1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቫግነር ግሩፕ በአፍሪቃ አሁን ያለዉ ተፅእኖ ምንድን ነው?

ቅዳሜ፣ ሰኔ 24 2015

ሩሲያ የቫግነር ቡድን አፍሪቃ ዉስጥ በመኖሩ ተመክታ ቆይታ ነበር። ይሁን እንጂ የፕሪጎዥን ያለፉት ሳምንታት ክስተቶች ቡድኑ ቀዉስ ባለባቸዉ የአፍሪቃ ሃገራት የነበረዉን እንቅስቃሴ እና ተፅዕኖ ሳያሟሽዉ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/4TIFU
Mali Bamako | Protest mit "Danke Wagner" Plakat
ምስል Florent Vergnes/AFP/Getty Images

"የሩሲያ መንግሥት እንኳን ሊቆጣጠረዉ አልቻለም"

ሩሲያ የቫግነር ቡድን አፍሪቃ ዉስጥ በመኖሩ ተመክታ ቆይታ ነበር።  ይሁን እንጂ የፕሪጎዥን ያለፉት ሳምንታት ክስተቶች ቡድኑ ቀዉስ ባለባቸዉ የአፍሪቃ ሃገራት የነበረዉን እንቅስቃሴ እና ተፅዕኖ ሳያሟሽዉ አልቀረም።

ይህ በማሊ ዋና ከተማ በባማኮ ጎዳናዎች የሚታይ ሆንዋል። ከሦስት ዓመት ገደማ በፊት የመንግሥት ግልበጣ ያደረጉት ባለሥልጣናት በሳህል ግዛት የነበረዉን የፀጥታ ኃይል በመቀየር እና ከፈረንሳይና ከምዕራባውያን አጋሮች በመነጠል ሩስያን ይዘዉ ፖለቲካዊ ለውጥ ማድረግ መጀመራቸዉ ይታወቃል።

ዜጎች የቫግነር ቡድን ወደ አገሪቱ መግባትን በደስታ ነበር የተቀበሉት። ማሊ በቅርቡ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሰዉን የተመድ ተልዕኮ አላራዝምም ማለትዋም አይዘነጋም። ባለፈዉ ሰሞን የቫግነር ቡድን መስራች ይቭጊኒ ፕሪጎዥን ወታደሩን አሰልፎ ወደ ሞስኮ  ንቅናቄዉን ጀመርኩ ባለበት ቅፅበት ኃይሉ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ግልጽ የሆነ የሐሳብ ልዩነት እንዳለዉ ይፋ ሆኖ ወጥቷል።   

"የሩሲያ መንግሥት እንኳን ሊቆጣጠረዉ አልቻለም" ሲል ለዶቼ ቬለ የተናገረዉ የቫግነር ቡድን አባል ነዉ።

Wagner-Chef Prigoschin behauptet in Telegram Video die Einnahme von Bachmut
የቫግነር አለቃ ፕሪጎዢንምስል TASS/dpa/picture alliance

"አሁን ምን ማድረግ ነዉ ያአለብን? ይህ ሰራዊት ቁጥጥር ዉስጥ ሊገባ እንደማይችል የሚያሳይ ነዉ። ይህ ደግሞ ለኛ በጣም አደገኛ ነዉ። ማሊ የቫግነር ቡድን እኛን ለመጠበቅ እንደሚመጣ ተስማምታለችል። አዲሷ አጋራችን ሩሲያ አሁን ከቡድኑ ጋር ግጭት ላይ ከሆነች ሁኔታዉ ለኛ አስፈሪ ነዉ የሚሆነዉ።"

ክሬምሊን የፕሪጎዥኒንን አመፅ ዝቅ አድርጎ በማስቀመጥ ሞስኮ በአፍሪቃ ያላትን ቀጣይነት ለማሳየት ጥረት እያደረገች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ አስተያየት ሰጥተዋል ። ቡድኑ በማሊ እና በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ጥሩ ስራ እንደሚሰራ ላቭሮቭ ባለፈዉ ሰኞ ለሩሲያዉ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን RT ላይ ቀርበዉ ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአፍሪቃ በቫግነር ሥራ እንደሚቀጥል በድጋሚ አስታዉቀዋል።

ይሁንና ሁለት ቀናት ቆየት ብሎ ይህ የሰርጌይ ላቭሮቭ የንግግር ቃና በመጠኑም ቢሆን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ቀዝቀዝ ብሎ ነዉ የቀረበዉ። ቃል አቀባዩ እንደተናገሩት አፍሪቃዉያን ከቫግነር ቡድን ጋር መስራት አለመስራት የመወሰናቸው ጉዳይ የአፍሪቃ ሃገራት ኃላፊነት ነው ያሉት። የሩስያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ የሩስያ ወታደራዊ አሰልጣኞች በማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተሳትፎ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ እና፤ ይህ እንቅስቃሴ  ግን ከቫግነር ኩባንያ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለዉ ነዉ የተናገሩት።

እንዲህ ያሉ መግለጫዎች ይፋ በሚሆኑበት ጊዜ ማየት የሚቻለው ኩባንያው በአፍሪቃ የሚያደርገው እንቅስቃሴ፤ ጥሬ ኃብቶች ባሉበት ሲሆን፤ የቫግነር ቡድን ንግዱን ይቆጣጠራል። ለቭላድሚር ፑቲን መንግሥት አካባቢዉ ላይ መቀጠሉ ምንም ጥያቄ የለውም ሲሉ የተናገሩት የቀድሞው የማዕከላዊ አፍሪቃ የፓርላማ አባል ዣን-ፒየር ማራ ናቸዉ።

"ጦርነቱን በገንዘብ ለመደገፍ የማዕከላዊ አፍሪቃ ወርቅ፣ የማሊያ ወርቅ ያስፈልጋል። ስለዚህ ምንም ነገር የሚለወጥ ነገር አይኖርም። ተዋናዮች የቀደሙት ይሁን ወይም አዲስ ስለመሆናቸው አሁን ምንም ግልፅ የሆነ ነገር የለም።"

በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ (CAR) ከአስርት ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ በፕሬዝዳንት ፋውስቲን አርቼንጅ ቱዋዴራ ስር የካቲት 2019 ዓ.ም. በሃገሪቱ መጠነ ሰፊ የሰላም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ የቫግነር ቡድን አካባቢዉ ላይ ብዙ ቦታዎችን እየደረሰ ነዉ።  ይህን በተመለከተ በርካታ ታዛቢዎች እንደሚሉት አካባቢዉ ላይ ብዙ አትራፊዎች ዘልቀው ገብተዋል። ለምሳሌ በነዳጅ ዘይት ዘርፉ ወይም - በማሊ - በወርቅ ማዕድኑ ዘርፍ ላይ ይገኛሉ። አንድ ካናዳዊና አንድ የደቡብ አፍሪቃ የማዕድን ኩባንያ ፈቃዳቸውን ተነጥቀዉ፤ አንድ ለሩሲያ ቅርበት ያለዉ ማላጋሲ የተባለ ኩባንያ አዲስ ፈቃድ ይዟል ።

ከዚህ ሌላ ከ2018 ወዲህ በመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ቱአዴራ በቫግነር ወታደሮች ጥበቃ ሥር ነዉ የሚገኙት ። የፕሬዚዜዳንቱ ለረጅም ጊዜ የቅርብ አማካሪ ከቫግነር ቡድን መስራቹ ከፕሪጎዥን ጋር የቅርብ ትስስር የነበረው ሰው ነዉ።

 Zentralafrikanische Republik Denkmal zu Ehre der "Wagner-Gruppe" in Bangui
የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሃውልት በባንግዊ ለ«ቫግነር ግሩፕ» ክብር ምስል Barbara Debout/AFP

የቀድሞው ሚኒስትር እና "ለአፍሪካ ፑቲን አያስፈልጋትም " የተሰኘዉ መፅሐፍ ደራሲ አድሪየን ፑሱ ፣ ከ ዶቼ ቬሌ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ  "ፕሬዚዳንት ቱዋዴራ የቫግነር ታጋች ናቸው፣ ይህንንም እራሳቸዉ ያውቁታል" ሲሉ ተናግረዋል።  

ቫግነር በአፍሪቃ የጀመረዉ እንቅስቃሴ ቀጣይነቱ እንዴት ይሆን?  ብዙ ነገሮች እንደሚያመለክቱት ግንኙነቱ በጣም አትራፊ እና ሞስኮ ልትተወው የማትችለዉ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ አለ ። በሩሲያና በአፍሪቃ መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ጥናት ያደረጉት የታሪክ ጸሐፊዋ ኢሪና ፊላቶቫ የቫግነር ኩባንያን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ ኩባንያዉ ስሙን በመቀየር አልያም በዝያዉ በስሙ ንዑስ መረብ በመዘርጋት እንቅስቃሴዉን ያጠናክራል። በሌላ በኩል ወታደራዊ ቡድኑ እጣ ፈንታ የወደቀዉ በፕሪጎዢን አለቃ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ይሆናል።  

አዜብ ታደሰ / ፊሊፕ ሳንድረር

ሸዋዬ ለገሠ