1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«የሰላም ስምምነቱ በምልዓት ገቢራዊ አልሆነም »ህወሓት

ማክሰኞ፣ መስከረም 15 2016

የሰላም ስምምነት የተፈራረመው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለአንድ ሳምንት አደረግኩት ካለው የማእከላይ ኮሚቴ ስብሰባ በኃላ ትላንት ባወጣው መግለጫ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በሙሉእነት እየተተገበረ እንዳልሆነ ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4Wpio
Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

ህወሓት፣ አሳሳቢ አስተዳደራዊ ችግሮች አሉብኝ አለ

የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አምና ጥቅምት ፕሪቶሪያ-ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ የተፈራረሙት ግጭት የማቆም ስምምነት በሙሉዕነት ገቢርዊ አልሆነም በማለት ሕወሓት አስታወቀ።ለሳምንት ከቆየ ስብሰባ በኃላ ትላንት ማታ መግለጫ ያወጣው ህወሓት ውሉ ሙሉ በሙሉ ባለመተግበሩ የትግራይ ህዝብ ችግሮች መቀጠላቸዉን አስታዉቋል።ሕወሓት አክሎ እንዳለዉ ለፕሪቶርያው ስምምነት ተግባራዊነት ከፌደራሉ መንግስት ጋር ውይይት እንደሚያስፈልግ አመልክቷል። ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ውስጥ አሳሳቢ አስተዳደራዊ ችግሮች እየታዩ መሆኑም ህወሓት ገልጿል።«የትግራይ ነፃነት ፓርቲ» በህወሓት ላይ ያቀረበው ክስ
ከፌደራል መንግስቱ ጋር ለሁለት ዓመታት ከቆየ ጦርነት በኃላ የሰላም ስምምነት የተፈራረመው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለአንድ ሳምንት አደረግኩት ካለው የማእከላይ ኮሚቴ ስብሰባ በኃላ ትላንት ባወጣው መግለጫ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በሙሉእነት እየተተገበረ እንዳልሆነ ገልጿል። ከጦርነቱ በኃላ በተደረሰ የሰላም ስምምነት ህዝባችን አንፃራዊ ሰላም ከማግኘቱ በተጨማሪ ተቋርጠው የነበሩ የህዝብ አገልግሎቶች ቀጥለዋል ያለው የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ ይሁንና የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እንደሚጠበቀው ሙሉበሙሉ ባለመተግበሩ አሁንም ህዝባችን ከፊሉ በመጠልያ ጣብያዎች፣ ሌላው በስደት፣ ነፃ ባልወጡ አካባቢዎች እና ሌሎች ተበታትኖ እየኖረ ነው ሲል አሁንም በትግራይ አስከፊ የዜጎች ሕይወት እየቀጠለ ስለመሆኑ አመልክቷል። በዚህም ምክንያት ከሰላም ስምምነቱ በኃላ ጭምር በትግራይ ህዝብ ላይ ብሔር ተኮር ጥቃት፣ ዝርፍያና የተለያዩ ማሕበራዊ ችግሮች እየተጋለጠ ነው ብሏል ህወሓት። ይህ ለመፍታት ደግሞ ስምምነቱ በሙሉእነት እንዲተገበር ከፌደራሉ መንግስት ጋር ፖለቲካዊ ውይይት ማድረግ ይገባል ብሏል።

ህወሓት አስተዳደራዊ አሳሳቢ ድክመት እንዳለበት አምኗል
ህወሓት መራሹ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ካቢኔምስል Million Hailesilassie/DW

ከዚህ በተጨማሪ በውስጣዊ ጉዳዮች ዙርያ ማብራርያ የሰጠው የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ መግለጫ በአስተዳደር፣ ሰላም፣ ድህንነት እና ፍትህ ጉዳዮች ውስጣችን ባለ የመሪነት እና አስተዳደራዊ ችግሮች በመጥፎ ሁኔታ ላይ እንገኛለን ሲል ገልጿል።ሕወሃት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ ተቃወመ

በህወሓት እና በክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር መካከል አለመግባባቶች መኖራቸው በትግራይ ፖለቲከኞች በተደጋጋሚ የሚነሳ ቢሆንም የትላንቱ የህወሓት መግለጫ በዚህ ጉዳይ ያለው ነገር የለም። ይሁንና በትግራይ ካለው የአስተዳደር ችግሮች ጋር በተገኛኘ በቅርቡ ማብራርያ የሰጡት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት እና የህወሓት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ የግዚያዊ አስተዳደር ስራ በማደናቀፍ ከመንግስት ውጭ ያሉ ያሏቸው ሌሎች አካላት ተጠያቂ ሲያደርጉ ተደምጠዋል።  አቶ ጌታቸው "በተቀናጀ መንገድ ወረዳዎች ራሳቸው እንደ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አካል አድርገው እንዳይቆጥሩ ለማድረግ የሚደረግ እንቅስቃሴ መኖሩ የሚያጠራጥር ነገር የለዉም። በግል የምናየው ነገር ነው። በቅርቡ የጥናት ቡድን ልከን ነበር። በመቐለ ክፍለ ከተሞች ለምን የግዚያዊ አስተዳደር ማሕተም እንደማይጠቀሙ ሲነሳ፣ እኛ የግዚያዊ አስተዳደሩ አካል አይደለንም የሚል ምክንያት ነው የሚሰጠው። ይህ ድንገት የፈጠሩት ሳይሆን፥ ይህ እንዲሆን የሚሰራ አካል መኖሩ የሚገመት ነው። በአስተዳደሩ ያለ ድክመት እንዳለ ሆኖ በመንግስት ውስጥ የሌሉ ስዎች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ግን መገመት ብቻ ሳይሆን በተግባርም አለ" ብለዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አዲስ ካቢኔ

በህወሓት መሪነት የትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ ሆንዋል የሚለው በትግራይ በተቃዋሚነት የሚንቀሳቀሰው ዓረና ትግራይ በበኩሉ በፕሪቶርያው ውል አፈፃፀም መጓደል እየታዩ መሆናቸው በህወሓት በኩል መገለፁ እንደ አቋም ይመራዋል። የዓረናው ሊቀመንበር አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ "በተገባው ውል መሰረት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት በሙሉእነት መተግበር አለበት" ይላሉ።

ከግራ ወደቀኝ ማርሻል ብርሐኑ ጁላ የኢትዮጵያ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የትግራይ ኃይል አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ
የፕሪቶሪያዉን የሰላም ስምምነት ገቢር ለማድረግ ናይሮቢ ላይ የተፈረመዉ ስምምነትምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

ህወሓት በበላይነት የሚቆጣጠረው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ተገቢው ተግባሩ እየፈፀመ አለመሆኑ በማንሳት የሚወቀሱት ደግሞ ሌላው ፓለቲከኞ አቶ ኪዳነ አመነ ናቸው። አቶ ኪዳነ "ብረታብረት የሰረቀ፣ ወርቅ የሰረቀ፣ እርዳታ የሰረቀ ለሕግ ይቅረብ። በትግራይ የሕግ የበላይነት ይረጋገጥ። ሌላ በትግራይ የሰላም እና ድህንነት ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ወጥቶ በሰላም መግባት አልተቻለም። ከፍተኛ የድህንነት ስጋት አለ። የዜጎች በሰላም የመኖር መብት ይከበር፥ መንግስት ከሆነ ይህ ያረጋግጥ ነው እያልን ያለነው" ይላሉ።

ትናንት ማታ በህወሓት በኩል ስለወጣው የጽሑፍ መግለጫ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር