1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀውስ ለባንኮች የማንቂያ ደወል ይሆን?

ረቡዕ፣ መጋቢት 11 2016

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የገጠመው ዕክል ለተወሰኑ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አጭር ፌሽታ ቢፈጥርም በባለሙያዎች ዘንድ ጥያቄ አጭሯል። የባንኩ አገልግሎቶች በሙሉ እንዲዘጉ ያስገደደው ክስተት አንድ ተማሪ 180 የገንዘብ ዝውውር እንዲያደርግ ፈቅዷል። ችግር የፈጠረው ማሻሻያ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ከነባሩ ሥርዓት ጋር መጣጣም ስለመቻሉ መፈተሽ ነበረበት።

https://p.dw.com/p/4dwfF
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ ከወሰዱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የመለሱ እንዲሁም የታሰሩ መኖራቸውን ዶይቼ ቬለ መረዳት ችሏል። ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀውስ ለባንኮች የማንቂያ ደወል ይሆን?

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞቹ በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የራሳቸው ያልሆነ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያወጡ ወይም እንዲያዘዋውሩ ቀዳዳ የከፈተውን ክስተት በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ቢያስቆምም ኩነቱ የዘርፉን ባለሙያዎች ሥጋት ውስጥ ጥሏል።

“ለአንድ ቀን ቢቆይ ኖሮ ምንአልባት ንግድ ባንክን ለከባድ ጦስ ሊዳርግ የሚችል ክስተት ነበረ” የሚሉት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ “የባንክ ዘርፉ ከኮምፒውተር ጋር በተያያዘ ምን ያህል ለአደጋ የተጋለጠ እንደሆነ” የጠቆመ እንደሆነ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

ዶክተር አብዱልመናንን የመሳሰሉ የባንክ ባለሙያዎች የተሰማቸው ሥጋት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገበያው ካለው ግዙፍ ድርሻ እና የሀገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ረገድ ምን ያክል ዝግጁ ናቸው? ከሚለው ጥያቄ የሚመነጭ ነው። ከ82 ዓመታት በፊት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በገበያው ከ50 በመቶ በላይ ድርሻ ያለው ግዙፍ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲሱ በዋጋ ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ምን ይፈልጋል?

ከጥቂት ጊዜያት በፊት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገልግሎቶች ተቋርጠው እንደነበር የሚያስታውሱት የሕግ ባለሙያው አቶ ሐብታሙ ኃይለመስቀል የተፈጠረው ክስተት “አሳሳቢ” ሆኖባቸዋል። ሀገሪቱ ከጥሬ ገንዘብ ይልቅ ወደ ዲጂታል ክፍያ ለመሸጋገር ለጀመረችው ጥረት “በከፍተኛ ደረጃ ባንክን የሚያምን ኅብረተሰብ የግድ ያስፈልጋል” የሚሉት አቶ ሐብታሙ በገበያው ከፍተኛ ድርሻ ባለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ “በቀናት ልዩነት ሁለት ጊዜ እንደዚህ አይነት ነገር መፈጠሩ፤ ሰዎች በባንክ ካላቸው ገንዘብ በላይ እንዲያንቀሳቅሱ መሆኑ ተጠቃሚዎች ላይ ትልቅ ስነ ልቦናዊ ጫና የሚያመጣ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች ያሻቸውን ገንዘብ ከኤቲኤም ማሽኖች እንዲያወጡ አሊያም ወደ ሌላ እንዲያዘዋውሩ ቀዳዳ የከፈተው ማሻሻያ ተግባራዊ የሆነው አርብ መጋቢት 06 ቀን 2016 ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ነው። የማሻሻያው ዓላማ የዲጂታል ግብይት ሲፈጸም የሚፈጠረውን መስተጓጎል ማረቅ እንደነበር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝደንት አቶ አቤ ሳኖ ተናግረዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ
የአዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ዲላ እና ሐዋሳን ጨምሮ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተግባራዊ ባደረገው ማሻሻያ የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅመው ገንዘብ አውጥተዋል አሊያም አዘዋውረዋል የተባሉ ተማሪዎች እንዲመልሱ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

ተግባራዊ በተደረገው ማሻሻያ ምክንያት “ያልተገባ የግብይት ሒደት” መከናወኑን ከዲስትሪክት ቢሮዎች ለዋናው መሥሪያ ቤት ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ ሪፖርት ከተደረገ በኋላ “አንዳንድ የተጠረጠሩ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ” ተደርጓል። የባንኩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኃላፊዎች የወሰዱት ርምጃ “ችግሩን ሙሉ በሙሉ” ስላልፈታ ከማለዳው 11:30 አካባቢ ሁሉም ዲጂታል አገልግሎቶች እንዲቆሙ መደረጉን ንግድ ባንክ አስታውቋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቅርንጫፎች የሚያቀርበው አገልግሎት የቆመው ቅዳሜ መጋቢት 07 ቀን 2016 ጠዋት ነው።

የሶፍትዌር ጥራት ቁጥጥር ምኅንድስና ባለሙያው አቶ አረፋት መሐመድ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማሻሻያውን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት ከነባሩ ሥርዓት ጋር መጣጣሙን በሙከራ መፈተሽ እንደነበረበት ይናገራሉ። “የሳይበር ጥቃት በጣም የተወሳሰበ ነው” የሚሉት አቶ አረፋት ”ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ክፍተቶች ከውስጥ ከተፈጠሩ ለጥቃት በጣም ቀላል ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ባንኮች የሚጠቀሙበት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ-ልማት “ደሕነቱ የተረጋገጠ፣ የገንዘብ ዝውውርን ሚስጥራዊነት ማስጠበቅ እና ሲስተሙ እንደሚሠራ ማረጋገጥ የሚችል” ሊሆን እንደሚገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ያዛል። ይኸ መመሪያ ሥራ ላይ የዋለው በጎርጎሮሳዊው 2022 ነው።

መመሪያው ባንኮች የሚጠቀሙበት ቴክኖሎጂ “ወደ ኋላ ተመልሶ እነ ማን ምን አደረጉ የሚለውን ሊያረጋግጥ የሚችል” እና በኢንሳ እውቅና የተሰጠው ሊሆን እንደሚገባ እንደሚያዝ የገለጹት የሕግ ባለሙያው አቶ ሐብታሙ “እንደዚህ አይነት የሳይበር ክስተቶች በሚከሰቱበት ጊዜ መጠባበቂያ የሚሆን ባክአፕ ሴንተር ሁሉ ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚያመለክት” መሆኑን አስረድተዋል።  

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ምን ያክል ያንን መመሪያ” ሥራ ላይ እንዳዋለ በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል የገለጹት አቶ ሐብታሙ “ነገር ግን መመሪያውን እየተከተሉ የሚሰሩ ከሆነ እንደዚህ አይነት ችግር ያጋጥማል የሚል እምነት የለኝም” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት
ምስል Eshete Bekele/DW

አርብ መጋቢት 06 ቀን 2016 በተፈጠረው ክፍተት 66 ሺሕ ገደማ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞች 2.4 ቢሊዮን ብር ማዘዋወራቸውን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል። በወቅቱ ከ490 ሺሕ በላይ “ጤነኛ እና ችግር ያለባቸው” የገንዘብ ዝውውሮች መደረጋቸውን የገለጹት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝደንት አቶ አቤ ሳኖ የደረሰው ጉዳት እስከዚህ ሣምንት መጨረሻ ይታወቃል ተብሎ እንደሚታመን ባለፈው ሰኞ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

አብዛኛውን የገንዘብ ዝውውር ፈጽመዋል የተባሉት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የወሰዱትን እንዲመልሱ ጠበቅ ያለ ትዕዛዝ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተሰጥቷቸዋል። “ለዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር እየሰጠን ሥማቸው እየተለጠፈ ሲያዩ እየመለሱ ነው” ያሉት አቶ አቤ ሳኖ “አሁንም እንዲመልሱ ነው የምንፈልገው። ከመለሱ ወደ ክስ አንሔድም። የማይመልሱ ከሆነ የሕግ እርምጃ እንወስዳለን” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

“አፍሪካ የሚወነጨፍ ዕድገት ያስፈልጋታል” የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት አኪንዉሚ አዲሺና

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የጅማ እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በየትምህርት ተቋማቾቻቸው በተለጠፉ ማስጠንቀቂያዎች መሠረት ወጪ ያደረጉትን ገንዘብ የመለሱ መኖራቸውን ተናግረዋል። አዲስ አበባ፣ ጅማ፣ ድሬዳዋ፣ ሐዋሳ እና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች የማይገባቸውን ገንዘብ አውጥተዋል ለተባሉ ተማሪዎች እንዲመልሱ አሊያም በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሔድ ሪፖርት እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ከሰጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ናቸው።

ገንዘብ አውጥተዋል ከተባሉ ተማሪዎች መካከል በቁጥጥር ሥር የዋሉ መኖራቸውን ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል። ስማቸው እና የስልክ ቁጥሮቻቸው በከፍተኛ ዩኒቨርሲቲዎች ከተለጠፈ መካከል ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የተወሰኑ ተማሪዎች “ምንም አይነት ገንዘብ አልወሰድንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የሕግ ባለሙያው አቶ ሐብታሙ ጊዜ እና ገንዘብ የሚጠይቅ ቢሆንም “ከሚገባቸው በላይ ምን ያህል አወጡ? የሚለውን ለመለየት የሚያስችል ሥርዓት ካለው ገንዘቡን ለማስመለስ ጊዜ ይወስድ ይሆናል እንጂ ይቸገራል ብዬ አላስብም” ሲሉ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሎጎ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጉዳዩ ላይ “አስፈላጊውን ምርመራ” በማድረግ ወደፊት ለሕብረተሰቡ እንደሚያሳውቅ ቃል ገብቷል።ምስል Eshete Bekele/DW

አቶ አቤ ሳኖ በዕለቱ የነበረው ግብይት አጠቃላይ ቢደመር “ገንዘቡ ትንሽ” ነው ሲሉ በባንኩ ላይ የደረሰው ጉዳት ብርቱ እንደማይሆን ገልጸዋል። የተፈጠረውን ኩነት ግን ፕሬዝደንቱ “አሳማሚ” ብለውታል።

ዶክተር አብዱልመናን ግን ባንኩ የበረታ ችግር ቢገጥመው በሀገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ያሳስባቸዋል። “ከገንዘብ መበደር እና ማስቀመጥ ባሻገር የሀገሪቱ ኤኮኖሚ የክፍያ ሥርዓት ባንክ ላይ ጥገኛ ነው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን ግዙፉ ንግድ ባንክ “በሳይበር ጥቃትም ይሁን በሌላ በሥርዓት ችግር” ብርቱ ዕክል ቢገጥመው “የሀገሪቱ ኤኮኖሚ ቀጥ” ሊል እንደሚችል ይሰጋሉ።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከዕቃዎች የወጪ ንግድ ያገኘችው የውጭ ምንዛሪ ነዳጅ ከገዛችበት ያነሰ ነው

የኢትጵያ ንግድ ባንክ “በብዙ ሺሕዎች” የሚቆጠሩ ጥቃቶች ከሚፈጸምባቸው ተቋማት አንዱ እንደሆነ ፕሬዝደንቱ አቶ አቤ ሳኖ ተናግረዋል። “state sponsored ጥቃቶች በብዛት ይደረጋሉ” ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝደንት “እስካሁን እነዚህ ጥቃቶች አንዳቸውም የእኛን የcyber security በጥሰው መግባት የቻለ የለም” ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተከሰተው ችግር ሌሎች የሀገሪቱ መሰል ተቋማት የሚጠቀሙበትን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ-ልማት የበለጠ እንዲያጠናክሩ መልዕክት ያስተላለፈ ነው። የኢትዮጵያን ባንኮች በቅርብ የሚያውቁት አቶ አረፋት ተቋማቱ ጠንከር ላለ የሳይበር ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል ቁመና አላቸው ብሎ ለማመን ይቸግራቸዋል።

“በትክክል ጥቃት ቢፈጸምባቸው፤ በትክክል ባለሙያዎች ቢፈትሹት የእኛ ሀገር ባንኮች ይኸን ነገር ለመቋቋም ያላቸው ዝግጁነት ያሳስበኛል” ያሉት አቶ አረፋት ዝግጅታቸው “አነስተኛ” እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጉዳዩ ላይ “አስፈላጊውን ምርመራ” በማድረግ ወደፊት ለሕብረተሰቡ እንደሚያሳውቅ ቃል ገብቷል። ባንኩ “በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የሚገኙ የፋይናንስ ሥርዓቶች ደሕንነታቸው የተጠበቀ” እንደሆነ ገልጿል።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ