አርብ።ብይኑ ተንታኖች እንደመሰከሩት ለደቡብ አፍሪቃ ድል፣ለፍልስጤሞች አለኝታ፣ ለአፍሪቃዉያን ተስፋ፣ለአረቦች ዉርደት፣ ለእስራኤል ሽንፈት፣ ለምዕራብ መንግስታት ሐፍረት፣ ለፍትሕ ትንሽ ግን ታሪካዊ ክስተት ነዉ።የፍርድ ቤቱ ምንነት፣ የዉሳኔዉ ይዘት፣ የገጠመዉ አፀፋ እንዴትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ-አብራችሁኝ ቆዩ።
አንድም ሁለትም መሳዮቹ
እርግጥ ነዉ ዘርዘር፣ ተንተን ሲል ስም፣ ምግባር፣ ዕድሜ አሰራራቸዉ ለየቅል ነዉ።የመጀመሪያዉ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አኩል የተመሰረተ-1945 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ)፣ የድርጅቱ አካልም ነዉ።የዓለም ፍትሕ ፍርድ ቤት-International court of Justice (ICJ) ይባላል።ሁለተኛዉን ዓለም ያወቀዉ በ1998 ነዉ።የዓለም የወንጀለኛ ፍርድ ቤት-Internationale Criminal Court (ICC) ይባላል።
የሁለቱም ዳኞች የሚሰየሙት ከመላዉ ዓለም ነዉ።ሁለቱም የሚያስችሉት ዘ-ሔግ ኔዘላንድስ ነዉ።እና አንድም ሁለትም ይመስላሉ።እዚያዉ ዘ ሔግ ኔዘርላንድስ የሚኖሩት ኢትዮጵያዊዉ የሕግ ባለሙያ ዶክተር አደም ካሴ ትንሽ ያስረዱናል።«የዓለም የፍትሕ ፍርድ ቤት የሚባለዉ፣ ሥልጣን ያለዉ በዋነኛነት በሐገራት መካከል ያሉ ልዩነቶችን ግጭቶችን፣ የሕግ ክፍተኞችን የሚሞላ ፍርድ ቤት ነዉ።የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት የሚባለዉ ደግሞ በሐገራት መካከል ሳይሆን የግለሰቦችን የወንጀል ኃላፊነት የሚወስን ነዉ---»
የዛሬ ትኩረታችን ሥለመጀመሪያዉ ነዉ።የዓለም ፍትሕ ፍርድ ቤት (ICJ)።እስራኤል በጋዛ ፍልስጤሞች ላይ የከፈተችዉ ጥቃት፣ የጣለችዉ የምግብ፣ የመድሐኒት፣የመዘዋወርና የመኖር እገዳ፣ ባለeልጣኖችዋ የሚያስተላልፉት መልዕክትና ሌሎችም እርምጃዎች ከዘር ማጥፋት ወንጀል ይቆጠራል በማለት ፍርድ ቤቱ የእስራኤልና እርጃዎች እንዲያስቆም ደቡብ አፍሪቃ ከሳለች።እስራኤል ክሱን ዉድቅ አድርጋ ተከራክራለች።
የዓለም የፍትሕ ፍርድ ቤት ዉሳኔ
ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር አድምጦ ባለፈዉ አርብ በስድት ጉዳዮች ላይ ጊዚያዊ ብይን ሰጥቷል።አስራ-አምስት መደበኛ ዳኞችና ከሳሽና ተከሳሾችን የሚወክሉት ሁለት ዳኖች በጥቅሉ 17 ዳኞች የተሰየሙት ችሎት ፕሬዝደንት ጆኦን ኢ ዳግሁ በንባብ ባሳሙት ጊዚያዊ ብይን መሠረት የእስራኤል መንግስት የዘር ማጥፋት ወንጀልን መከላከል፣ ርዳታ እንዲቀርብ መፍቀድና መረጃ መጠበቅ አለበት።
«1. 15 ለ 2 በሆነ ድምፅ፣ የእስራኤል መንግስት የጠር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቅጣት የሚደነግገዉን ደንብ ለማክበር በገባዉ ግዴታ መሰረት፣ጋዛ ከሚኖሩ ፍልስጤሞች ጋር በተያያዘ፣በደንቡ አንቀፅ II መሰረት እነዚያ ወንጀሎቹን ለመከላከል አቅሙ የሚፈቅደዉን ሁሉ ማድረግ አለበት።በተለይ፣ ሀ) የቡድን አባላትን መግደል፣ለ)በቡድን አባላት ላይ ከፍተኛ አካላዊና አዕምሯዊ ጉዳት ማድረስ፣ ሐ)በቡድኑ አባላት ላይ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ አካላዊ ጥፋት ለማድረስ ያለመ ሆን ተብሎ የሚፈፀም ጉዳት፣ መ) በቡድኑ ዉስጥ ወሊድን ለመከላከል ሆን ተብሎ የሚወሰድ እርምጃን።»
ፍርድ ቤቱ ያሳለፈዉን ጊዚያዊ ብይን እስራኤል ገቢር ማድረግ አለማድረጓን ባንድ ወር ጊዜ ዉስጥ እንድታረጋግጥ አዝዟልም።ይሁንና ደቡብ አፍሪቃ በጠየቀችዉ መሠረት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ ላይ የከፈተችዉ ድብደባ ሙሉ በሙሉ እንዲያቆም አላዘዘም።እንደገና ደክተር አደም።
«ደቡብ አፍሪቃ የጠየቀችዉን የጦር ማቆም (ተኩስ አቁም)----የሚጠይቀዉን ነገር በግልፅ ባይልም ፍርድ ቤቱ የሰብአዊዉ ርዳታ እንዳይቋረጥ፣ ዘር ማጥፋት ወንጀል እንዳይከሰት፣ የሚደረጉ ንግግሮች እንዲቆሙ፣ መረጃዎችን እንዳይጠፉ---ለጊዜዉ ርምጃዎችን ወስዷል።»
የደቡብ አፍሪቃ ድልና ትርጓሜዉ
ደቡብ አፍሪቃ ዉሳኔዉን በደስታ ተቀብላዋለች።የሐገሪቱ ፕሬዝደንት ሲሪያል ራማፎዛ እንዳሉት መንግስታቸዉ ክሱን ሲመሠርት የንቀትም፣ የቅንነትም የሚመስሉ አስተያትና ማስጠንቀቂያዎች ሲሰጡት ነበር።«ICJ ዛሬ የሰጠዉ ትዕዛዝ እንድምታ የዘርማጥፋት ለመፈፀሙ አሳማኝ ጉዳይ መኖሩን (ጠቋሚ) ነዉ።ይሕ የጋዛ ሕዝብ ፍትሕ እንዲያገኝ ለምናደርገዉ ጥረት የመጀመሪያዉ ጠቃሚ ርምጃ ነዉ።አንዳዶች የራሳችንን ጉዳይ እንደንመለከትና በሌሎች ሐገራት ጣልቃ እንዳንገባ ሲነግሩን ነበር።ሌሎች ደግሞ ቦታችን እንዳልሆነ ሲነግሩን ነበር።ይሁንና መነፈግን፣ የዘር መድሎና መንግስት የሚያደርሰዉን ግፍ በጣም ጠንቅቆ እንደሚዉቅ ሕዝብ፣ ይሕ በርግጥ ትክክለኛዉ ቦታችን ነዉ።»
ለዓለም ሠላም፣ ለፍትሕ፣ ለሰዎች እኩልነት አጥብቀዉ እንደሚሟገቱ መዓለት ወሌት የሚደሰኩሩት ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎቻቸዉ ሙሉ በሙሉ የተመሰጉበት እልቂት እንዲቆም አፍሪቃዊቱ ሐገር መጠየቋን አልተቀበሉትም።
በኖተርዳም ዩኒቨርስቲ የሕግ ፕሮፌሰር ማሪይ ኤለን ኦኮኔል እንደሚሉት የአርቡ ዉሳኔ ለደቡብ አፍሪቃ ድል፣ ለፍትሕም አንድ ርምጃ ነዉ።
«ደቡብ አፍሪቃ ግልፅ አሸናፊ መሆኗን አይቻለሁ።መጀመሪያ ዓለም አቀፍ ሕግ በግልፅ፣ ፊትለፊትና ከመሐል እንዲታይ፣ ሁሉም ወገኖች ማክበር እንዳለባቸዉ በማድረጓ አሸንፋለች።በተከታታይ ያቀረበቻቸዉ ጥያቄዎች 16 ለ1፣ 15 ለሁለት በሆኑ ድምፆች ተቀባይነት አግኝተዋል።ይሕ ግልፅ ድል ነዉ።ባጠቃላይ ደቡብ አፍሪቃ በዚሕ ጉዳይ ድል አድርጊ ናት።»
ዶክተር አደምም በፕሮፌሰር ማሪይ ኤለን ኦኮኔል አስተያየት ይስማማሉ።ሌላዉ ቀርቶ የእስራኤልን መንግስት የወከሉት ዳኛ ሳይቀሩ ከስድስቱ ዉሳኔዎች ሁለቱን ደግፈዋል።
«ወደ አራቱ የሚሆኑት በ15 ለሁለት፣ ሁለቱ ጉዳዮች ግን 16 ለ1 (በሆነ ድምፅ ነዉ) የጠደቁት።ያማለት በሁለቱ ጉዳዮች ላይ የእስራኤል መንግት የወከላቸዉ ዳኛ ደቡብ አፍሪቃን ደግፎ ድምፅ ሰጥቷል ማለት ነዉ።-----»
ደቡብ አፍሪቃ በአረቦቹ ፍልስጤሞች ላይ የሚፈፀመዉ ግፍ እንዲቆም ያቀረበችዉን ክስ፣አፍሪቃዊቱ ዳኛ ዋና ተቃዋሚ ሆኑ።ዩጋንዳዊቱ ዳኛ ስድቱንም የክስ ጨብጦች ተቃዉመዋል።የዩጋንዳ መንግስት ዉሳኔዉ የዳኛዋ እንጂ የዩጋንዳ መንግስትን እንደማይወክል አስታዉቋል።
ሴትዮዋ 15ና 16 ባልደሮቦቻቸዉ የደገፉትን ዉሳኔ የተቃወሙት ጉዳዩ ፖለቲካዊ እንጂ የፍርድ ቤት አይደለም በሚል ነዉ።የእስራኤል ጠበቆች ወይም ተወካዮችም መጀመሪያ ላይ የተከራከፉት ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ጨርሶ ዉድቅ እንዲያደርገዉ ነበር።አላደረገዉም።
የአርቡ ዉሳኔ የምዕራብ ኃያላን መንግስታት የሚደግፉትን ርምጃ በመቃወም የተላለፈ በመሆኑ ታሪካዊ ነዉ። ዉሳኔዉ የጀርመን ናዚዎች በአይድ ላይ የፈፀሙት የዘር ማጥፋት ወንጀል 79ኛ ዓመት በሚዘከርበት ዋዜማ በመተላለፉ ታሪካዊ ነዉ።
አፍሪቃዊት ሐገር የመሰረተችዉን ክስ ዋና ዳኛ ዳግሁን የመሳሰሉ የአሜሪካና የሌሎች ሐገራት ዳኞች ሲደግፉት አፍሪቃዊቱ (ዩጋንዳዊቱ) ዳኛ መቃወማቸዉም ታሪካዊ ያደርገዋል።ታሪካዊዉን ብይን ፍልስጤሞች ደግፈዉታል።የፍልስጤም ራስ ገዝ መስተዳድር ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሪያድ ማሊኪ እንዳሉት የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ለሰብአዊነትና ለፍትሕ የቆመ ነዉ
«ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ያሳለፈዉን ጊዚያዊ ትዕዛዝ ፍልስጤም በደስታ ይቀበለዋል።የICJ ዳኞች እዉነታዉን ሕጉን አጢነዋል።ሰብአዊነትንና ዓለም አቀፍ ሕግን በደገፍ ወስነዋል።»
የደቡብ አፍሪቃን ድል አድራጊነት፣ የአፍሪቃን ኩራት፣ የዩጋንዳዊቱን ዳኛ ተቃዉሞ፣ የፍልስጤሞችን ድጋፍ ያገኘዉ ብይን ለአረቦች ዉርደት ለምዕራባዉያን ሐፍረት ይሕ ቢቀር ዶክተር አደም እንደሚሉት ፈታኝ ነዉ የሆነዉ።
«እኛ የዓለም ዓቀፍ ሕግ ሐዋርያት ነን፣ የዓለም አቀፍ ሕግ ጠባቂዎች ነን የሚሉ አካላት ላይ ከፍተኛ ፈተና ዉስጥ ነዉ ያስገባቸዉ።ፍርድ ቤቱ ፕሬዝደንቷ አሜሪካዊት ናቸዉ።አብዛኛዎቹ ፍርድ ቤቱ ላይ የሚቀመጡት ምዕራባዉያን ከሚባሉ ሐገራት ነዉ።በቀላሉ ዝም ብለዉ፣ ፖለቲካዊ ነዉ፤ ትክክል አይደለም፣ አንቀበልም ብለዉ የሚተዉት አይደለም።»
የፍርድ ቤቱ ዉሳኔና እስራኤል
የሕግ ፕሮፌሰር ሜሪይ ኤለን ኦኮኔል እንደሚሉት ዉሳኔዉ በትክክል ከተጤነ ለእስራኤል እንደ ሽንፈት ሊቆጠር አይገባም።«ቢሆንም በዚሕ ጉዳይ እስራኤል እንደ ተሸናፊ መታየት የለባትም።በፍርድ ቤቱ ጠንካራ ሙግት አድርጋለች።በዉሳኔዉም ከፈለገቻቸዉ ጉዳዮች ብዙዎቹን አግኝታለች።ከሁሉም በላይ በተሰጣት የአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ በእዉነቱ መልካም ስሟን ማደስ ትችላለች።«
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ግን ይኽን የተቀበሉት አይመስልም።ኔታንያሁ ከሳሽ፣ በያኞቹን የሐማስ ደጋፊ፣ አዲሶቹ ናዚዎች በማለት ወንጅለዋቸዋል።
«ዛሬ የዓለም ሆሎካዉስት ዕለት ነዉ።ትናንት፣ የዓለም ሆሎካዉስት ዕለት በሚታሰብበት ዋዜማ የሆነዉን ዓይነት ቧልት የለም።ዛሬ ዘ ሔግ የተሰበሰቡት እኛን በዘር ማጥፈት ለመወንጀል የሐሰትና አናዳጅ ክስ መስርተዋል።በማስም ነዉ የመጡት? የመጡት በሐማስ ስም፣ በአዲሶቹ ናዚዎች ስም፣ እኛ ላይ የዘር ማጥፋት ለመፈፀም ነዉ።»
ብይኑ ጊዚያዊ ግን አሳሪ ወይም ገዢ ነዉ።ገቢር ይሆን ይሆን?ዶክተር አደም መልሳቸዉ አይ አዎ ብጤ ነዉ።
«እንደምታዉቀዉ የዓለም አቀፍ ሕግ እንደ ሐገር ሕግ አይደለም። ፖሊስ ወይም ወታደር እሚያስፈፅመዉ አካል የለም። ነገር ግን በተለይ እንደዚሕ አይነት ነገሮች ሲከሰቱ፣ ሐላፊነት ያለባቸዉ ሐገራት የመቀበልና የማስፈፀም ግዴታ አለባቸዉ።»
ፍርድ ቤቱ በየነ።የጋዛ ፍልስጤሞች እልቂትቀጠለ።የእልቂቱ መዘዝ ከዮርዳኖስ እስከ ሊባኖስ፣ ከኢራቅ እስከ የመን እስከ ሶሪያ ያን ምድር በጥቃት አፀፋ ጥቃት እያተረመሰዉ ነዉ።የዋሽግተን፣ ለንደን ብራስልስ ተባባሪዎች፣ የካይሮ-ሪያድ አቡዳቢ ተከታዮቻቸዉም እስካሁን ኢራንን ከማዉገዝ፣ ከሐማስ እስከ ሒዝቦላሕ፣ ከሁቲ እስከ ኢራቅ ያሉ አማፂያንን ካማሳደድ ባለፍ ያደረጉት ካለ የወታደሮቻቸዉን ሕይወት መገበር እንጂ ለሰላም የፈየዱት የለም።
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ