1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ እና አፋር ክልሎች ከስምምነቱ በኋላ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 22 2016

ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ ለሁለት ዓመታ በቆየው ጦርነት ክፉኛ ከወደሙ ክልሎች የአማራ እና የአፋር ክልሎች ይገኙበታል፡፡በነዚህ ሁለት ክልሎች የደረሰው ሰብዓዊና የንብረት ውድመት እስካሁንም ሙሉ በሙሉ አልተጠገነም።የፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነቱን ቢያስቆምም የሕዝቡንና የክልሎቹን ጉዳት ለዘላቂዉ ለማቃለል ግን ብዙ የተከረዉ የለም የሚሉ አሉ።

https://p.dw.com/p/4YKii
በአማራ ክልል የቀጠለዉ ጦርነት
በአማራ ክልል የቀጠለዉ ጦርነት ምስል AP/picture alliance

«የፕሪቶርያዉ ስምምነት ግልጽነትና አካታችነት ያልነበረው» አስተያየት ሰጭ

“አንደኛው በአከባቢው ማህበረሰቡ በስነልቦናም በጦርነቱ ክፉኛ ተጎድቷል፡፡ አሁንም የእርሰበርስ ግጭቱ በመሃል ሰውን ወደነበረው አለመረጋጋት ከተተው እንጂ ሰው ከዚያ ጦርነት ስነልቦና እያገገመ ነበር፡፡ ያው እንደምናውቀውም ጦርነት ለአጭር ጊዜ ብደረግም ጉዳቱ በቀላሉ ሚሽር አይደለም፡፡”
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ ላይ ነዋሪነታቸውን ያደረጉ አስተያየት ሰጪ የዛሬ ሁለት ዓመታት ገደማ አከባቢያቸውን ስላወደመው የተስፋፋው የትግራዩ ጦርነትን በተመለከተ የሰጡን አስተያየት ነበር፡፡ በአከባቢው በመምህርነት ሙያ የሚተዳደሩትና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት ነዋሪው፤ ከጦርነቱ ማግስት ልክ የዛሬ ዓመት የትግራይ ጦርነትን ያበቃው ስምምነት መፈረሙ ይበል ቢያሰኝም፤ ያንኑን ጦርነት ተክቶ በአማራ ክልል የተከሰተው ሌላኛው አለመረጋጋት ለህብረተሰቡ ራስምታት ሆኗልም ባይ ናቸው፡፡ አስተያየት ሰጪው በጦርነቱ ክፉኛ የወደሙ መሰረተልማቶች ጠባሳን ለመጠገን ጥረት ብደረግም አሁንም ግን ገና የሚቀሩ ሰፊ ክፍተቶች አሉ ብለዋል፡፡ “በተለይም በኮምቦልቻ አኒደስትሪዎች ላይ የደረሰውን ውድመት ተከትሎ በትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ የተሰሩ በርካታ ስራዎች ብኖሩም አሁንም ግን ነገሮች ወደ መደበኛ ሁኔታ ተመለሱ የሚስብል አይደለም፡፡”የዓረና ትግራይ ለጦርነቱ ውጤት ወቀሳ
አንድ ዓመት የደፈነው የፕሪቶሪያው ስምምነት በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ ተጨማሪ ውድመት እንዳይከሰት አስተዋጽኦ ማድረጉ አይታበልም የሚሉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ፍልስፍና ረዳት ፕሮፈሰርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናቶች የሶስተኛ ድግሪ ተማሪ ሲሳይ አሳምሬ ስምምነቱ ግልጽነትና አካታችነት ግን ያልነበረው በሚል አጣጥለውታል፡፡  “መንግስት እና ህወሓት ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ ሄደው ጦርነትን ለማቆም ያደረጉት ስምምነት ባንድ በኩል ጦርነትን ያቆመ ሆኖ በሌላ በኩል ጦርነትን የቀሰቀሰ በመሆኑ ስምምነቱ ያመጣው በጎ ጎን እንዳለው ሁሉ ለሌላ ጦርነትም ድግስ የደገሰ ሆኗል፡፡ ስምምነቱ ሲካሄድ አካታች መሆን ነበረበት፡፡ ከፌዴራል መንግስት ሌላ በጦርነቱ ቀጥታ የተሳተፉና በተለየ መንገድ ክፉኛ የወደሙ አማራ ክልል እና አፋር ክልል ብሎም ከፌዴራል መንግስት ባልተናነሰ መልኩ የተሳተፈው የኤርትራ መንግስት ተሳታፊ መሆን ነበረባቸው፡፡”የትግራይ ሲቪክ ማኅበራት ጥሪ
ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አማራ እና አፋር ክልሎችን ብሎም የኤርትራ መንግስትን በጦርነቱ አሳትፎ ከፌዴራል መንግስት ጎን ያሰለፈውም ፌዴራል መንግስቱ ለጦርነቱ መከፈት ካቀረበው ምክኒያት የሚሻገር ነው ይላሉ፡፡ “እነዚህ የትግራይ አጎራባች ክልሎች እና ኤርትራ ከህወሓት ጋር የሚያወዛግባቸው የግዛት ጥያቄዎች እንደ ተቀበረ ቦምብ ጊዜውን የሚጠብቁ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ በዚያም ነው ቀጥታ ህወሓትን ከፌዴራል መንግስት ጎን ሆነው የተፋለሙት፡፡ የፕሪቶሪያው ስምምነት ግን የአሰላለፍ ለውጥ እንጂ ዘላቂ የሰላም ምፍትሄን ያመጣ አይመስልም፡፡”
በሰሜን ኢትዮጵያው የሁለት ዓመታት አስከፊ ጦርነት ክፉኛ ከተጎዱ ክልሎች ሌላኛው የአፋር ክልል ነው፡፡ በክልሉ በተስፋፋው ጦርነት በርካቶች ተፈናቅለው ብዙ ህይወት መስዋእት ሆኗል መሰረተ ልማቶችም ወድመዋል፡፡ የአፋር ህዝብ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ኃላፊው አቶ ገዓዝ አህመድ ግን ትልቁ የስምምነቱ ትሩፋት ሞት እንዲገታ ማድረጉ ነው ይላሉ፡፡ “ሞት እንዲያበቃ የቆመው ጦርነት ትልቅ እምርታ ተደርጎ የሚነሳ ነው፡፡ መሰረተ ልማቶችን የመልሶ ማቋቋም ስራ ግን አሁንም አርኪ አይደለም፡፡”  
አቶ ገዓዝ ከስምምነቱ ማግስት አሁንም የቀጠሉ የጦርነት ማግስት ጉዳቶች መኖራቸውንም አክለው ያነሱታል፡፡ “እስካሁን ወደ መጠለያቸው ይልተመለሱ ወረዳዎች አሉ፡፡ የአፋር ሰሜናዊ ዞንና ጭፍራ ወረዳ በጦርነቱ ክፉኛ ወድሟል፡፡ አሁንም ድረስ በተቀበሩ ቦምቦች በህጻናት ላይ ጉዳት ሚደርስበት አከባቢም አለ፡፡” 

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ