1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዩጋንዳ የዜጎቿን ሕይወት ከቀጠፈ የቆሻሻ ክምር መደርመስ አደጋ በኋላ ኃይለኛ ጥያቄ ተጋፍጣለች

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 18 2016

ዩጋንዳ እንደ ኢትዮጵያ ኃይለኛ የቆሻሻ ክምር ተንዶ የ35 ዜጎቿን ሕይወት ተነጥቃለች። ከአደጋው በኋላ የሀገሪቱ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ጥያቄ ተነስቶበታል። የፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ መንግሥት ከአራት ዓመታት በፊት ብሔራዊ የቆሻሻ አወጋገድ ዕቅድ ይፋ ቢያደርግም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ተግባራዊነቱ እጅግ ዘግይቷል።

https://p.dw.com/p/4jrm0
በዩጋንዳ የተደረመሰ የቆሻሻ ማስወገጃ
በዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ አቅራቢያ በሚገኘው ኪቴዚ የቆሻሻ ማስወገጃ በደረሰው አደጋ ቢያንስ 35 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ምስል Hajarah Nalwadda/Xinhua/IMAGO

ዩጋንዳ የዜጎቿን ሕይወት ከቀጠፈ የቆሻሻ ክምር መደርመስ አደጋ በኋላ ኃይለኛ ጥያቄ ተጋፍጣለች

ግዙፍ ኤክስካቫተሮች የቆሻሻ ክምር ከአንዱ ወደ ሌላው ያገላብጣሉ። ኤክስካቫተሮቹ ቆሻሻ በዛቁ ቁጥር የሚገለማ አስቀያሚ ሽታ አካባቢውን ይጫነዋል። ለቁጥር የሚታክቱ ዝምቦች ወዲህ ወዲያ ይበራሉ። የተበከለ የቆሻሻ ፍሳሽ ከኤክካቫተሮቹ አካፋ ላይ ይንጠባጠባል። የኤክስካቫተሮቹ ሾፌሮች ራሳቸውን ከሽታው ለመጠበቅ ሁለትም ሦስትም የኮቪድ መከላከያ ጭንብል ከአፍና አፍንጫቸው አድርገዋል።

በዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ የቆሻሻው ክምር ሲናድ ድሆች ከሚኖሩበት የኪቴዚ መንደር ራሳቸውን ማዳን የቻሉት 14 ሰዎች ብቻ ናቸው። የቆሻሻው ክምር ከተናደባቸው መኖሪያ ቤቶች የ35 ሰዎች አስከሬኖች ተገኝተዋል። ዩጋንዳ ሌሎች የሚተርፉ ሰዎች ካሉ ፍለጋ ስታካሒድ ቆይታለች። የሕይወት አድን ፍለጋውን የሚመራው ቀይ መስቀል ግን አደጋው ከደረሰ ከአንድ ሣምንት በኋላ ሰው በሕይወት የተረፈ ሰው የማግኘት ተስፋ እንደሌለ አስታውቋል።

በዩጋንዳ የቶማስ ክዎዬሎ ፍርድ ፍትህ አስገኝቶ ይሆን ?

የፖሊስ መኮንኖች አደጋ ወደ ደረሰበት ሰዎች አልፈው እንዳይገቡ በቢጫ የማስጠንቀቂያ ምልክት አካባቢውን አጥረውታል። ዝናባማው ወቅት ቀስ እያለ እየገባ በመሆኑ የቆሻሻው ክምር ዳግም ሊናድ ይችላል የሚል ሥጋት አለ። የከተማው ምክር ቤት አደጋው በደረሰበት አካባቢ 200 ሜትር ራዲየስ ውስጥ በሚገኙ  ቤቶች የሚኖሩ ሁሉ ወደ ሌላ አካባቢ ሊዘዋወሩ እንደሚገባ ወስኗል።

ፕሮስኮቪያ ናባፉ መኖሪያ ቤታቸው ግድግዳ ላይ በቀይ ቀለም ምልክት የተደረገበት ሲሆን ግቢያቸው በቢጫ ፕላስቲክ ታጥሯል። የ44 ዓመቷ የአራት ልጆች እናት በመኖሪያ ቤታቸው ሣህኖች እና ብርጭቆዎች እየሰበሰቡ ነው።

“ከዚህ እንድንሔድ ትዕዛዝ ተሰጥቶናል። ነገር ግን ይኸ ለእኛ ፍትሐዊ አይደለም። ከእኛ ይልቅ ቆሻሻውን እያስቀደሙ ነው” የሚሉት ናባፋ በመንግሥት ውሳኔ ደስተኛ አይደሉም። የመኖሪያ ቤታቸው ሊፈርስ እንደሚችል ሥጋት ያላቸው የአራት ልጆች እናት “ነገ ምን እንደሚሆን አናውቅም። ካሳ ሊከፍሉን ቃል ሊገቡ ይችላሉ። ከዚያ 5 ሚሊዮን ሰጥተውን ዝም ይላሉ። ነገር ግን የምሔድበት የለኝም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ፕሮስኮቪያ ናባፉ
ፕሮስኮቪያ ናባፉ የዩጋንዳ መንግሥት የቆሻሻው ክምር በመደርመሱ ችግር ውስጥ የወደቁ ዜጎችን በገንዘብ እንዲያግዝ ይፈልጋሉ። ምስል Simone Schlindwein/DW

ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ሰለቦች ቤተሰቦች 5 ሚሊዮን ሽልንግ (1,300 ዶላር ወይም 1,169 ዩሮ) ገደማ ጉዳት ለደረሰባቸው ደግሞ አንድ ሚሊዮን ሽልንግ ለእያንዳንዳቸው እንዲከፈል አዘዋል።

ውጤታማ ያልሆነው የዩጋንዳ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት

ሁለት ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎች ባሏት የዩጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ በየቀኑ 2,500 ቶን ቆሻሻ ይመረታል። ከዚህ ውስጥ 1200 ቶን የሚሆነው ቆሻሻ በጭነት መኪና የሚሰበሰብ ነው። የተቀረው ይቃጠላል ወይም በየጉድጓዱ ይደፋል። በዩጋንዳ ብስባሽ፣ ወረቀት ወይም ፕላስቲክ አንዱ ከሌላው የሚለይበት ሥርዓት የለም። ከሙዝ ልጣጭ እስከ አሮጌ የኤሌክትሮኒክ ቁሳቁሶች አንድ ላይ ወደ ቆሻሻው ተራራ ይከመራሉ።

የኪቴዚ የቆሻሻ መጣያ ለዓመታት ለካምፓላ ከተማ ስተዳደር ችግር ሲፈጥር የቆየ ነው። ከ28 ዓመታት በፊት በቦታው ቆሻሻ መጣል ሲጀመር በሦስት ተራራዎች መካከል የሚገኝ ጎድጓዳማ ሥፍራ ነበር። ቆሻሻ የሚሰበስቡ ተሽከርካሪዎች ወደ ቦታው እያቀኑ ዝም ብለው የጫኑትን ያራግፋሉ። በሒደት የቆሻሻው ጥርቅም ግዙፍ ተራራ ፈጠረ።

በተራሮቹ መካከል የነበረው ጎድጓዳማ ሥፍራ ከሞላ 16 ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህ ምክንያት የከተማ አስተዳደሩ ጭምር አዲስ የቆሻሻ ማስወገጃ ሥፍራ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ እምነት አለው። ከስምንት ዓመታት በፊት ሙኮኖ በተባለ የከተማው ክፍል ቆሻሻ በአግባቡ ለማስወገድ የከተማ አስተዳደሩ አዲስ ቦታ መርጧል። ይሁንና የቆሻሻ ማስወገጃውን ለመገንባት የሚያስፈልገው ገንዘብም አልተገኘም። በዚህ ምክንያት የካምፓላ ቆሻሻ በኪቴዜ መጠራቀሙ ቀጠለ።

ሙስና እና የመልካም አስተዳደር እጦት ያማረራቸው የኬንያ ተቃዋሚዎች

ርዋንዳ እና ኬንያን መሰል ጎረቤት ሀገራት ቆሻሻ በመለየት ፕላስቲኩን መልሶ መጠቀም፣ ባዮ ጋዝ ማምረት እና አትክልቶችን በማበስበስ ለማዳበሪያነት ማዋል ጀምረዋል። የዩጋንዳ መንግሥት ግን በዚህ ረገድ ወደ ኋላ ቀርቷል። ብሔራዊ የቆሻሻ አወጋገድ ዕቅድ ይፋ የተደረገው ከአራት ዓመታት በፊት ነው። ይሁንና በገንዘብ እጥረት ምክንያት ተግባራዊነቱ እጅግ ዘግይቷል።

የዩጋንዳ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ
የቆሻሻው ክምር ከተደረመሰ በኋላ የዩጋንዳ ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ “በእንዲህ አይነት ለጤና ጠንቅ እና አደገኛ በሆነ ቦታ ሰዎች እንዲኖሩ ማን እንደፈቀደ” ማወቅ እፈልጋለሁ ብለዋል። ምስል SIMON MAINA/AFP/Getty Images

ሙዋዳ ንኩንይንጊ አካባቢውን በመወከል ምርጫ ተወዳድረው የዩጋንዳ ምክር ቤት አባል ናቸው። ተቃዋሚው ፓርቲያቸው ብሔራዊ የአንድነት መድረክ (NUP) በኪቴዚ አካባቢ ተደማጭ ነው። አደጋው ከደረሰበት ቦታ አቅራቢያ ቦቲ ጫማ ተጫምተው የቆሙት ሙዋዳ “ነዋሪዎችን ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወር ብቸኛው አማራጭ ሆኖ ሊቀርብ አይገባም” ሲሉ ይተቻሉ።

“የቆሻሻ መጣያው ውጤታማ አስተዳደር ይፈልጋል” የሚሉት ተቃዋሚው ፖለቲከኛ “ለአደጋ እያጋለጠ የሚገኘው በአካባቢው የሚኖሩትን ብቻ አይደለም። ከቆሻሻው የሚወጣው በካይ ጋዝ እና አስቀያሚ ሽታ ርቀው የሚኖሩ ሰዎች ላይ ጭምር ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። ስለዚህ ተገቢ ምርመራ ሊደረግ ይገባል የሚል እምነት አለን” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።  

ምንም ፍራሽ እና በቂ ምግብ የለም

ቀይ መስቀል አደጋው ከደረሰበት ቦታ ራቅ ብሎ በሚገኘው የኪቴዚ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነጫጭ ድንኳኖች አዘጋጅቷል። አብዛኞቹ ሕጻናት የሆኑ ወደ 120 ገደማ ሰዎች በድንኳኖቹ ውስጥ ተቀምጠዋል፤ አሊያም ጋለል ብለዋል። ከጀርባቸው ሰባት መጸዳጃ ቤቶች ይገኛሉ። ፍራሽ፣ የመጸዳጃ ቤት ወረቀት፣ ሳሙና የመሳሰሉ አስፈላጊ ነገሮች ከፍተኛ እጥረት አለ።

ኪቴዚ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ አደጋ
ኪቴዚ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ለጤና አደገኛ እንደሆነ በርካቶች ሥጋት አላቸው።ምስል BADRU KATUMBA/AFP

ፕሮስኮቪያ ናባፉን የመሰሉ እና በመኖሪያ ቤቶቻቸው መቆየት የተከለከሉ ሰዎች በየሰዓቱ ወደ መጠለያው ይደርሳሉ። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ሥር የሚገኘው የየሲቪል ሰዎች ጥበቃ ምግብ ያቀርባል።

ሩሲያ እና ዩክሬን በአፍሪካ የእጅ አዙር ጦርነት እያካሔዱ ነው?

የዩጋንዳ ቀይ መስቀል ባልደባ ጆን ክሊፍ ዋማላ “በበጎ ፈቃደኞች በኩል ሰዎች አልባሳት፣ የሴቶች እና የሕጻናት የንጽህና መጠበቂያዎች እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበናል” ሲሉ ተጨማሪ ዕገዛ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

የኪቴዚ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ከአደጋው በኋላ ተዘግቷል። ተሽከርካሪዎች ቆሻሻ በቦታው ማራገፍ አይችሉም። በሣምንቱ መጀመሪያ በካምፓላ የተለያዩ አካባቢዎች ቆሻሻ ተከምሮ ይታይ ነበር። የሀገሪቱ ባለሥልጣናት  ተሽከርካሪዎች በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የኢንቴቤ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ወስደው እንዲያራግፉ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

የኢንቴቤ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ በአንጻሩ ከቪክቶሪያ ሐይቅ አጠገብ የሚገኝ ነው። የአካባቢ ደህንነት ተሟጋቾች እና የሀገሪቱ የዱር እንስሳት ባለሥልጣን በቦታው የሚከመረው ቆሻሻ ሐይቁን እንደሚበክል አስጠንቅቀዋል። ዩጋንዳ ግን በአፋጣኝ የረዥም ጊዜ መፍትሔ ያስፈልጋታል።

ሲሞን ሽሊንድቫይን/ እሸቴ በቀለ

ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር