1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩክሬን የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት በኢትዮጵያ

ዓርብ፣ ኅዳር 16 2015

አራት የተለያዩ ሲቪል ተቋማትን የወከለ አንድ የዩክሬን የልዑክ ቡድን ኢትዮጵያን ውስጥ ከትናንት ጀምሮ ለልዩ ልዩ ተቋማት እና ግለሰቦች ገለፃ እየሰጠ ውይይትም እያደረገ ነው። የልዑክ ቡድኑ ለአፍሪቃ ኅብረት፣ ለመገናኛ ብዘኃን እና ለልዩ ልዩ ማኅበራት ማብራሪያ ሰጥቷል።

https://p.dw.com/p/4K3cP
BdTD Ukraine-Krieg Kiew | Frau mit Getreideähren
ምስል Ceng Shou Yi/NurPhoto/IMAGO

«መላው ዓለም እየተጎዳ መሆኑ ይታወቅልን» ዩክሬን

አራት የተለያዩ ሲቪል ተቋማትን የወከለ አንድ የዩክሬን የልዑክ ቡድን ኢትዮጵያን ውስጥ ከትናንት ጀምሮ ለልዩ ልዩ ተቋማት እና ግለሰቦች ገለፃ እየሰጠ ውይይትም እያደረገ ነው። የዩክሬን የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን እና የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ተቆርቋሪ ድርጅቶችን እንዲሁም የንግድ ማሕበራትን ያካተተው ይሄው ልዑክ ለአፍሪካ ሕብረት፣ ለመገናኛ ብዘኃን እና ለልዩ ልዩ ማሕበራት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጦርነት ያስከተለውን ውድመት ፣በዚህ ምክንያት ዓለም ላይ በምግብ እጥረት፣ በዋጋ መናር ብሎም በኃይል አቅርቦት መታጎል ደረሰ ያለውን ዘርዝሮ እያስገነዘበ ነው። የልዑክ ቡድኑ ለአፍሪቃ ኅብረት፣ ለመገናኛ ብዘኃን እና ለልዩ ልዩ ማኅበራት ማብራሪያ ሰጥቷል። በማብራሪያውም፦ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ጦርነት ስላስከተለው ውድመት፣ በዚያም ዓለም ላይ በምግብ እጥረት፣ በዋጋ መናር ብሎም በኃይል አቅርቦት መታጎል አደረሰ ስላለው ችግር  ገለጣ አድርጓል።

የዩክሬይን ጦርነት

የልዑካን ቡድኑ የሩሲያ ፖለቲከኞች በዩክሬን ላይ ፈፅመውታል ላሉት ወንጀል በአሁኑ ወቅት ተጠያቂ ሊያደርጋቸው የቻለ ዓለም አቀፍ ተቋም አለመኖሩ እንዳሳዘናቸውና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ሁሉም ለዩክሬን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቋል። የልዑክ ቡድኑ ከዚህ ቀደም ብሎ በኬንያ ፣ በናይጀሪያ እና በጋናም ተመሳሳይ ጉብኝት አድርጓል። 

ፕሮፌሰር ኦሌክሲ ሀራን የዩክሬን ምሁራንን ወክለው ኢትዮጵያ የተገኙ ሰው ናቸው። በተለይ የማኅበረሰባዊት ኢትዮጵያ ዘመን አስተዳደር ታሪክ ወዳጅ እንደሆኑ ይናገራሉ። ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት የጀመረችው ዛሬ ሳይሆን ከ1994 እንደጎርጎረሲያኑ አቆጣጠር ጀምሮ ነው ይላሉ። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባል የመሆን ጥያቄ መነሳት የጀመረው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በዚያ የተፈጠረው ሥጋት ማየሉን ተከትሎ ነውም ይላሉ።

Irland | Ankunft eines Getreide-Frachtschiff aus der Ukraine
እህል የጫነች የዩክሬን መርከብ በጥቁር ባሕር ላይ ኦዴሳ ወደብን ለቅቃ ስትጓዝምስል Clodagh Kilcoyne/REUTERS

«የፑቲን ሀሳብ ዩክሬንን አንኮታኩቶ ትቢያ ማድረግ ነው። የቀድሞ የራሺያን ግዛት ዳግም የመመለስ የፀና ፍላጎት አለው። ዩክሬን ራሷን የቻለች ሀገር ሆና መቀጠል የለባትም ብሎ በግልጽ አውጇል። የሩሲያ አካል ናት ነው ያለው። ይህ በዲሞክራሲ እና በአምባገነን መካከል የሚደረግ ውጊያ ነው። ፑቲን አምባገነን ነው።»

ሩሲያ በዩክሬን ቁልፍ የኃይል እና ሌሎች መሠረተ ልማቶች ላይ የምታደርገውን የአየር ድብደባ ቀጥላለች። ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ይህንን የተባበሩት መንግሥታት እንዲያስቆም እየተማፀኑ ይገኛሉ። ፕሮፌሰር ኦሌክሲ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተጓዙባቸው የአፍሪካ ሀገራት ይህንን ሰቆቃ በስልካቸው የያዙትን የሀገራቸውን የቀደመ እና ዛሬ ወድሞ የሚያሳይ ምስል ጭምር በማሳየት ሁሉም ከሀገራቸው ጎን እንዲቆም ጠይቀዋል።

«ከምግብ ዋስትና ደህንነት መረጋገጥ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ችግር አለ። ምክንያቱም ዩክሬን ከዓለም ዋነኛ የጥራጥሬ እና የሱፍ አምራች ሀገሮች አንዷ ናት። ከኒውክሌር ደህንነት ጋርም ችግር አለ። ምክንያቱም ራሺያ በአውሮጳ ግዙፉን የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በረዢያን ተቆጣጥራለች። ይህ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ እናውቃለን። የኒውክሌር ደህንነት ስምምነትን ጥሰዋል። ይህ በጣም አደገኛ ነው። ምክንያቱም የራዲዮ አክቲቭ ካፈተለከ ከፍተኛ ብክለት ይከሰታል። ለበርካታ ሰዎችም ተጨማሪ የምግብ እጥረት አደጋ ይደቅናል። ለዚህም ነው የእኛ ብቻ ጦርነት ያልሆነው። ለፍትሕ እየታገልን ነው። ነገር ግን ደግሞ ለዓለም ሥርዓት መጠበቅም እየተዋጋን ነው የምንገኘው።» 

የዩክሬን ጦርነት ለአውሮጳ ኅብረት ዳፋ

ኦሌክሳንድራ ድሪክ በዩክሬን የሰብዓዊ መብት ባለሙያ እና ዋና ከተማ ኬቭ ተቀማጭ የሆነ የሲቪል ድርጅት ስሉጥ ሀሳብ አራማጅ ናት። በጦርነቱ የሀገሯ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ መላው ዓለም እየተጎዳ መሆኑ ይታወቅልን ትላለች።

«እሁን እየተናገርንበት ባለው ሰዓትም ሁሉም ዩክሬናዊያን እየተሰቃዩ ነው። በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት ኢርዮጵያን ጨምሮ በ94 ሀገራት ውስጥ የሚገኙ 1.6 ቢሊየን ሰዎች ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ ምክንያቶች በተፈጠሩ ሌሎች አባባሽ ችግሮች በቀጥታ ተጎጁ ሆነዋል። እያሉ ያሉትም የምግብ እጥረትን ጨምሮ የኑሮ ውድነት ማሻቀቡን፣ የገንዘብ እጥረት እና የኃይል አቅርቦት ችግር ውስጥ መዘፈቃቸውን ነው። ይህ ምናልባትም የምግብ እጥረትን በአፍሪካ ፣ የዋጋ ግሽበትን በላቲን አሜሪካ፣ ውድቀትን በኤስያ እያስከተለ ነው። ሁሉም ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወረራ ሰለባዎች ናቸው»

Simferopol grain processing plant in Crimea
ክሬሚያ ውስጥ የስንዴ እህል በወንፊት የሚያጣራ እጅ ይታያል።ምስል Sergei Malgavko/TASS/dpa/picture alliance

ማስረጃዎች በሙሉ ግልጽ እና የሚታዩ መሆናቸውንም ጦርነቱ ያስከተለውን ውድመት በማጣቀስ በሩሲያ ተጥሰዋል ለተባሉ ብዙ ስምምነቶችን እና ሕግጋትን፣ ተፈጽመዋል ላለቻቸው ከፍተኛ ሁሉን አቀፍ ውድመት የሩሲያ የፖለቲካ እና የጦር መሪዎች እንዲጠየቁ ድጋፍ ተጠይቋል።

«በአሁኑ ወቅት የሩሲያ የፖለቲካ መሪዎች ለፈፀሙት ወረራ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ የቻለ አንድም አለም አቀፍ ተቋም የለም። ለዚህ ነው የዩክሬን መንግሥት በወረራው ወንጀል ላይ የሚያተኩር ልዩ የችሎት ፍርድ ቤት እንዲቋቋም እያራመደ ያለውን ተነሳሽነት የምንደግፈው። ምክንያቱም የጦርወንጀልን፣ በሰብዓዊነት ላይ የተቃጣ ወንጀል እና በእርግጥም የዘር ማጥፋት ወጀልን በተመለከተ በአለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ይህንን ወንጀል የሚያመረምር አካል እንደሌለ አረጋግጧል።»

ዩክሬን ባለፈው መስከረም በድርቅ በብርቱ ለተመቱት የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ 50 ሺህ ቶን ስንዴ ድጋፍ አድርጋለች። ይህንን የእርዳታ ስንዴ ለማጓጓዝ ደግሞ ሥራውን ለከወነው የተባበሩት መንግሥታት የምግብ መርሐ ግብር ፈረንሳይ ለሶማሊያ የሚላከውን፣ ጀርመን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ የገባውን ስንዴ ለማጓጓዝ እያንዳንዳቸው የ14 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርገው ነበር።

በሌላ በኩል የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት የተቀሰቀሰ ሰሞን አዲስ አበባ ቀበና ወንዝ አካባቢ በሚገኘው የሩስያ ኤምባሲ ቅጥር በር ላይ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ሩሲያ ምልምል ወታደር እየመዘገበች ነው በሚል ከሩሲያ ጎን ተሰልፈው ለመዋጋት ለመመዝገብ ለቀናት ልዩ ልዩ ወረቀትና ሰነዶችን በመያዝ ሲመላለሱ ነበር።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ