1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በውዝግብ የታጀበው ጉባኤ

ሰኞ፣ ነሐሴ 6 2016

የህወሓት ማእከላዊ ቁጥጥር ኮምሽን ህወሓት ውስጥ ያለ አንድ ቡድን በማንአለብኝነት፣ እልህ እና ግልፅነት በጎደለው አካሄድ ለራሱ ጥቅም ሲል ጉባኤ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው በማለት ኮንኗል።

https://p.dw.com/p/4jOIr
ደብረጽዮን ገብረሚካኤል(ዶ/ር) የህወሓት ሊቀመንበር
ደብረጽዮን ገብረሚካኤል(ዶ/ር) የህወሓት ሊቀመንበርምስል Million Haileselassie/DW

በውዝግብ የታጀበው ጉባኤ

በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው ክፍፍል እየሰፋ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከነገ ጀምሮ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያደርግ ፓርቲው አስታወቀ። የህወሓት ምክትል ሊቀመንበርን ጨምሮ 14 የፓርቲው ማእከላይ ኮሚቴ አባላት ከጉባኤው ራሳቸው አግልለዋል። ይህ የፖለቲካ ውጥረት እና ሌሎች ምክንያቶች በመጥቀስ የክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በትግራይ ላልተወሰነ ግዜ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት መታገዱ አስታውቀዋል።

በህወሓት መካከል የሰፋ ልዩነት እየታየ ባለበት፣ በርካታ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች በየደረጃው ያሉ ካድሬዎች በጉባኤው አንሳተፍም እያሉ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት ፓርቲው ከነገ ጀምሮ የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ አስታውቋል።

በህወሓት አመራር ላይ እየታየ ያለው ችግር በጉባኤው እፈታለሁ ያለ ሲሆን የጉባኤው ተሳታፊዎችም ወደ መቐለ እየገቡ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግንየህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 14 የፓርቲው ማእከላይ ኮሚቴ አባላት ከጉባኤው ራሳቸው ማግለላቸው ያስታወቁ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከተለያዩ የትግራይ ወረዳዎች ተወክለው በጉባኤው ሊሳተፉ የነበሩ የፓርቲው አባላትም ከዚሁ መድረክ ራሳቸው በማግለል ላይ ናቸው።

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕረዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳ
የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕረዚደንት አቶ ጌታቸው ረዳምስል Million H. Silase/DW

ህወሓት ከውስጥ ክፍፍሉ በተጨማሪ በፓርቲው ህጋዊነት ጉዳይም ውዝግቡ እየቀጠለ ያለ ሲሆን፥ ከምርጫ ቦርድ በልዩ ሁኔታ ተብሎ የተሰጠው እውቅናም እንደማይቀበል አስታውቋል። በዚህ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ትላንት መግለጫ የሰጡት የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ህወሓት የጠየቀው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ ሆኖ ሳለከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተሰጠው ምላሽ ግን እንደ አዲስ ፓርቲ የሚያስቆጥረው እውቅና ነው በማለት ይህም ህወሓት አይቀበለውም ብለዋል።

ደብረፅዮን ገብረሚካኤል "ጥያቄው ሌላ ነው፥ የተሰጠው ምላሽ ደግሞ ሌላ ነው። ጥያቄአችን የተሰረዘ ሕጋዊ ሰውነታችን ይመለስ ነው። እዚህ ላይ የምርጫ ቦርድም ስራቸው ነው የሰሩት፣ የማመሰግናቸውም ነገር አለ። ጥያቄአችን ምን እንደሆነ በግልፅ አስቀምጠዋል። ስለዚህ ጉዳዩ ወደ ፌደራል መንግስት ይመለሳል ነው" ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ ዛሬ መግለጫ ያወጣው የኢፌድሪ የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት የፌደራል መንግስቱ ህወሓት ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ድጋፍ ማድረጉ፣ በተሻሻለው አዋጅ መሰረት ደግሞ ተመዝግቦ ሕጋዊ ሰውነቱ ማግኘቱ የገለፀ ሲሆን፥ በዚህ ዙርያ ያሉ ንትርኮች እንዲያበቁ እና ወደ ሌሎች የመልሶ ግንባታ፣ ሰላም እና ልማት አጀንዳዎች መሻገር እንደሚገባ ገልጿል።

የህወሓት 45ኛ ዓመት አከባበር
የህወሓት 45ኛ ዓመት አከባበር ምስል DW/M. Haileselassie

ይህ በእንዲህ እንዳለ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በትግራይ የፖለቲካ ውጥረቱ ማየሉ በማንሳት እና ሌሎች ምክንያቶች በመጥቀስ፥ ለክልሉ በግዚያዊነት ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት መታገዱ ገልፀዋል።

ጀነራል ታደሰ "በሆነ ይሁን መንገድ የሆነ መፈክር ይዘህ፣ ሌላ ከፖለቲካ ውጪም ቢሆን የሆነ መነሻ ወይ መፈክርም ቢሆን፣ በፖለቲካም ለተቃውሞ አልያም ለደግፎ የሚደረግ ሰልፍ አንፈቅድም" ብለዋል።

በሌላ በኩል በጉባኤው ዋዜማ ዛሬ መግለጫ ያወጣው የህወሓት ማእከላዊ ቁጥጥር ኮምሽን  ህወሓት ውስጥ ያለ አንድ ቡድን በማንአለብኝነት፣ እልህ እና ግልፅነት በጎደለው አካሄድ ለራሱ ጥቅም ሲል ጉባኤ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው በማለት ኮንኗል። የህወሓቱ ሊቀመንበር ደብረፅዮን ግን ጉባኤው ህወሓት ከገባበት ችግር እና አለመግባባት የሚታደግ መድረክ ነው ብለውታል። ከዚህ በተጨማሪ ሊቀመንበሩ ጉባኤ ከማድረግ ጋር ተያይዞ የሚፈጠር የከፋ ችግር የለም የሚሉ ሲሆኑ፥ ጉባኤ ለማድረግ የተለየ ፍቃድ ከማንም ማግኘት አያስፈልገንም ሲሉ አክለዋል።

ውዝግብ እና ንትርኩ በናረበት በዚሁ ወቅት 14ተኛ የተባለው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ከነገ ጠዋት ጀምሮ ደረጋል ተብሏል።


ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ኂሩት መለሰ