1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አወዛጋቢው የህወሓት ጉባኤ ያሳለፈው ውሳኔ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 11 2016

ህወሓት የፓርቲው ማእከላይ ኮሚቴ እና ቁጥጥር ኮምሽን በፓርቲው ስም የሚያደርጉት ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ውሳኔ አስተላለፈ። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው የህወሓቱ ጉባኤ ውሳኔዎች እና ውጤቶች ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው ብለዋቸዋል።

https://p.dw.com/p/4ja93
Generalversammlung der TPLF wird von Nationaler Wahlbehörde Äthiopiens (NEBE) nicht anerkannt
ምስል Million Haileselassie/DW

አወዛጋቢው የህወሓት ጉባኤ ያሳለፈው ውሳኔ

ጉባኤ ላይ ያለው ህወሓት የፓርቲው ማእከላይ ኮሚቴ እና ቁጥጥር ኮምሽን በፓርቲው ስም የሚያደርጉት ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆሙ ውሳኔ አስተላለፈ። ይህ ውሳኔ በጉባኤው የተላለፈው ነባሩ ማእከላይ ኮሚቴ እና ቁጥጥር ኮምሽን የስራ ግዚያቸው በመገባደዱ ነው ተብሏል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው የህወሓቱ ጉባኤ ውሳኔዎች እና ውጤቶች ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው ብለዋቸዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሰባት ሲቪክ ተቋማት የትግራይ ፖለቲከኞች ለስልጣናቸው ሲሉ በሚፈጥሩት ችግር የትግራይ ህዝብ ለአደጋ ተጋልጦ ይገኛል አሉ። ፓለቲከኞቹ ለመሸምገል የተደረገ ጥረትም እንዳልተሳላቸው ሲቪክ ተቋማቱ ገልፀዋል። 

14ተኛ ጉባኤ ላይ ያለው ህወሓት ዛሬየጉባኤ ውሳኔብሎ ባሰራጨው መግለጫ እንዳለው፥ በህወሓት ሕገና ደንብ መሰረት ካለፈው ጉባኤ ጀምሮ እስካሁን ስራ ላይ የቆየው ማእከላይ ኮሚቴ እና ማእከላዊ ቁጥጥር ኮምሽን የስልጣን ግዜው ስላበቃ፥ በህወሓት ስም ፓለቲካዊ ስራዎች መተግበር እንደማይችል አስታውቋል። ጉባኤ ላይ ያለው ህወሓት እንዳለው የፓርቲው ማእከላይ ኮሚቴ ይሁን ቁጥጥር ኮምሽን ስራ ላይ የሚቆየው በሁለት ጉባኤዎች መካካል ነው የሚል ሲሆን፥ አሁን ላይ 14ተኛ ጠቅላላ ጉባኤ ካለፈው ነሐሴ 8 ቀን ጀምሮ በመሰየሙ ቀጣይ ፓለቲካዊ ስራዎች መፈፀም የሚያስችለው ሓላፊነት ያለው ማእከላይ ኮሚቴ ይሁን ቁጥጥር ኮምሽን የለም በማለት፥ በህወሓት ስም ፓለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ሲል አግዷል። ይህም የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንትና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ጨምሮ ሌሎች ከጉባኤው ራሳቸው ያገለሉ የማእከላይ ኮሚቴ አባላት፥ በጉባኤው ከነበራቸው የፓርቲ ሐላፊነት መታገዳቸው የሚያሳይ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ተብሎለታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ለክልሉ መንግስት ሚድያዎች መግለጫ የሰጡት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ፥ እየተካሄደ ያለው ጉባኤ ሁሉም የህወሓት አባል የማይወክል፣ በተወሰኑ የማእከላይ ኮሚቴ አባላት ፍላጎት የሚደረግ እንዲሁም ውጤቱ እና ውሳኔዎቹ ተቀባይነት የሌለው በማለት እንደኮነኑት ትግራይ ቴሌቭዥን ያሰራጨው መረጃ ያመለክታል። 

በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተነፈገው የህወሓት ጉባኤ
በምርጫ ቦርድ ዕውቅና የተነፈገው የህወሓት ጉባኤምስል Million Haileselassie/DW

በትግራይ ይህ በህወሓት ውስጥ ያለ የፖለቲከኞች ውዝግብ በርካቶችን አሳስቧል። በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሰባት ሲቪል ተቋማት በጋራ ባሰራጩት መግለጫ፥ የክልሉ መሪዎች ለስልጣን እና ለግል ጥቅም ብለው በሚፈጥሩት ውዝግብ ምክንያት የትግራይ ድህንነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ ተፈጥሯል በማለት ያለው ሁኔታ እንዳሳሰባቸው እና እንዳሳዘናቸው አስታውቀዋል። ሲቪክ ተቋማቱ ልዩነቱ ለመፍታት ጥረት ማድረጋቸው ይሁንና ጥረቱ አለመሳካቱም ገልፀዋል። ሲቪል ተቋማቱ ባዘጋጁት መድረክ የተናገሩት የትግራይ እስልምና ጉዳዮች ምክርቤት ዋና ፀሐፊ ሓጁ መሓመድ ካሕሳይ "ተፈናቃዮች አራት በጋ እና አራት ክረምት በፕላስቲክ ድንኳን ተጠልለው እያሉ፣ ሌሎች መዓት ችግሮች እያሉ ስለወንበር፥ ስልጣን ማውራት መልካም አይደለም። መጀመርያ ትግራይ እና ተጋሩ እናድን። ወደተሻለ ደረጃ ካሸጋገርን በኃላ ማለት የሚገባን ነገር እንበል። እኛ ደግሞ እንደማሕበራት፣ የትግራይ ህዝብ እንደምንወክል እያልነው ያለ ነገር ሊሰማ ይገባል" ብለዋል።

የትግራይ ስቪል ማሀረበረሰብ ጥምረት፣ ትግራይ ህዝባዊ ግንኙነት ምክር ቤት፣ ጥላ የምዕራብ ትግራይ ስቪክ ማህበረሰብ ማህበር፣ የትግራይ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት እና ሌሎች መግለጫው ካወጡ ሲቪክ ተቋማት መካከል ናቸው። የማሕበር ሕውነት ደቂሰብ መረዳጃ ድርጅት ስራ አስከያጅ መምህር ፍቅረ አሰፋ በበኩላቸው "አካሄዳቸው ሊያስተካክሉ፣ ወደ ሰላም ሊመለሱ፣ በፍቅር መንገድ ሊመላለሱ ሊነገራቸው ይገባል። ይበቃል መባል አለባቸው። አስተካክሉ ሊባሉ ይገባል። ህዝባችን የሚፈልገው ይህ ነው" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማሕበራት ፕሬዝደንት አቶ በሪሁ ሀፍቱ በበኩላቸው የትግራይ የፖለቲካ አመራር ህዝብን በመርሳት በግል ጥቅም ተጠምዷል ብለዋል። አቶ በሪሁ "አመራሩ ከህዝብ የወጣ ከሆነ ህዝብን ነው መመልከት ያለበት። ህዝብ መምሰል አለበት። የትግራይ ህዝብን እንዴት መጥቀም አለብኝ ማለት መቻል አለበት እንጂ፥ በዚህ ሰዓት የግል ጥቅምና ትርፍ ላይ ማትኮሩ ትግራይን አይጠቅምም" ብለዋል።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር