1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 21 2016

በሪጋ የዓለም የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች የበላይነታቸውን ዐሳይተዋል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ፉክክሩ እጅግ ተጠናክሯል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ከታች ያደገው ዳርምሽታትድ ቬርደር ብሬመንን ኩም አድርጎታል ። በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ግጥሚያዎች ነገና ከነገ በስትያ ይቀጥላሉ ።

https://p.dw.com/p/4X3X5
በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ
በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይቀጥላሉ ።ምስል Matthieu Mirville/DPPI media/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በትናንቱ የሪጋ የዓለም የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን ጎልተው ወጥተዋል ። በተለይ በግማሽ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ጫፍ ደርሰው በኬንያውያን እንዴት ሊበለጡ ቻሉ? የአትሌቲክስ ስፖርት ተንታኝ አነጋግረናል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ፉክክሩ እጅግ ተጠናክሯል ። መሪው ማንቸስተር ሲቲ ባልተጠበቀ ሁኔታ በዎልቨርሀምፕተን መራር ሽንፈት ሲገጥመው፤ ሊቨርፑ በቪዲዮ አጋዥ ዳኛ(VAR)ባለሞያዎች ስህተት ነጥብ ጥሏል ። አርሰናል ገስግሶ በመድረስ ከመሪው በአንድ ነጥብ ልዩነት ተቃርቧል ። ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ሽንፈት አስተናግዷል ። በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ከታች ያደገው ዳርምሽታትድ ብዙ ልምድ ያለው ቬርደር ብሬመን ላይ በርካታ ግብ አስቆጥሮ ኩም አድርጎታል ። 

በቅድሚያም አትሌቲክስ

በላቲቪያ ዋና ከተማ ሪጋ ትናንት በተከናወኑ የዓለም የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን አትሌቶች የበላይነታቸውን ዐሳይተዋል ። አትሌት ድርቤ ወልተጂ በአንድ ማይል ርቀት አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በማስመዝገብ ድል ስትቀዳጅ፤ ሐጎስ ገብረሕይወት በ5 ኪሎ ሜትር ፉክክር ወርቅ አስገኝቷል ።

ለመጀመሪያ ጊዜ በላቲቪያ ሪጋ በተከናወነው የዓለም የጎዳና ላይ ውድድር፦ ኢትዮጵያ  በሁለት ወርቅ፤ በአራት የብር እና በአንድ የነሀስ በአጠቃላይ በሰባት ሜዳሊያ  ከዓለም የሁለተኛ ደረጀን ይዛ አጠናቃለች ።

በውድድሩ በተለይ በግማሽ ማራቶን ነግሠው የዋሉት ኬንያውያን በአምስት ወርቅ፤ በሦስት የብር እና በአራት የነሀስ በድምሩ በዐሥራ ሁለት ሜዳሊያዎች የአንደኛ ደረጃ ይዘው አሸንፈዋል ። አንድ የወርቅ እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ብቻ ያገኘችው ዩናይትድ ስቴትስ ሦስተኛ ደረጃ ስትይዝ፤ አንድም ወርቅ ሳታገኝ በአንድ የብር እና በአንድ የነሐስ ሜዳሊያ ብቻ የተወሰነችው ብሪታንያ አራተኛ ደረጃ አግኝታለች ።

የመስከረም 14 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በሪጋ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በ7 ሴቶች እና በ6 ወንዶች በአጠቃላይ በ13 አትሌቶች  ተወክላ ያስገኘችው ውጤት በአጠቃላይ ምን ያሳያል? በኢትዮ ኤፍ ኤም የኢትዮ ስፖርት መርኃ ግብር ዋና አዘጋጅ ምሥጋናው ታደሰ።

በትናንቱ የሪጋ የግማሽ ማራቶን በወንድም በሴትም ፉክክር ኬንያውያን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው በበላይነት አጣናቀዋል ። በዚህ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በወንድም በሴትም ብርቱ ተፎካካሪ ሆነው ከሜዳሊያ ውጪ ነበሩ ። በወንዶች ግማሽ ማራቶን  ኢትዮጵያ በጀማል ይመር  በኩል የ4ኛ ደረጃን አግኝታለች ። ንብረት መላክ 7ኛ፤ ፀጋዬ ኪዳኑ 10ኛ ሆነው ነው ያጠናቀቁት ። በሴቶች ተመሳሳይ ርቀት ጽጌ ገ/ሰላማ 4ኛ፤ ፍታው ዘርዬ 6ኛ፤ እንዲሁም ያለምጌጥ ያረጋል 28ኛ ደረጃ ይዘው ነው ያጠናቀቁት ። በማራቶኑ ዘርፍ ረዥም ጊዜ ርቆን የቆየው ድል በትእግስት አሰፋ ጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ክብረወሰኑ ጭምር ሲሰበር ትልቅ ተስፋ አጭሮ ነበር ። ትናንት ግን  በላቲቪያው የሪጋ የግማሽ ማራቶን ፉክክር ጫፍ ደርሰን ከሜዳሊያ ውጪ ሆነናል ። የቤርሊኑ የማራቶን ድል ተስፋን ለማስቀጠል ምን ነበር ትናንት የጎደለው?

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ትእግስት አሰፋ ክብረወሰን ያሸነፈችበት  የቤርሊን ማራቶን ።
በማራቶኑ ዘርፍ ረዥም ጊዜ ርቆን የቆየው ድል በትእግስት አሰፋ ጀርመን ቤርሊን ከተማ ውስጥ ባለፈው ሳምንት ክብረወሰኑ ጭምር ሲሰበር ትልቅ ተስፋ አጭሮ ነበር ።ምስል Markus Schreiber/AP/picture alliance

በትናንቱ ፉክክር በሴቶች ምድብ በአንድ ማይል ርቀት የተሳተፈችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ድርቤ ወልተጂ የውድድር ክብረ ወሰኑን በሰባት ሰከንድ አሻሽላ በ4 ደቂቃ ከ20.98 ሰከንድ አሸንፋለች ። በወንዶች በ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ደግሞ ሀጎስ ገብረ ሕይወት 12 ደቂቃ ከ59 ሰከንዶች በመሮጥ አሸናፊ ሁኗል ። ሐጎስ ገብረ ሕይወት አሸናፊ በሆነበት የወንዶች የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ዮሚፍ ቀጄልቻ ሁለተኛ ወጥቷል።  

እግር ኳስ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዛሬ ማታ ቸልሲ የከተማው ተቀናቃኙ ፉልሀምን ይገጥማል ። ለምሽቱ የለንደን ከተማ ቡድኖች ግጥሚያ ወደ ክራቨን ኮቴጅ ስታዲየም የሚያቀናው ቸልሲ 5 ነጥብ ብቻ ይዞ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ፉልሀም በስምንት ነጥብ ትንሽ ከፍ ብሎ 12ኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። ባለፈው ግጥሚያ ፉልሀም በሜዳው ቸልሲን አስተናግዶ የ2 ለ1 ሽንፈት ገጥሞት ነበር ።

ሊቨርፑል እና ቶትንሀም ሆትስፐር በደረጃ ሰንጠረዡ የበላይ ለመሆን ባደረጉት የቅዳሜ ዕለት ፍልሚያ ሊቨርፑል ባለቀ ሰአት የተከላካይ ድክመት እና የቪዲዮ አጋዥ ዳኞች(VAR) ስህተት ወሳኝ ነጥብ ጥሏል ። ሊቨርፑል ኩርቲስ ጆንስ በ26ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከተናበተበት በኋላ በሉዊስ ዲያዝ ያስቆጠረው ድንቅ ግብ ተሰርዞበታል ። ስህተቱን በተመለከተ የዳኞች አስተዳደር፦ «በሰው የተፈጠረ ከፍተኛ ስህተት» ብሎታል ። የቪዲዮ አጋዥ ዳኞች(VAR) ስህተት ነው በማለት አጥብቆ የተከራከረው ሊቨርፑል፦ «የስፖርት ልዕልና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል» በማለት ውሳኔውን አጥብቆ ኮንኗል ።

የመስከረም 7 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በ69ኛው ደቂቃ ላይ ዲዮጎ ጆታ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ዐይቶ በቀይ ካርድ መሰናበቱ ለሊቨርፑል ተጨማሪ ራስ ምታት ነበር ። በቅዳሜው እልህ አስጨራሽ ግጥሚያ በ9ኝ ተጨዋቾች ተወስኖ እስከ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተፋለመው ሊቨርፑልን የማታ ማታ በተፈጠረ የተከላካይ ስህተት ቶትንሀም ሆትስፐር ድል አድርጎ ደጋፊዎቹን አስቦርቋል።  መደበኛው 90 ደቂቃ የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪው ስድስተኛ ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ወደ ሊቨርፑል የገሰገሱት ቶትንሀሞች በጆዌል ማቲፕ የመከላከል ስህተት በገዛ መረብ ላይ ባረፈ ግብ 2 ለ1 አሸንፈዋል ።

የሉዊስ ዲያዝ የተሻረበት ግብ ያንገበገበው ሊቨርፑል፦ «በአሁኑ ወቅት ማናቸውንም አማራጮች እያጤንን ነው » ሲል በመግለጫው ጽፏል ። የቀድሞው የማንቸስተር ዩናይትድ እና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ጋሪ ኔቭል፥ የሊቨርፑልን መግለጫ «የተሳሳተ» ሲል ተችቷል ። በትዊተር ላይ ባሰፈረው ትችቱም፦ «ዬርገን ክሎፕ ትናንት ማታ ከጨዋታው በኋላ ጉዳዩን በደንብ ነው የያዙት ። በርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪያን የሆነው ነገር ይሰማቸዋል፤ ስህተትም መሆኑን ይቀበላሉ» ብሏል።  «ሆኖም የማታው የሊቨርፑል መግለጫ ስህተት ነው ። ሁሉንም አማራጮች እንጠቀማለን» ማለቱም ምንድን ነው? ሲልም አክሏል ። የቪዲዮ አጋዥ ዳኞች (VAR) በሌሉበት በመሀል ዳኛው ብቻ ውሳኔ ተሰጥቶበት ያደረውን ጨዋታ ጉዳይ በተመለከተ ሊቨርፑል በምን መልኩ ሊፈታ እንደፈለገ በእርግጥ የታወቀ ነገር የለም ።

ሊቨርፑል የቪዲዮ አጋዥ ዳኞች (VAR) ጉዳይ እጅግ አበሳጭቶታል ።
የቪዲዮ አጋዥ ዳኞች (VAR) በሌሉበት በመሀል ዳኛው ብቻ ውሳኔ መሰጠቱ ሊቨርፑልን ጎድቶታል ። ፎቶ ከማኅደርምስል David Blunsden/Action Plus/picture alliance

ትናንት በነበሩ ግጥሚያ፦ ኖቲንግሀም ፎረስት ከብሬንትፎርድ ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል ። በቅዳሜ ዕለት ግጥሚያዎች፦ አስቶን ቪላ ብራይተንን 6 ለ1 አበራይቷል ። ኤቨርተን በሜዳው በሉቶን ታውን የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ዌስትሀም ዩናይትድ ሼፊልድ ዩናይትድን እንዲሁም ኒውካስል በርንሌይን 2 ለ0 አሸንፈዋል ። ማንቸስተር ዩናይትድ በሜዳው ኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም ተጋጥሞ በክሪስታል ፓላስ የ1 ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል ። አርሰናል አስተማማኝ በሆነ መልኩ በበርመስ ሜዳ ተጫውቶ የ4 ለ0 ታላቅ ድል አስመዝግቦ ደጋፊዎቹን አስቦርቋል ። እንደቶትንሀም 17 ነጥብ ይዞም ደረጃውን  ወደ 3ኛ ከፍ አድርጓል ። ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ የሚበለጠው በአንድ ነጥብ ብቻ ነው ።

የጳጉሜ 6 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ማንቸስተር ሲቲ ታች 16ኛ ደረጃ ላይ በነበረው ዎልቨርሀምፕተን ተበልጦ የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። በተለይ ፔድሮ ኔቶ በ12ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ ክንፍ በማለፍ ወደግብ ያሻማት ኳስ በሩበን ዲያስ ተገጭታ በገዛ ማንቸስተር ሲቲ መረብ ላይ አርፋለች ። አማካይ መስመር ላይ ኮቫቺች እና ፎደን ግራ በመጋባታቸው ግብ የምትሆነው ኳስ ፔድሮ እግር ላይ አርፋለች ። ፔድሮን ኔቶን አኪምም ሊያቆመው አልቻለም ። የፔድሮ ኔቶ የተክለ ሰውነት እና ቴክኒክ ብቃት ጎልቶ የታየበት ግብ ነው ። ለማንቸስተር ሲቲ ጁሊያን አልቫሬዝ አቻ የምታደርገውን ግብ በ58ኛው ደቂቃ ላይ ቢቆጠርም፤ ደስታው ከጥቂት ደቂቃዎች በላይ አልዘለቀም ። 66ኛው ደቂቃ ላይ ሕዋንግ ሒ-ቻን የማሸነፊያዋን ግብ ለዎልቨርሀምፕተን አስቆጥሮ ጨዋታው በ2 ለ1 ተጠናቋል። 

ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ፦  ባየር ሌቨርኩሰን በ16 ነጥብ ይመራል።  ሽቱትጋርት 15 ነጥብ ይዞ ይከተላል ። ባዬርን ሙይንሽን እና ቦሩስያ ዶርትሙንድ በተመሳሳይ 14 ነጥብ ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ 3ኛ እና 4ኛ ላይ ይገኛሉ ።

በጀርመን የቡንደስሊጋ ግጥሚያ፦ ላይፕትሲሽ ከባየርንሙይንሽን
በጀርመን የቡንደስሊጋ ግጥሚያ ። ላይፕትሲሽ ከባየርንሙይንሽንበአሊያንስ አሬና ስታዲየም ።ምስል Hendrik Schmidt/picture alliance/dpa

በቡንደስሊጋው የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች በርካቶችን ያስደመመው ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገው ዳርምሽታድት  ቬርደር ብሬመንን 4 ለ2 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፉ ነበር ። ቬርደር ብሬመን በቡንደስ ሊጋው እና በዓለም አቀፍ ውድድሮች የበርካታ ዓመታት ልምድ ያካበተ ቡድን ነው ። ትናንት በነበረ ሌላ ግጥሚያ ፍራይቡርግ አውግስቡርግን 2 ለ0 አሸንፏል ።  ቅዳሜ ዕለት ላይፕትሲሽ ከባየርን ሙይንሽን ጋር ሁለት እኩል ተለያይቷል ። ባዬር ሌቨርኩሰን ማይንትስን 3 ለ0 ድል አድርጎ የደረጃ ሰንጠረዡ መሪነትን ተረክቧል ። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ ቦሁምን እንዲሁም ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሆፈንሀይምን 3 ለ1 አሸንፈዋል ።  ኮሎኝ በሽቱትጋርት፤ አይንትራኅት ፍራንክፉርት በቮልፍስቡርግ በተመሳሳይ የ2 ለ0 ሽንፈት ገጥሟቸዋል ።

ሻምፒዮንስ ሊግ

በአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ግጥሚያዎች ነገ እና ከነገ በስትያ ይቀጥላሉ ። በሁለቱ ቀናት ከሚኖሩ 16 ግጥሚያዎች መካከል፦ ማንቸስተር ሲቲ ከላይፕትሲሽ፤ ባርሴሎና ከፖርቶ ናፖሊ ከሪያል ማድሪድ፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከኤሲ ሚላን፤ አርሰናል ከሌን፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ከጋላታሳራይ፤ ባየርን ሙይንሽን ከኤፍሲኬ እንዲሁም ኢንተር ሚላን ከቤኔፊካ ጋር የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ይገኙበታል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ