1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጥቅምት 5 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥቅምት 5 2016

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች እንደተለመደው አመርቂ ድሎችን አመዝግበዋል ። የአውሮጳ እግር ኳስ የማጣሪያ ግጥሚያዎች ቀጥሏል። ኖርዌይ በሜዳዋ ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ መሆኗ በርካቶችን አስደምምሟል ። የአቶ ፍቅሩ ኪዳኔ የሙት ዓመት መታሰቢያ ፈረንሳይ ውስጥ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ዝግጅቶች ተከናውኗል።

https://p.dw.com/p/4XbWp
የአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ
የአውሮጳ እግር ኳስ ዋንጫ፦ ፎቶ ከማኅደርምስል picture-alliance/dpa/EPA/G. Licovski

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች እንደተለመደው አመርቂ ድሎችን አመዝግበዋል ። የአውሮጳ እግር ኳስ የማጣሪያ ግጥሚያዎች ቀጥሏል። ኖርዌይ በሜዳዋ ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ መሆኗ በርካቶችን አስደምምሟል ። ጀርመናዊው የሽቱትጋርት አጥቂ ሴሮህ ጊራሲ በቡንደስሊጋው በአጭር ጊዜያት ውስጥ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ክብረወሰን ሰብሯል ። በኢትዮጵያ ስፖርት በተለይም በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ የሙት ዓመት መታሰቢያ ፈረንሳይ ውስጥ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ዝግጅቶች ተከናውኗል።

አትሌቲክስ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በካናዳ ቶሮንቶ፤ በኔዘርላንድስ አምስተርዳም እንዲሁም በሕንድ ዴልሂ የአትሌቲክስ ፉክክሮች ድል ተቀዳጅተዋል ። በቶሮንቶ ዋተርፍሮንት የማራቶን ሽቅድምድም ኢትዮጵያውያን ከአንደኛ እስከ አራተኛ ተከታትለው ገብተዋል። ያም ብቻ አይደልም እስከ አስረኛ ደረጃ ድረስ ስድስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተከታትለው ገብተዋል ።

በዚህ ፉክክር የሴቶች ዘርፍ አትሌት ቡዜ ድሪባ 2 ሰአት ከ23 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በመግባት አንደኛ በመውጣት ድል ተቀዳጅታለች ።  አትሌት ዋጋነሽ መካሻ ለጥቂት በ1 ሰከንድ ልዩነት የሁለተኛ ደረጃ አግንታለች ። አትሌት አፈራ ጎፋይ 2 ሰአት ከ23 ደቂቃ ከ15 ሰከንድ በመሮጥ የሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች ። አራተና ደረጃውም የተያዘው በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ፎዚያ ጀማል ሲሆን፤ ፎዚያ ከአትሌት አፈራ የተቀደመችው በ3 ሰከንድ ልዩነት ብቻ ነው ።

የመስከረም 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በወንዶቹ ተመሳሳይ ርቀት ፉክክር ኢትዮጵያ በአትሌት አዱኛ ታከለ የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ኬንያዊው አትሌት ኤልቪስ ኪፕቾጌ 2 ሰአት ከ9 ደቂቃ ከ20 ሰከንድ በመግባት አሸናፊ ሆኗል ። አትሌት አዱኛ ታከለ ሩጫውን ያጠናቀቀው 2 ሰአት ከ10 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ በመሮጥ ነው ። የሦስተኛ ደረጃውንም ኬንያዊው አትሌት አልፍሬድ ኪፕቸርቺር ይዞታል ።

በአምስተርዳም ማራቶንም ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መሠረት በለጠ አሸናፊ ሆናለች ። በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲነም ደረጃ በተሰጠው እና እሁድ ጥቅምት 04 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በተካሄደው የቲሲኤስ አምስተርዳም ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ አትሌት መሰረት በለጠ አሸናፊ የሆነችው ርቀቱን 2፡18፡21 ሮጣ በማጠናቀቅ ነው ። ያስመዘገበችው ሰዓት በኔዘርላንድ ዋና ከተማ ከተካሄዱ ማራቶኖች ሦስተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዘግቧል ። በዚህ ውድድር አትሌት መሠረት አበባየሁ በ2:19:47 ሰዓት 2ኛ በመውጣት ተጨማሪ ድል ተመዝግቧል ።  አሸቴ በክሪ በ2:21:50 ሰዓት 4ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች ።

ኢትዮጵያውያን በአትሌቲክሱ ዘርፍ በመላው ዓለም በርካታ ድሎችን አስመዝግበዋል።
ኢትዮጵያውያን በአትሌቲክሱ ዘርፍ በመላው ዓለም በርካታ ድሎችን አስመዝግበዋል። ፎቶ ከማኅደር ። ምስል Charlie Neibergall/AP/picture alliance

ትናንት በህንድ ደልሂ በተካሄደው የዓለም የሴቶች የግማሽ ማራቶን ፉክክርም ድሉ የኢትዮጵያውያን ሆኗል ። አትሌት አልማዝ አያና የህንድ ዴልሂ የዓለም ኤሊት የሴቶች የግማሽ ማራቶንን በ1:07:58 ሰዓት 1ኛ በመውጣት አሸንፋለች ። በአስደናቂ አጨራረስና ብቃት ለድል የበቃችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አልማዝ አያና ቀደም ሲልም በርካታ አመርቂ ድሎችን በዓለም መድረኮች አስመዝግባለች ።

አልማዝ አያና ቀደም ሲል በ5000 ሜትር የ2015 የቤጂንግ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አሸናፊ ስትሆን፤ በ10,000 ሜትር የ2017 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባለድል ናት ። በተመሳሳይ 10,000 ሜትር የ2016 የሪዮ ኦሊምፒክ አሸናፊ መሆኗም የሚታወስ ነው ። በዚሁ ምድብ በወንዶች አዲሱ ጎበና በ1:00:51 በሆነ ሰዓት 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል።

እግር ኳስ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ሰሞኑን የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው የሽቱትጋርቱን አጥቂ ሌሎች ቡድኖች ወደራሳቸው ለመውሰድ ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተዘግቧል።  የእንግሊዙ ብሬንትፎርድ ቡድን ይህን በቡንደስሊጋው የመጀመሪያ 7 ግጥሚያዎች 13 ግቦችን በማስቆጠር  ክብረወሰን የሰበረ አጥቂ ለመውሰድ ፍላጎት ማሳደሩ በሽቱትጋር ደጋፊዎች እና ቡድን ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሯል።  የሽቱትጋርቱ አጥቂ ሴሮህ ጊራሲ ከዚህ ቀደም በሮቤርት ሌቫንዶብስኪ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን መስበር የቻለ ብርቱ ተጨዋች ነው። የ27 ዓመቱ ሴሮህ ጊራሲ ከጊኒ ቤተሰቦች የተወለደ ሲሆን ዜግነቱ ፈረንሳዊ ነው ። 

የአውሮጳ እግር ኳስ የማጣሪያ ግጥሚያዎች ዛሬም ቀጥለዋል። ዛሬ ማታ ከሚኖሩ ጨዋታዎች መካከል፦ ቤልጂየም ከስዊድን፤ ግሪክ ከኔዘርላንድ የሚያደርጉት በበርካቶች ዘንድ የሚጠበቁ ናቸው ። በነገው ዕለት ከሚኖሩ ጨዋታዎች መካከል ደግሞ፦ እንግሊዝ ከጣሊያን፤ እንዲሁም ሉታንያ ከሐንጋሪ የሚያደርጉት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል። ሐንጋሪ እና ጣሊያን ከምድባቸው ተመሳሳይ 10 ነጥብ ስላላቸው ከተጋጣሚዎቻቸው ጋ የሚያደርጉት ፉክክር ይበልጥ አጓጊ ነው።  ቀደም ሲል ከነበሩ ግጥሚያዎች መካከል ኖርዌይ በገዛ ሜዳዋ ትናንት በስፔን 1 ለ0 ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ መሆኗ በርካቶችን አስቆጭቷል። ከምድቡ ስፔን እና ስኮትላንድ 15 ነጥብ ሲኖራቸው ኖርዌይ በ10 ነጥብ ተወስናለች ። ጆርጂያ 7 ነጥብ ሲኖራት ሲፕረስ በዜሮ ነጥብ በመጣችበት እግሯ ተመልሳለች ። ከምድቦቹ በአጠቃላይ ፖርቹጋል 21 ነጥብ በመሰብሰብ ማንም አልተስተካከላትም ።

የአቶ ፍቅሩ ኪዳኔ መታሰቢያ

«አንድ ሽማግሌ ሲሞት አንድ መጻሕፍት ቤት እንደተቃጠለ ይቆጠራል ። እንደሚባለው ይህ ጥቅስ በተለይ በአኅጉራችን ውስጥ እርግጠኝነቱ አያጠራጥርም » ይላሉ ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ ። «የፒያሳ ልጅ» በተሰኘው መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ያሰፈሩት አጠር ያለ ጥቅስ ነው ።  ጋሽ ፍቅሩ ኪዳኔ ለረዥም ጊዜ በኖሩባት ፈረንሳይ ፓሪስ ውስጥ ካለፉ አንድ ዓመት ተቆጥሯል ። ዝክራቸውንም ኢትዮጵያውያን የስፖርት አፍቃሪዎች እና የጋሽ ፍቅሩ ወዳጆች እና ቤተሰቦች ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ በግሩም ሁኔታ አሰናድተዋል።  የኢትዮጵያውያን ስፖርት እና ባህል ፌዴሬሽን በአውሮጳ የቀድሞው ሕዝብ ግንኙነት እንዲሁም ከፌዴሬሽኑ መካከል አንዱ እንዲሁም የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ግርማ ሣኅሌ  ለአቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ያዘጋጁት መታሰቢያ ካሰቡት በላይ መከናወኑን ገልጿል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ