1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“ሠላም ከሌለ ኮርማም ቢታረድ አይጣፍጥም” በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃይ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 27 2016

በግጭት ምክንያት መረጋጋት በራቃቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ከሠላም እጦት ባሻገር የሸቀጦች ዋጋ መናር ይፈትናቸዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የኪረሙ፣ የቱሉ ቦሎ፣ የጎሮ ዶላ ነዋሪዎች ገና ዘንድሮ ግጭት አጥልቶበት እንደደበዘዘ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4avf1
በጉጂ ዞን የተቃጠለ ተሽከርካሪ
ግጭት በበረታበት እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በተፈናቀለበት የኦሮሚያ ክልል የገና በዓል አከባበር የደበዘዘ መሆኑን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ምስል Private

የገና በዓል በኦሮሚያ ክልል ግጭት እና ዋጋ ንረት ተጭኖታል

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ከሚኖሩበትና ብዙ ህይወታቸውን ከመሩበት ቀዬያቸው በግጭት ምክኒያት ተፈናቅለው የሶስት ዓመታት የተፈናቃይነት ህይወት የመሩት አርሶ አደር አስተያየታቸውን ከሰጡን ቀዳሚ ናቸው፡፡ 

ለደህንነታቸው ሲባል ስሜ ይቆይ ብለው ሃሳባቸውን ያጋሩን እኚህ ነዋሪ ከእነሱ ዘንድ አሁን በዓል የሚታሰበው በስም ብቻ ሆኗል፡፡ “ምንም ቀዝቃዛ ነው፡፡ የበዓልም ድባብ የለም፡፡ በዚ ላይ መንገዶች በብዛት ስለሚዘጋጉ ሽንኩርት የለም፤ ሌላውም ሸቀጥ ስለማይገባ በዓሉን አስቸጋሪ አድርጎብናል” በማለት የጸጥታው ስጋት በህይወታቸው ሁሉ ፈታኝ እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡

“አስከሬኑን አቃጥለው አመድ ነው ሰብስበን የቀበርንው” ሙሽራ ልጃቸው በታጣቂዎች የተገደለባቸው አባት

አርሶ አደር አስተያየት ሰጪው እንደወጉ በአውደ ዓመት ሰው እንደየአቅሙ በግና ቅርጫን ጨምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ድባቡ ይደምቅ ነበር፡፡ ከሶስት ዓመታት በፊት ከመተዳደሪያቸው ግብርና በግጭት ለተፈናቀሉት አርሶ አደር ግን ይህ በቢሆን የቀረ ሆኖባቸዋል፡፡

እንደ ሰማይ ርቆ የናረው ኑሮ እንኳን በዓል ማክበር ነገን የሚያስናፍቅ ብርቱ ፈተና ደቅኗልም በማለት ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል፡፡ “እርሻ ካቆምን ሶስት ዓመት ነው፡፡ ምንም የሚላስ የሚቀመስ የለንም፡፡ ከሌላ ቦታ የሚመጣው ሸቀጥማ በታም እየተወደደ ነው” ብለዋል፡፡

የወለጋ ተፈናቃዮች ሮሮ

አሰርተያየት ሰጪው ከምንም በላይ የራቀንና የናቀቀን ሉትንም ሲያስረዱ “ከሁሉም በላይ እኛ የምንጓጓለት እና የሚናፍቀን ሰላም ነው” ብለዋል፡፡ ያለ ሰላም የሚከበር በዓልም ሆነ ደስታ ባዶ ነው ሲሉም ሃሳባቸውን አከሉ፡፡

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ
በግጭት የተፈናቀሉ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪ “ሠላም ከሌለ ኮርማም ቢታረድ አይጣፍጥም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል Privat

በኦሮሚያ በጸጥታው ከሚፈተኑ አከባቢዎች ሌላው የደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን በቾ ወረዳ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከሰሞኑ እንኳ በርካታ ተሽከርካሪዎች በሌሊት በዚያው ሲያልፉ በደፈረሰው የጸጥታ ሁኔታ ጥቃት ደርሶባቸው ጉዳት ማስተናገዳቸው አይዘነጋም፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የቱሉ ቦሎ ከተማ ነዋሪን እንቅስቃሴው እና የበኣል ዋዜማ ምን ይመስላል ብለን ጠየቅናቸው፡፡ እሳቸውም ተሸከርካሪዎች ከቀን ውጪ እንደወትሮ በሌሊት እንደማይንቀሳቀሱ አስረድተው የበዓሉንም ድባብ እጅግ የቀዘቀዘ ሲሉ መልሰዋል፡፡

“ተሸከርካሪዎች ቀን ቀን ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ግን ከሰሞኑ በቀንም ቢሆን እንቅስቃሴው ቀንሶ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ትንሽ ደህና እቅስቃሴ አለ፡፡ ይሁንና የበዓሉ ድባብ እጅግ ቀዝቃዛ ነው፡፡ ምንም ደስ አይለም” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በቅርቡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዘረጋሁ ባለው የአስተዳደር መዋቅር ከፍተኛ አለምጋጋት በተፈጠረበት ምስራቅ ቦረና እና ጉጂ ዞን አዋሳን ወረዳ በሆነው ጎሮዶላ የሚኖሩት አስተያየት ሰጪ ጸጥታውና በዓሉን በማስመልከት ሃሳባቸውን ካጋሩን ናቸው፡፡ ዱሬቲ ባነታ የተባሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ የጸጥታው ይዞታ በዓሉን ከማደብዘዝ አልፎ ህይወትን ፈታኝ አድርጎብናልም በማለት ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ አስከባሪዎች
መከላከያ ሠራዊት እና የኦሮሚያ ጸጥታ አስከባሪዎች ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ የገቡበት ግጭት እስካሁን መፍትሔ አላገኘም። ምስል Eric Lafforgue/IMAGO

“በዚህ በዓል በኛ ዘንድ የሚከወን የበኣል ዝግጅት እና መንፈሱ የለም፡፡ እነ አሁን የክርስትና እምነት ተከታይ ነኝ፡፡ ግን ባለው የጸጥታ ችግር ምንም የበዓል ስሜትም አይሰማኝም፡፡ መንግስት በሰላም እየኖርን እያለን ነው ድንገት ያላሰብነውን መዋቅር ዘረጋሁ በሚል ሰላማችን የጠፋው፡፡

ይህን ተከትሎ በተፈጠረው የህዝብ ቅሬታ ሰላማችን በብዙ ተፈትኗል፡፡ እናም እኛ ጋ ምንም የበዓል ስሜት የለም አሁን፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ በዓሉን ማክበርም አንችልም” በማለት ነው አስተያየታቸውን ያጋሩን፡፡

በኦሮሚያ የቀጠለው የጸጥታ ስጋት

በግጭት ምክኒያት በአውደ ኣመት በዓላቱ በህይወት ስለመቆየት ብቻ ስለሚየሰስቡ ጸጥታ በደፈረሰባቸው በነዚህ አከባቢዎች ወጥቶ መግባቱም ፈታኝ ነውና በዓላት አይደምቁም፡፡ የማህበረሰቡ ትልቁ መሻትም የዘንድሮን አልፎ ስለከርሞ በጎ ነገር ማሰብ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆነው ግን በዓሉን ለሚያከብሩ የእንኳን አደረሳችሁ በጎ ምኞታቸው አልተገታም፡፡

ሥዩም ጌቱ 
እሸቴ በቀለ