1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትን ገንዘብ ወደ አቋማሪ ድርጅቶች ያዛወሩ ተማሪዎች አጣብቂኝ

Eshete Bekele
ዓርብ፣ መጋቢት 20 2016

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕክል በገጠመው ወቅት ገንዘብ ያዘዋወሩ ደንበኞቹ የወሰዱትን እንዲመልሱ የሰጠው ቀነ-ገደብ ቅዳሜ ይጠናቀቃል። የወሰዱትን ገንዘብ ወደ አቋማሪ ድርጅቶች ያዘዋወሩ ተማሪዎች በተሰጣቸው ቀነ-ገደብ መመለስ ባለመቻላቸው ሥጋት ውስጥ ገብተዋል። በቴሌ-ብር ወደ አቋማሪ ድርጅቶች የተላለፈውን ገንዘብ ንግድ ባንክ እንዲያስመልስ ይሻሉ።

https://p.dw.com/p/4eGDO
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕክል በገጠመው ወቅት ገንዘብ ያዘዋወሩ ደንበኞቹ እስከ መጋቢት 21 ቀን 2016 እንዲመልሱ ቀነ ገደብ ሰጥቷል።ምስል Eshete Bekele/DW

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትን ገንዘብ ወደ አቋማሪ ድርጅቶች ያዛወሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወሰዱትን ገንዘብ ወደ አቋማሪ ድርጅቶች ያዘዋወሩ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ መሠረት መመለስ ባለመቻላቸው አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። ተማሪዎቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቴሌ ብር አማካኝነት በአቋማሪ ድርጅቶች በከፈቱት አካውንት ያስገቡት ገንዘብ የት እንደገባ ማወቅ ተስኗቸዋል። 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ግብይት ሲፈጸም የሚፈጠረውን መስተጓጎል ለማረቅ መጋቢት 06 ቀን፤ 2016 ተግባራዊ ባደረገው ማሻሻያ ምክንያት በተፈጠረው ዕክል 801 ሚሊዮን ብር ገደማ ዝውውር እንደተፈጸመ ፕሬዝዳንቱ አቶ አቤ ሳኖ ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ከዚህ የገንዘብ መጠን ውስጥ 622.9 ሚሊዮን ብር ተመልሷል። 

በባንኩ መረጃ መሠረት ዕክሉ በተከሰተበት ዕለት ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ38 እስከ 8 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ባሉት አምስት ገደማ ሰዓታት በ25 ሺሕ 761 የባንክ ሒሳቦች 238 ሺሕ 293 ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተፈጽሟል። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት የገንዘብ ዝውውሩን ከፈጸሙት መካከል 57 በመቶው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ናቸው። 

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ሕገ-ወጥ” የተባለውን የገንዘብ ዝውውር ካከናወኑ ተማሪዎች አንዱ የሆነው አልበርት ተፈራ 10 ሺሕ ብር ለባንኩ መመለስ አለበት። የ24 ዓመቱ ተመራቂ ተማሪ በወቅቱ ከባንኩ “በስህተት” ካዘዋወረው 148 ሺሕ ብር ውስጥ 10 ሺሕ ብር ቫሞስ በተባለ አቋማሪ ድርጅት በከፈተው አካውንት ማስገባቱን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። ንግድ ባንክ በአካውንቱ ውስጥ የነበረውን ገንዘብ መውሰዱን የገለጸው አልበርት ቫሞስ ወደተባለው አቋማሪ ድርጅት የተላለፈው በአንጻሩ “ኔጌቲቭ” ሆኖ መቀመጡን አስረድቷል።

 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀውስ ለባንኮች የማንቂያ ደወል ይሆን?

ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚመለስ 141 ሺሕ ብር ያለበት ሌላ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የአምስተኛ ዓመት ተማሪ ሁሉ ስፖርት እና ቫሞስ ወደተባሉት ሁለት አቋማሪ ድርጅቶች 81 ሺሕ ብር ገደማ እንዳዘዋወረ ተናግሯል። የንግድ ባንክ ዕክል በተፈጠረበት ወቅት 16 ሺሕ 380 ብር ያዘዋወረው ይበልጣል በዓሉ በሦስት አቋማሪ ድርጅቶች በሚገኙ አካውንቶቹ ገንዘብ እንዳስቀመጠ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጋቢት 6 ቀን 2016 በገጠመው ዕክል 801 ሚሊዮን ብር ገደማ መዘዋወሩን ፕሬዝደንቱ አቶ አቤ ሳኖ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተወሰደውን ገንዘብ ለማስመለስ እርምጃ መውሰድ ከጀመረ በኋላ ተማሪዎቹ በባንኩ የሚገኝ ሒሳባቸው “ኔጌቲቭ” መሆኑ ተገልጾላቸዋል። ወደ አቋማሪ ድርጅቶች ያዘዋወሩት ገንዘብ በአካውንታቸው የማይገኝ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተመልሶ ያለባቸውን ዕዳ እንዳላስተካከለ ተረድተዋል። 

“ቫሞስ ላይ ያስቀመጥኩት 14 ሺሕ ብር እንደገባ ብዙም አልቆየም ሲነሳ። ቫሞስ አካውንት ላይ ኔጌቲቭ ብሎ ነው ያስቀመጠው። ወደ ንግድ ባንክ ከተመለሰ ኔጌቴቩን ማጥፋት ነበረበት” ሲሉ ይበልጣል ይናገራል።

 የንግድ ባንክ ገንዘብና ተማሪዎች

ገንዘቡ ቫሞስ በተባለው አቋማሪ ድርጅት አካውንት ለአጭር ጊዜ ብቻ እንደቆየ የሚናገረው ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ተማሪ የተቋሙን ባልደረቦች ስልክ በመደወል ሲጠይቁ አንዴ “ብሔራዊ ባንክ አግዶናል” ሌላ ጊዜ ደግሞ “ንግድ ባንክ አካውንታችንን አግዶብናል” የሚል መልስ እንደሰጡ ይናገራል። 

ተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ የገጠመው ይበልጣል “ከንግድ ባንክ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ስለሆነ እየተጣራ ነው ጠብቁ የሚሉ አሉ። አንዳንዶች ደግሞ ገንዘቡን ለንግድ ባንክ በጥሬ ከከፈላችሁ በኋላ ‘ንግድ ባንክ ከፍለውኛል’ የሚል ምላሽ ሲሰጥ ገንዘቡ ወደ ቫሞስ አካውንት ይለቀቃል” የሚል መልስ እንደተሰጠው ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

ዶይቼ ቬለ ቫሞስ ከተባለው ድርጅት ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረጋቸው የስልክ ጥሪዎች አልተነሱም። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ቅጥር ግቢ በሕገ-ወጥ መንገድ ገንዘብ ወስደዋል ያላቸውን ደንበኞች ሥም፣ የሒሳብ ቁጥር እና ምን ያክል ዕዳ እንዳለባቸው የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ለጥፏል። በዚህ ማስጠንቀቂያ ባንኩ ገንዘብ የማይመልሱ ደንበኞቹ ላይ “የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔር እና የአስተዳደር እርምጃዎች እንዲወሰዱ” ሊያደርግ እንደሚችል ገልጿል። 

 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕክል በገጠመው ወቅት ያዘዋወሩትን ገንዘብ ያልመለሱ ደንበኞች ዝርዝር
በአርባ ምንጭ ዋና ግቢ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕክል በገጠመው ወቅት ያዘዋወሩትን ገንዘብ ያልመለሱ ደንበኞች ዝርዝር ተለጥፏልምስል Private

“ጥናት አቁመናል። እያነበብን አይደለም” የሚለው ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ተማሪ የፖሊስ ተሽከርካሪ በቅጥር ግቢው ሲመለከቱ ፍርሐት እየፈጠረባቸው እንደሚገኝ ይናገራል። ተመሳሳይ ሥጋት ውስጥ እንደሚገኝ የሚናገረው አልበርት በበኩሉ “ተማሪ አንድ ቀን ቢታሰር የአንድ ቀን ትምህርት ያመልጠዋል፤ ሁለት ቀን ቢታሰር የሁለት ቀን ትምህርት ያመልጠዋል። ሦስት አራት ቀን ከሆነ ሙሉውን መንፈቀ-ዓመት ወይም የዓመቱን ትምህርት ያቆማል” በማለት ሊፈጠር የሚችለውን ችግር አብራርቷል።

ትምህርት ለመማር እየተማፀኑ ያሉ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች

በቅጥር ግቢው የተለጠፈውን ማስጠንቀቂያ ከተመለከተ በኋላ በቅጡ ሳያጠና ለፈተና ለመቀመጥ እንደተገደደ የሚናገረው ይበልጣል “ነገሩ በጣም ነው የሚያጨናንቀው፤ ዛሬ ነው የምንታሰረው? ነገ ነው የምንታሰረው? ለቤተሰብስ ደውለን እንዴት ነው ገንዘብ ክፈሉ የምንለው?” እያለ የተሰማውን ሥጋት እና የገባበትን አጣብቂኝ ይገልጻል። 

“እኛን ሌቦች ናቸው ብለው ቢያስወሩብን፤ የእኛን ሕይወት ከማበላሸት ወይም የእኛን ሞራል ከመግደል ውጪ ለኢትዮጵያም ለሕዝባችንም የሚጠቅመው ነገር የለም” የሚለው ስሙ እንዳይገለጽ የፈለገ ተማሪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያስቀመጠውን ቀነ ገደብ እንዲያራዝም ይፈልጋል። ገንዘቡ ወደ አቋማሪ ድርጅቶች የተላለፈው በቴሌ-ብር ብር አማካኝነት እንደሆነ የሚናገረው አልበርት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀጥታ ከአካውንቶቹ ተመላሽ የሚያደርግበትን መንገድ እንዲፈልግ ይጠይቃል።

ሦስቱ ተመራቂ ተማሪዎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጀመሪያ ባስተላለፈው ጥሪ መሠረት ገንዘቡ ወዴት እንደተዘዋወረ የሚገልጽ ሠነድ መሙላታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ይበልጣል በበኩሉ “የእኛ ብቻ ስህተት ብቻ ሳይሆን የእነሱም ስህተት አለበት። የሁላችንም ስህተት ነው። ስህተታችንን አብረን ማለፍ አለብን” የሚል ጥሪ አቅርቧል። 

እሸቴ በቀለ 
ማንተጋፍቶት ስለሺ