1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሙስና እና የመልካም አስተዳደር እጦት ያማረራቸው የኬንያ ተቃዋሚዎች

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 4 2016

ባለፈው ሐሙስ ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ኬንያውያን ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተኮሷል። ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር እና የሥራ ዕድል እጦት ያማረራቸው ወጣቶች ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ሥልጣን እንዲለቁ ሲጠይቁ ይደመጣል። የኬንያ ባለሥልጣናት አጠያያቂ በሆነ መንገድ ያካበቱት ሐብት የተቃውሞ አስተባባሪዎችን እጅግ ከሚያናድዱ ጉዳዮች መካከል ይገኝበታል።

https://p.dw.com/p/4jK7Y
የኬንያ ተቃውሞ
ካለፈው ሰኔ ጀምሮ የተሻለ ዕድል እጦት ያማረራቸው ኬንያውያን ወጣቶች ተቃውሞ እያደረጉ ነው። ምስል Monicah Mwangi/REUTERS

ሙስና እና የመልካም አስተዳደር እጦት ያማረራቸው የኬንያ ተቃዋሚዎች

ዲጄ ራፋኤል ኦሞንዲ በሙዚቃ ማጫዎች እና ስፒከሮች ተከቦ ከናይሮቢ በምትገኝ ትንሽ የመኖሪያ አፓርታው ውስጥ ተቀምጧል። በጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪ ቢኖረውም የ24 ዓመቱ ወጣት ሥራ አግኝቶ አያውቅም።

በሀገሪቱ የተንሰራፋ ሙስና እና የመልካም አስተዳደር እጦት ጋዜጠኛ የመሆን ሕልሙን እንዳኮላሸ ኦሞንዲ ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።

“ለሥራ ባመለከትኩ ቁጥር ወይ ምንም ምላሽ አላገኝም፤ አለበለዚያ ደግሞ የሥራ ቦታው በትውውቅ ለሌላ ሰው እንደተሰጠ ይነገረኛል” የሚለው ኦሞንዲ ችግሩ የእርሱ ብቻ እንዳልሆነ ያውቃል።

“በመሪዎቻችን እየመከነ ያለው መላ ትውልዱ ነው” የሚለው የ24 ዓመት ወጣት ባለፈው ሐሙስ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጡ መካከል ነው።

ተቃውሞው “ናኔ ናኔ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት ነበር። “ስምንት ስምንት” ማለት ነው። የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር ተከትሎ የተሰጠ ሥያሜ ነው።

ፖሊስ በዕለቱ ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል። እነ ኦሞንዲ ግን የሚያፈገፍጉ አይመስልም።

ማሕደረ ዜና፣ የኬንያዎች አመፅ፣ ሩቶ «አዉሮፕላኑ አምልጧቸዉ» ይሆን?

“ሀገራችንን መልሰን ከእጃችን እናስገባለን” የሚለው ራፋኤል ኦሞንዲ ፕሬዝደንቱ ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ አመርቂ ሥራ አከናውነዋል ብሎ አያምንም።

ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ
ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ተቃውሞዎቹን ለማብረድ የካቢኔ አባላቶቻቸውን አባረው ነበር።ምስል Brendan Smialowski/AFP/Getty Images

“ስለ እኛ የሚያስብ መንግሥት እንዲኖረን ፕሬዝደንቱ ከሥልጣን እንዲለቁ እንፈልጋለን። በማናቸውም ዋጋ አዲስ ጅማሮ ያስፈልጋል። ለውጥ ለማምጣት ትክክለኛው ጊዜ ነው” የሚል አቋም አለው።  

ኦሞንዲ እንደሚለው ኬንያውያንን እየደጋገመ ለተቃውሞ ሰልፍ እንዲወጡ የሚያስገድዷቸው በቂ የሙስና እና የመልካም አስተዳደር እጦት ችግሮች አሉ።

“ምንም የምንፈራው ነገር የለም። ይኸ የወደፊት ዕጣ ፈንታችን የሚወሰንበት ወሳኝ ጊዜ ነው። አሁን ለመብታችን መቆም ካልቻልን ነገሮች የበለጠ ሊባባሱ ይችላሉ” የሚለው ራፋኤል የሙዚቃ ሥራዎቹ የበኬንያ ሊመጣ ይገባል የሚለው አብዮት ማጀቢያ እንዲሆኑ ይሻል።

የኬንያ ፕሬዚደንት ከአመጹ ጀርባ የውጭ ዜጎች እጅ አለበት አሉ

ሌሎች ኬንያውያን በተደጋጋሚ የሚካሔዱት የተቃውሞ ሰልፎች እንዲቆሙ ይፈልጋሉ። ምክንያታቸው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ ነው። በአሁኑ ወቅት በየሣምንቱ ማክሰኞ እና ሐሙስ የንግድ እንቅስቃሴ ይስተጓጎላል።

“ኦሞሽ አንድ ሰዓት” ወይም “ጃካባባ” በሚል የቅጽል ስሙ የሚታወቀው ሻድራክ ኦሞንዲ ኦርዋ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ሥልጣን ከያዙም ሆነ ከዚያ በፊት ኡኹሩ ኬንያታ ሀገሪቱን ሲመሩ በመንግሥት ላይ በሚሰነዝረው ትችት ይታወቃል።

የተቃዋሚዎች ደጋፊ የሆነው ኦርዋ በሥራዎቹ የኬንያውያንን የሕይወት ትግል ማንጸባረቅ የሚያዘወትር ታዋቂ ኮሜድያን ነው። በርካቶችን ያስገረመው ኦርዋ ጭምር በተቃውሞዎቹ መሰላቸቱን እና ሀገሪቱ ወደ ፊት እንድትራመድ መፈለጉን ሲናገር ነበር።

ባለፈው ሐሙስ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ “ወጣቶችን ቁጣ እና ንዴት እረዳለሁ” ይላል ኦርዋ። “ነገር ግን እንደ ኬንያውያን በዚህ አልተደናገጥንም። መንግሥትን እንደግፋለን። ወደ ፊት መራመድ እና አብሮ መሥራት እንፈልጋለን። ተጨማሪ ኹከት እና አለመረጋጋት አንፈልግም” የሚል አቋም አለው።

ኦርዋ ያለ ማቋረጥ የሚካሔድ ተቃውሞ መፍትሔ ያመጣል የሚል እምነት የለውም። በተቃውሞው የገፋበት እና “ጄኔሬሽን ዜድ” ተብሎ የሚጠራው የመጨረሻው ትውልድ ፍላጎቱን በአግባቡ የሚወክል መሪ ሊመርጥ እንደሚገባ ይመክራል።

“ያን ማድረግ ካልቻሉ ጊዜው ሀገራችን ወደፊት የምትራመድበት መሆን አለበት” የሚለው ኦርዋ “በትብብር በመሥራት እና ለሁሉም የተረጋጋ እና ሰላማዊ ከባቢ በመፍጠር ላይ ልናተኩር ይገባል” ሲል ይሞግታል።

የኬንያ ፖሊስ በተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ሲተኩስ
ፖሊስ ባለፈው ሐሙስ ተቃዋሚዎችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተኩሷልምስል Thomas Mukoya/REUTERS

እንዲህ አይነቱ መከራከሪያ ግን ካስሙኤል ማክኡሬ ተቀባይነት የለውም።

ካስሙኤል ማክኡሬ “የዩኒቨርሲቲ ክፍያ ስንት እንደደረሰ አይታችኋል፤ ነገር ግን ሰዎች መቃወም የለባቸውም? ምክንያቱም የጎሳ አለቆቻችሁ የመንግሥት ሥልጣን ስላገኙ ድንገት እናንተም እንደ ወጣት መንግሥት ናችሁ ማለት ነው?” እያለ ይሟገታል።

ባለፈው ሐሙስ የተካሔደው ተቃውሞ በወጣት ማኅበራት እና የሲቪክ ድርጅቶች የተቀናጀ ነው። ተቃውሞው በዋናነት ለዓመታት የዘለቀ ኤኮኖሚያዊ ችግር፣ ከፍተኛ ሥራ አጥነት እና በሀገሪቱ በተንሰራፋው ሙስና ምክንያት የተቀሰቀሰ ነው።

በወጣቶች የሚመራው ተቃውሞ እንዲጠናከር ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ድጋፍ በማሰባሰብ ከፍ ያለ ሚና ተጫውተዋል። በተቃውሞዎቹ ከፍተኛ ተደማጭነት እያገኘ የመጣው የ27 ዓመቱ የለውጥ አራማጅ ካስሙኤል ማክኡሬ ወጣት ኬንያውያን ከመንግሥት በሚሰጣቸው ቀቢጸ ተስፋ ተሰላችተዋል ይላል።

ማክኦሬ በተለይ የኬንያ የካቢኔ ሚኒስትሮች አጠያያቂ በሆነ መንገድ ያከማቹት ሐብት እጅግ ያናድደዋል። “ባለፉት 30 ዓመታት ሰዎች 400 ሚሊዮን ሽልንግ አግኝተዋል እንበል። ነገር ግን የሆነ ሰው ከሁለት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከ200 ሚሊዮን ሽልንግ በላይ አግኝቷል” የሚለው ካስሙኤል “እኛ የማናውቀው ምን አይነት ሥራ ቢሰሩ ነው ይኸን ያህል ገቢ ያገኙት” ሲል ይጠይቃል።

በአፍሪቃ የጨመረው የወጣቶች ተቃውሞ

“እንዲያም ሆኖ እኛ ተቃውሞ እንዳንወጣ ልትነግሩን ትፈልጋላችሁ? ወጣቶች መታወቂያ ማግኘት አትችሉም፤ ነገር ግን መብቶቻቸው እንዲከበር ተቃውሞ ለማሰማት ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ትናገራላችሁ” ይላል።

በኬንያ የወጣቶች ሥራ አጥነት ከ35 በመቶ በላይ ደርሷል። ከፍተኛ የኑሮ ውድነትም አለ። የኤኮኖሚ ባለሙያው ሳሙኤል ካራንጃ የወጣቶቹ ቅሬታ ምክንያታዊ እንደሆነ ይናገራሉ።

“ሙስና እና ብልሹ አስተዳደር የኤኮኖሚ ዕድገትን እና የሥራ ዕድል ፈጠራን አንቀው ይዘውታል” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ወጣቶቹ ተጠያቂነት እና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የመጠየቅ ሁሉም መብት አላቸው የሚሉት ካራንጃ አጠቃላይ የሥርዓት ለውጥ እንደሚያስፈልግ ያምናሉ።

አንድሪው ቫሲከ/እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ