1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ በጦርነት 80 ቢሊዮን ዶላር ውድመት እንደደረሰበት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ገለጸ

ማክሰኞ፣ የካቲት 5 2016

በጦርነቱ በትግራይ ላይ የደረሰው ውድመት በገንዘብ ሲተመን በአጠቃላይ 80 ቢልዮን ዶላር እንደሚገመት የገለፁት አቶ ጌታቸው ረዳ ይሁንና ይህ የሚያካክስ ድጎሞ እየተደረገ እንዳልሆነ ተናግረዋል። በዚህና ሌሎች ምክንያቶችም የክልሉ አስተዳደር ለበጀት ክፍተት ተዳርጎ እንዳለ ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4cM4H
Äthiopien | PK Friedensgespräche | Redwan Hussien und Getachew Reda
ምስል Siphiwe Sibeko/REUTERS

በትግራይ በጦርነቱ የደረሰው ጉዳት 80 ቢልዮን ዶላር ነው ተባለ

ጦርነቱ ተከትሎ በትግራይ ላይ የደረሰው ውድመት በገንዘብ ሲተመን በአጠቃላይ 80 ቢልዮን ዶላር መሆኑ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ገለፀ። የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ ለክልሉ መገናኛ ብዙሐን በሰጡት መግለጫ ውድመቱ የሚተካ ማካካሻ አሁንም እንደሌለ ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ በወቅታዊ ጉዳዮች የተናገሩት አቶ ጌታቸው ፥ በህወሓት እና ፌደራል መንግስቱ መካከል አሁንም "ተጨባጭ አለመተማመን" መኖሩ ጠቁመዋል። የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት የሚመለስበት አግባብ ለመፍጠርም ከፌደራል መንግስቱ ጋር መግባባት መደረሱ ፕሬዝደንቱ ገልፀዋል።

በቅርቡ የፌደራል መንግስቱ፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የስራ አፈፃፀም መገምገሙ የተናገሩት የአስተዳደሩ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ በነበረው ስብሰባ በዋነኝነት የፕሪቶርያ ውል እንዲሁም የጊዚያዊ አስተዳደር የስራ አፈፃፀም አጀንዳዎች እንደነበሩ ትላንት ማምሻው ለክልሉ መገናኛ ብዙሐን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

በወቅታዊ ጉዳዮች  ትላንት ማምሻው ለክልሉ መገናኛ ብዙሐን ማብራርያ የሰጡት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ የተለያዩ ጉዳዮች ዳሰዋል። በመግለጫቸው የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር የስራ አፈፃፀም በቅርቡ በፌደራል መንግስቱ መገምገሙ የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳበፕሪቶሪያ የሰላም ውል አፈፃፀም፣ በበጀት ጉዳዮች እና ሌሎች ፖለቲካዊ አጀንዳዎች  ከፌደራሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች ውይይት መደረጉም ጠቁመዋል። በፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ አመራር መካከል ተጨባጭ አለመተማመን መኖሩ የገለፁ ፕሬዝደንቱ፥ የፌደራል መንግስቱ ያሉት ጥርጣሬዎች እና ቅሬታዎች ማቅረቡን፥ በአስተዳደራቸው እና ህወሓት በኩል ደግሞ ምላሾች መሰጠታቸውን ገልፀዋል። አቶ ጌታቸው በመግለጫው በህወሓት እና ፌደራል መንግስቱ መካከል አሁንም "ተጨባጭ አለመተማመን" መኖሩ ጠቁመዋል።

በፌዴራል መንግስት እና የትግራይ ኃይሎች መካከል በፕሪቶሪያ ስምምነት ሲፈጸም
በቅርቡ የፌደራል መንግስቱ፥ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የስራ አፈፃፀም መገምገሙ የተናገሩት የአስተዳደሩ ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ በነበረው ስብሰባ በዋነኝነት የፕሪቶርያ ውል እንዲሁም የጊዚያዊ አስተዳደር የስራ አፈፃፀም አጀንዳዎች እንደነበሩ ትላንት ማምሻው ለክልሉ መገናኛ ብዙሐን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።ምስል PHILL MAGAKOE/AFP/Getty Images

"በአጠቃላይ አለማመን አለ። የመጣ ገንዘብ ቢመጣ ትጥቃችሁ ልታወርዱ ፍላጎት የላችሁም፣ ሰራዊታችሁ ልታጠናክሩ ነው የምትሹት የሚሉ የሚነሱ ነገሮች አሉ" የሚል ሀሳብ ከፌደራሉ መንግስት በኩል መቅረቡ አንስተዋል።

አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት
"በአጠቃላይ አለማመን አለ። የመጣ ገንዘብ ቢመጣ ትጥቃችሁ ልታወርዱ ፍላጎት የላችሁም፣ ሰራዊታችሁ ልታጠናክሩ ነው የምትሹት የሚሉ የሚነሱ ነገሮች አሉ" የሚል ሀሳብ ከፌደራሉ መንግስት በኩል መቅረቡ አንስተዋል።ምስል Million Haileselassie/DW

አቶ ጌታቸው "ያሉት የሕግ እንቅፋቶች በፍጥነት ጠርገን፥ ህወሓት ሕጋዊ ፓርቲነቱ የሚረጋገጥበት ሁኔታ ሊፈጠር ተግባብተናል። በፍትህ ሚኒስቴር በኩል ይህ የሚመለከት አፋጣኝ ውሳኔ ሊሰጥ የቤትስራ ወስዷል" ብለዋል።

ይሁንና "እኛ፥ ህልውናችን ከማረጋገጥ ውጭ፥ ሀገር የመበጥበጥ ፍላጎት እንደሌለን፣ ከምንም በላይ በሰላም የመኖር የትግራይ ህዝብ ፍላጎት ከማረጋገጥ ባለፈ አካባቢ የማመስ ይሁን፥ በአንድም በሌላም መንገድ የማእከል ስልጣን የመመኘት ፍላጎት እንደሌለን በደንብ ለማስረዳት ሞክረናል" ሲሉም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከፌደራል መንግስት አመራሮች ጋር በነበረ ውይይት እስካሁን ድረስ መቋጫ ያላገኘውየህወሓት የሕጋዊ ሰውነት ጉዳይ መነሳቱ የገለፁት ሲሆን፥ ያሉት የሕግ እንቅፋቶች በፍጥነት በመቅረፍ የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት ለመመለስ ከፌደራል መንግስቱ ጋር መግባባት መደረሱ አንስተዋል።

ሌላው የግዚያዊ አስተዳደሩ መሪ ያነሱት ጉዳይ ከበጀት ጋር የተያያዘ ነው። በጦርነቱ በትግራይ ላይ የደረሰው ውድመት በገንዘብ ሲተመን በአጠቃላይ 80 ቢልዮን ዶላር እንደሚገመት የገለፁት አቶ ጌታቸው ረዳ ይሁንና ይህ የሚያካክስ ድጎሞ እየተደረገ እንዳልሆነ ተናግረዋል። በዚህና ሌሎች ምክንያቶችም የክልሉ አስተዳደር ለበጀት ክፍተት ተዳርጎ እንዳለ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ ሰላማዊ ሕይወት መልሶ የማቋቋም ተግባራት አለመከናወናቸው ተከትሎ፥ በክልሉ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮ እንዳለም ጠቁመዋል። አቶ ጌታቸው "ከ270 ሺህ በላይ ሰራዊት አለን። ይህ ሰራዊት ወደ ኑሮው ሊመለስ ከሆነ፥ ለዚህ የሚመጥን በጀት ሊኖር ይገባል። ይህ እስኪሆን ረዥም ግዜ ስለሚወስድ በካምፖች ሆኖ ስንቅ ሊቀርብለት ፌደራል መንግስት ሐላፊነት አለው። በተወሰነ ደረጃ የአንድ ወር ነው ይመስለኛል መንቀሳቀስ ጀምረው እንደነበር አውቃለሁ። ከዛ በኃላ ግን ይህ ለትግራይ ህልውና መስዋዕት የከፈለ ሰራዊት የፕሪቶርያው ውል በምሉእነት ሳይተገበር ተበተን የምንልበት ምክንያት ስለሌለ፥ ካለው እየቀነስን የሰራዊት መዋጮ የምናወጣበት ሁኔታ አለ" ብለዋል።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
እሸቴ በቀለ