1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋቡን ምርጫ፣ ቦንጎዎች አስተዳደር፤ የቫግነር ተፅዕኖ በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 20 2015

የዓሊ ቦንጎ አባት ዑመር ቦንጎ የመሰረቱት ሰፊ ቤተ-ሠብ የዓሊን ሥልጣን ለማጠናከር ለማወላከፍም ምክንያት መሆኑ አይቀርም።አባት ቦንጎ ዓሊን ጨምሮ ሐምሳ ልጆች ነበሯቸዉ።ሐብታቸዉም በዛዉ ልክ ነበር።ፈረንሳይ ዉስጥ ብቻ 40 የቅንጦት ቤትና ንብረት ነበራቸዉ።በ66 ባንኮች ዉስጥ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ አከማችተዋል

https://p.dw.com/p/4Vb2i
ፕሬዚንደንት ዓሊ ቦንጎ በምርጫ ዘጠመቻ ወቅት-2015
ፕሬዚንደንት ዓሊ ቦንጎ በምርጫ ዘመቻ ወቅት-2015ምስል imago images/Afrikimages

የጋቡን ቤተሰባዊ አስተዳደርና ምርጫ፤ የቫግነር ቡድን በአፍሪቃ

 

                              የጋቡን ምርጫና የቦንጎዎች አገዛዝ

ትንሺቱ ግን በነዳጅ ዘይት የበለፀገችዉ አፍሪቃዊት ሐገር ጋቡን ዛሬ ምርጫ ላይ ናት።የሐገሪቱ ሕዝብ የወደፊቱን ፕሬዝደንት፣የብሔራዊና የአካባቢ አስተዳደር ምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ ድምፅ ሲሰጥ ዉሏል።ጋቡን ሶስቱን ምርጫዎች ባንድ ቀን ስታስተናግድ የዛሬዉ የመጀመሪያዋ ነዉ።

ዋናዉ ትኩረት፣ ከፍተኛ ፉክክር የታየዉም ከምክር ቤቶቹ ይልቅ በፕሬዝደንታዊዉ ምርጫ ላይ ነዉ። «ለዉጥ እፈልጋለሁ።» ይላል የ27 ዓመቱ ወጣት ጆርዳን ማሳላ-ድምፅ ከመስጠቱ በፊት።ተማሪ ነዉ።

ፕሬዝደንት ዑመር ቦንጎ «ጤናቸዉ ያሰጋል»
ፕሬዝደንት ዑመር ቦንጎ «ጤናቸዉ ያሰጋል»ምስል Witt Jacques/Pool/ABACA/picture alliance

«በግሌ ለዉጥ ፈላጊ ነኝ።ይሕንን በሙስና የተተበተበ ሥርዓት ለማስወገድ ሚስተር ኦንዶ ኦሳን ነዉ የምመርጠዉ።»

                                  የአባትና የልጅ ሥርዓት

ይሁንና ከምርጫዉ በፊት የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት በፕሬዝደንታዊዉ ምርጫ ሐገሪቱን ለረጅም ጊዜ የመሩት ዓሊ ቦንጎ ማሸነፋቸዉ አይቀርም።ዓሊ ካባታቸዉ የወረሱትን  አልጋ በ2001 በምርጫ ካስከበሩ ወዲሕ ያቺን ሐብታም ትንሽ ሐገር እየመሩ ነዉ።የዓሊ አባት ኤል ሐጂ ዑመር ቦንጎ  ከ1959 ጀምሮ ጋቡንን ለ42 ዓመታት ያክል ገዝተዋል።በ2001 ሞት ባያነሳቸዉ ኖሮ ይቀጥሉ ነበር።56 ዓመታት ያስቆጠረዉን የአባትና የልጅ ሥርወ-መንግስትን ለማስወገድ ስድት የተቃዋሚ ፓርቲዎች አንድ የጋራ ዕጩ አርበዋል።የ69ኝ ዓመቱ ኦንዶ ኦሳ በዓሊ አባት በዑመር ቦንጎ ዘመን የትምሕርት ሚንስትር ነበሩ።ብዙ የፖለቲካ አዋቂዎች ያደንቋቸዋል።የጋቡን ፕሬዝደንታዊ ምርጫ

 

በዛሬዉ ምርጫ ግን፣ የፖለቲካ ተንታኝ ግይላድስ ኦፎዉላሐስት እንደሚያምኑት የቀድሞዉ ሚንስትር በድሮ አለቃቸዉ ልጅ በቀላሉ መሸነፋቸዉ አይቀርም።

 «ዓሊ ቦንጎ አሸናፊ መሆናቸዉ ምንም ጥያቄ የለዉም። ጥያቄዉ ፍፁም አብላጫ ድምፅ ያገኙ ይሆን ወይ የሚለዉ ነዉ።»

እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2016 በተደረገዉ ምርጫ ዓሊ ቦንጎ ዋና ተቀናቃኛቸዉን ያሸነፉት በጥቂት የድምፅ ልዩነት ነበር።የምርጫዉ ዉጤት ተጭበርብሯል በሚል በተነሳዉ ተቃዉሞና ግጭት ብዙ ሰዎች ተገድለዋል።የተቃዋሚዎቹ ዕጩ ኦንዶ ኦሳ የዛሬዉ ምርጫ የሰዉ ሕይወት የማይጠፋበት መሆን አለበት ይላሉ።

ሊበርቪል በ2008 በተደረገዉ ምርጫ ማግስት የተቀሰቀሰዉ ግጭት
ሊበርቪል በ2008 በተደረገዉ ምርጫ ማግስት የተቀሰቀሰዉ ግጭትምስል Reuters/Life Africa TV

                              የቦንጎ ዝግጅትና ጤና

ቦንጎም ካለፈዉ ምርጫ ብዙ ተምረዉ ተቀናቃኛቸዉን በቀላሉ የሚያሸንፉበትን ብልሐት፣ኃይልም፣ ደጋፊም ያደራጁ መስለዋል።ወድዶም፣ተጠቅሞም፣ ፈርቶም አክብሮም ድምፁን ሊሰጣቸዉ የተዘጋጀ በርካታ ሕዝብ መኖሩ በምርጫዉ ዘመቻዉ ወቅት ታይቷል።ከነዳጅ ዘይት ከሚዝቁት ገንዘብ እየቆነጠሩ  የሸጓጎጡለትም በታማኝነት እንደቆመ ነዉ።«ስራ ሰጥተዉናል።ሐገራችንን እያሳደጉ ነዉ» ይላል ኦሊቨር ምባንጎ።የሊቨርቪል ነዋሪ ነዉ።ከመፈንቅለ መንግሥት የተረፉት አሊ ቦንጎ ማን ናቸው?

                                 

«ያሸንፋሉ።ለጋቡን ሕዝብ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።ሥራ አጥነት ቀንሷል።ያሸንፋሉ።ምክንያቱን ሐገሪቱን አሳድገዋል።ጋቡንን።»

በርግጥም 2.4 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሐገሪቱ ሕዝብ የአንድ-ሶስተኛዉ ኑሮ ከድኽነት ጠገግ በታች ቢሆንም ከአብዛኛዉ የአፍሪቃ ሐገራት ሕዝብ ጋር ሲወዳደር ግን ሕዝቡ ብዙ ችግር አያዉቅም።የ64 ዓመቱ ፕሬዝደንት ጤና ግን ብዙም የሚያወላዳ አይመስልም።ከአምስት ዓመት በፊት ልባቸዉ ከታመመ ወዲሕ ባደባባይ በሰፊዉ የታዩት በሰሙኑ የምርጫ ዘመቻ ወቅት ነዉ።ጋቦን አዲስትዋን ጠቅላይ ሚኒስትር ሾመች

እጅና እግራቸዉ እንደልብ አይታዘዝላቸዉም ይባላልም።

                              የቦንጎ ቤተሰብ

የዓሊ ቦንጎ አባት ዑመር ቦንጎ የመሰረቱት ሰፊ ቤተ-ሠብ የዓሊን ሥልጣን ለማጠናከር ለማወላከፍም ምክንያት መሆኑ አይቀርም።አባት ቦንጎ ዓሊን ጨምሮ ሐምሳ ልጆች ነበሯቸዉ።ሐብታቸዉም በዛዉ ልክ ነበር።ፈረንሳይ ዉስጥ ብቻ 40 የቅንጦት ቤትና ንብረት ነበራቸዉ።በ66 ባንኮች ዉስጥ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ አከማችተዋል።አንዱ 1.5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቡጋቲ  የተሰኘዉን ጨምሮ  118 ዉድ መኪኖች ነበሯቸዉ።ሁሉንም ጥለዉት ሔዱ።

ዓሊ ቦንጎ የአባታቸዉን ሐብት፣ ስምና የቤተሰባቸዉን ብዛት ለስልጣናቸዉ ደግም-መጥፎም ሊሆን ስለሚችል ብዙም ሲያወሱና ሲያነሱት አይሰሙም።የዛሬዉ ምርጫ ግን ፕሬዝደንታዊ ብቻ ከሚሆን የብሔራዊዉ ፓርላማና የአካባቢያዊ አስተዳድርም  ምርጫ በመሆኑ ፕሬዝደንቱ ለማሸነፍ በጣም ይጠቅማቸዋል ነዉ የሚባለዉ።

የቫግነር ቡድን መሪ ሞተዉል መባሉና  ቡድን አፍሪቃ ዉስጥ የሚኖረዉ ሚና

የሩሲያዉ የቅጥረኛ ወታደሮች ኩባንያ የቫግነር ባለቤት የቭጌኒይ ፕሪጎዢን በአዉሮፕላን አደጋ መሞታቸዉ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።እስካሁን ግን ፕሪጎዢን ባለፈዉ ሮብ ወድቃ በተከሰከሰችዉ የግል አዉሮፕላን ዉስጥ መሳፈራቸዉ እንጂ በአደጋዉ መሞታቸዉ በትክክል አልተረጋገጠም።ከዩክሬኑ ጦርነት በኋላ የምዕራባዉያን መገናኛ ዘዴዎች በየሰበብ አስባቡ የሚያብጠለጥሏቸዉ ፕሪጎዢን በርግጥ ሞተዉ ከሆነ የሚመሩት ኩባንያ በዉጤቱም ሩሲያ ከአፍሪቃ ሐገራት ጋር የሚኖራት ግንኙነት እንዴትነት አዲስ ርዕስ ሆኗል።

የቫግነር ኩባንያ ባለቤት የፕሪጎዢን መታሰቢያ
የቫግነር ኩባንያ ባለቤት የፕሪጎዢን መታሰቢያ ምስል Anton Vaganov/REUTERS

የዶቸ ቬለዉ ፊሊፕ ዛንድነር እንደፃፈዉ ሩሲያ በተለይ ምዕራብና ማዕከላዊ አፍሪቃ ዉስጥ የምታሳድረዉ ተፅዕኖ የቫግነር ኩባንያ ባዘመታቸዉ ወታደሮች አማካይነት በግልፅ እየታየ ነዉ።ሩሲያ ከፍተኛ ድጋፍ ታደርግላቸዋላች ከሚባሉት አንዷ ቡርኪናፋሶ ናት።ምዕራብ አፍሪቃዊቱ ሐገር ዉስጥ ሁለት ጊዜ መፈንቅለ መንግስት ያደረጉት የጦር መኮንኖች ምዕራባዉያን መንግስታትን ገለል እያደረጉ ፊታቸዉን ወደ ሞስኮ አዙረዋል።የቭጌኒይ ፕሪጎዢን የሚመሩት የቫግነር ኩባንያም ርኩናፋሶ ዉስጥ ወታደሮች ማስፈሩ በሰፊዉ እየተነገረ ነዉ።የቫግነር እጣ ፋንታ በአፍሪቃ

የፕሪጎዢን ሞት ዋጋዱጉ እንደተሰማ አንድ የከተማይቱ ነዋሪ «ሊሆን አይችልም» አለ።ሌላዉ ደግሞ ፊሊፕ ዛንድነር እንደጠቀሰዉ ሰዉዬዉን «ደፋር፣ ፅኑ፣ዓላማ ያላቸዉ» በማለት አወድሷቸዋል።

                        ሥራ እንደወትሮዉ

ፕሪጎዢን በርግጥ ሞተዉ ከሆነ፣ የቫግነርን ቡድን ሥራና አወቃቀር የሚከታተሉት የፖለቲካ ተንታኝ አደሙ ከቢሩ እንደሚሉት ቡድኑ ራሱ ሊፈረካከስ ይችላል።

«ይሕ ምናልባት የቫግነር-ቡድን መሪ ቢሰደድ ወይም ቢሞት የዓመራር ለዉጥ ብቻ ሳይሆን በቡድኑ ዉስጥ ያለዉ የተማከለ ዕዝ ሊለወጥ፣ በተለያዩ የቡድኑ የዕዝ መዋቅሮች ዉስጥ መከፋፈል ወይም ጨርሶ መበታተን ሊያስከትልም ይችላል።ሥለዚሕ በዚሕ ላይ በመመስረት ሁኔታዉ ሲጤን በቡድኑ ዉስጥ ሊፈጠር የሚችለዉን ነገር ከወዲሁ ለመገመት በጣም ከባድ ነዉ።»

የቫግነር-ቡድን ከፍተኛ ተፅዕኖ ከሚያሳርፍባቸዉ የአፍሪቃ ሐገራት አንዷ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ናት።የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ታዛቢዎች  እንደሚሉት ባለፈዉ ሰኔ የቫግነር ወታደሮች በሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ካመፁ ወዲሕ ማዕከላዊ አፍሪቃ ዉስጥ ያለዉ የቫግነር መዋቅር ተቀይሮ የቡድንኑን አመራር ወይም አስተዳደር በባንጁል የሩሲያ ኤምባሲ ይቆጣጠረዋል የሚል ግምት አሳድሮ ነበር።ቫግነር ግሩፕ በአፍሪቃ አሁን ያለዉ ተፅእኖ ምንድን ነው?

ይሁንና የፕሬዝደንት ፋዉስቲን-አርቻንጄ ቶዋዴራ አማካሪ ፊደል ጎዋንድጄ ያኔ እንዳሉት የቫግነር ቡድን አመፀም-አላመፀ በሩሲያና በአፍሪቃዊቱ ሐገር መካከል ያለዉ ግንኙነት አይለወጥም።አሁንም ቢሆን የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር አዳሙ ከቢሩ እንደሚሉት ቫግነር- እንደ ቡድን ቀጠለም አልቀጠለ አፍሪቃ ዉስጥ ባሉት ዘመቻዎቹ ላይ ብዙ ለዉጥ አይኖርም።

«በቫግነር ቡድን ዉስጥ ያሉት ጉዳዮች ተለዋዋጭ ናቸዉ።በጠቅላላዉ ሲታይ ግን ቫግነር አፍሪቃ ዉስጥ የከፈታቸዉ ዘመቻዎች ባለፉት ወራት ምናልባት ዓመታት በነበሩበት ሁኔታ መቀጠላቸዉ አይቀርም።»

የቫግነር ወታደሮች ለማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ለፋዉስቲን-አርቻንጌ ቶዉዴራ ፀጥታ ሲያስከብሩ
የቫግነር ወታደሮች ለማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ለፋዉስቲን-አርቻንጌ ቶዉዴራ ፀጥታ ሲያስከብሩምስል Leger Kokpakpa/REUTERS

                የሩሲያ የአፍሪቃን ወርቅ ትታ አትወጣም  

እርግጥ ነዉ የሩሲያዉ ፕሬዝደት ቭላድሚር ፑቲን ለፕሪጎዢን ቤተሰቦች ሐዘናቸዉን ገልጠዋል።ይሁንና ሞስኮ ባለፈዉ ሮብ በደረሰዉ የአዉሮፕላን አደጋ ፕሪጎዢን በትክክል ሥለመሞት አለመሞታቸዉ እስከ ትናንት ማታ ድረስ ግልፅ መረጃ ይፋ አላደረገችም።የቫግነር የወደፊት ሕልዉና፣ ዘመቻና በተለይ አፍሪቃ ዉስጥ የሚኖረዉ ተልዕኮን  በተመለከተም ከሞስኮ ምንም የተባለ ነገር የለም።

የፖለቲካ ተንታኝ አደሙ ከሪሙ እንደሙሉት የሞስኮ ባለስልጣናት ባይረጋግጡም ቫግነር ካለፈዉ ሰኔ አመፅ በኋላ የጎላ እንቅስቃሴ እያደረገ አይደለም።ይሕም ቡድኑ የአመራር ለዉጥ ሳይደረግበት አይቀርም የሚል ግምት አሳድሯል።ማሊ ከምዕራባውያኑ ያላትን የሻከረ ግንኙነት

«ፕሪጎዢን በፑቲን ላይ ያልተሳካ አመፅ ካደረጉ ወዲሕ ቫግነር በሚያደርጋቸዉ ወታደራዊ ዘመቻዎች ላይ ፕሪጎዢን ያደረጉት የጎላ አስተዋፅኦና ተሳትፎ ብዙ አልነነበረም።እንዲያዉ አፍሪቃ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን ሌላም ሥፍራ ተሳትፎ አልነበራቸዉም።የቡድኑን ዘመቻ የሚመሩና የሚያስተባብሩ የፑቲን የቅርብ ታማኞች ሊኖሩ ይችላሉ።»

የባማኮ-ማሊ ሕዝብ ለሩሲያ ያለዉን ድጋፍ ባደባባይ ሰልፍ ሲገልፅ
የባማኮ-ማሊ ሕዝብ ለሩሲያ ያለዉን ድጋፍ ባደባባይ ሰልፍ ሲገልፅምስል Nicolas Remene/Le Pictorium Agency via ZUMA Press/picture alliance

ቫግነርን የሚመራዉ ማንም ሆነ ማን ወይም ቫግነር ራሱ በሌላ ቢተካም ሩሲያ አፍሪቃ ዉስጥ ያላትን ጥቅም ባጭር ጊዜ ዉስጥ ለቅቃ ትወጣለች ተብሎ አይታሰብም። የቀድሞዉ የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ የምክር ቤት አባል ፔሪ ማራ እንደሚሉት ደግሞ ፕሪጎዢን ሞቱም ኖሩ ሩሲያ የማዕከላዊ አፍሪቃንና የማሊን ወርቅ ትታ አትሄድም።ሩሲያ ከቡርኪና ፋሶ፣ በቅርቡ ደግሞ ኒዠርን ከመሳሰሉ የአፍሪቃ ሐገራትም ጋር ግንኙነቷን ማጠናከሯ አይቀርም።የስልታዊና የዓለም አቀፍ ጥናት የተባለዉ የዩናይትድ ስቴትስ አጥኚ ተቋም ከሁለት ዓመት በፊት እንደዘገበዉ ማሊ በሐገሯ ለሠፈሩ የቫግነር ወታደሮች በዓመት አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ትከፍላለች።

ነጋሽ መሐመድ