1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እኤአ ሰኔ 20 የዓለም የስደተኞች ቀን

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2016

በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር በየዓመቱ ሰኔ 20 የሚከበረውን የዓለም የስደተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን መብት ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያረጋግጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጠየቀ።

https://p.dw.com/p/4hJhV
ፎቶ ከማኅደር፤ የሱዳን ስደተኞች
ቻድ ውስጥ የተጠጉት የሱዳን ስደተኞች ፎቶ ከማኅደር፤ የሱዳን ስደተኞች ምስል AP/picture alliance

የዓለም የስደተኞች ቀን

 

በጎርጎሪዮስ የዘመን ቀመር በየዓመቱ ሰኔ 20 የሚከበረውን የዓለም የስደተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን መብት ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያረጋግጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጠየቀ። ስደተኞች ከጥገኝነት፣ ከደህንነት እና ከሰነዶች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ አሁንም ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል ያለው ኢሰመኮ፣ የዘፈቀደ እሥራት ሁኔታዎች፣ ፍትሕ እና መሰረታዊ ፍላጎቶችን የማግኘት መብት ፣ የሰብአዊ እርዳታ፣ ዘላቂ መፍትሔዎች እና መልሶ ማቋቋምን የተመለከቱ ጉዳዮች ስደተኞች ለችግር ከሚጋለጡባቸው መካከል መሆናቸውን ጠቅሷል። በኢኮኖሚም ይሁን በፖለቲካ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ በርካታ ስደተኞች መኖራቸውን የገለፀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰላም ሰርተው መኖር እንዲችሉ መንግሥት ከአጋሮች ጋር እንደሚሠራ ገልጿል። ዓለም በየዓመቱ ሰኔ 20 ከግጭት ወይም ስደት ለማምለጥ ከትውልድ ሀገራቸው ለመሰደድ የተገደዱ ሰዎችን ጥንካሬ እና ድፍረት ለማክበር የስደተኞች ቀን ይታሰባል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች

ኢትዮጵያ በዋናነት ጋምቤላ ውስጥ የተጠለሉ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የየመን፣ በአዲስ አበባ በብዛት የሚኖሩ የኤርትራ እንዲሁም ጎንደር ውስጥ የሱዳን ዜጎች የሆኑ ስደተኞችን ተቀብላ ታኖራለች። አብዛኞቹ ስደተኞችበስደተኞች ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን በተወሰነ ቁጥርም ቢሆን በከተማ አካባቢ መጠጊያ አግኝተው የሚኖሩ መኖራቸውን ኢሰመኮ ገልጧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚመለከታቸው ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሚያደርገውን «ከፍተኛ ጥረት» እንደሚገነዘብ ያስታወቀው ኮሚሽኑ፣ ስደተኞች አሁንም አንዳንድ ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል ብሏል፤ ዛሬ ባወጣው መግለጫ።

የጥገኝነት ጥያቄ ፣ የደህነት፣ ሁኔታ፣ ሰነድ የማግኘት ጉዳይ የሰብአዊ እርዳታ እና የዘላቂ መፍትሔ ጉዳዮች ተጠቃሽ መሆናቸውም ተመላክቷል። የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ይህንኑ ዛሬ የሚከበረውን የስደተኞችን ቀን በማስመልከት ለዶቼ ቬለ በሰጡት ማብራሪያ፤ «የሰብዓዊ መብቶቻቸውን በተለይ ደግሞደህንነት እና ሴኪዩሪቲን በተመለከተ ያሉ ክፍተቶችን በመሸፈን ስደተኞች ምቹ አካባቢን፣ ተቀባይ ሀገር ማመቻቸት በሚለው መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲፈጥር» ጥሪ ማድረጋቸውን ገለፀዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የባንግላዴሽ ስደተኞች
ባንግላዴሽ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ ለስደት የዳረጋቸው ወገኖችፎቶ ከማኅደር፤ የባንግላዴሽ ስደተኞች ምስል Zakir Hossain Chowdhury/picture alliance/AA

የስደተኞች ቀን የሚከበርበት ምክንያት

በየዓመቱ በጎርጎሪዮሳዊው የዘመን አቆጣጠር ሰኔ 20፣ ዓለም ከግጭት ወይም ስደት ለማምለጥ ከትውልድ ሀገራቸው ለመሰደድ የተገደዱ ሰዎችን ጥንካሬ እና ድፍረት ያከብራል። በዚሁ ዕለት ስደተኞች ከሀገራቸው ለመሰደድ የተገደዱባቸው ጉዳዮች ማለትም መብቶች፣ ፍላጎቶች እና ሕልሞች እንዲከበሩ ግፊት ይደርጋል። 

ሃገራት ሰዎች በተለያየ ችግር ምክንያት ለስደት ሲዳረጉ በሮቻቸውን ክፍት እንዲያደርጉ እና የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ግምት ውስጥ እንዲያስገቡም ውትወታ ይደረጋል።

ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ቀውስ ውስጥ መግባቷን ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ምዕራብ ጎንደር ዞን የተጠለሉ የሀገሪቱ ስደተኞች ችግር እየገጠማቸው መሆኑን ደጋግመው በመግለጽ ላይ ናቸው። እሑድ ዕለት ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ አንድ ሱዳናዊት ስደተኛ መገደላቸው ተዘግቧል። በዚሁ ዞን ውስጥ ባሉት አውላላ እና ኩመር የተባሉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች የነበሩ 1,300 ያህል የሱዳን ስደተኞች የፀጥታ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የምግብ እና የቦታ ችግር እንደገጠማቸው በመግለጽ ከመጠለያቸው ወጥተው ሜዳ ላይ ስለመሆቸውም ቀደም ብሎ ተዘግቧል። ይህንን በተመለከተ ዛሬ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢዩ ተድላ ተከታዩን ምላሽ፤ በኢኮኖሚም ይሁን በፖለቲካ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ የገቡ በርካታ ስደተኞች መኖራቸውን በመግለጽ፤ «በሰላም ሠርተው መኖር እንዲችሉ መንግሥት ከአጋሮቹ ጋር እንደሚሠራ አመልክተዋል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የሩሂንጊያ ስደተኞች
ሕንድ ውስጥ የተጠለሉት የሩሂንጊያ ሙስሊም ስደተኞች ፎቶ ከማኅደር፤ የሩሂንጊያ ስደተኞች ምስል Amarjeet Kumar Singh/AA/picture alliance

ኢትዮጵያ ውስጥ የተጠለሉ ስደተኞች ከዚህ በፊት ምን ገጠማቸው?

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን፣ በጋምቤላ ከ30 ያላነሱ ስደተኞች በረሃብና በምግብ እጦት፣ ጦርነት ሸሽተው በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ሱዳናዊያን ስደተኞች መካከል ደግሞ ዘጠኝ ያህሉ በኮሌራ ወረርሽኝ መሞታቸውን ከወራት በፊት አስታውቆ ነበር።

በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተምላሾች አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ስደተኞች መኖራቸውን፣ ከእነዚህም ውስጥ 80 ሺህ ያህሉ አዲስ አበባ ውስጥ እንደሚገኙ በቅርቡ ለዶቼ ቬለ መግለፁ ይታወሳል።

በአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያ እንዲሁም ሱዳን በውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት እና የፖለቲካ ሁኔታ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እስራኤልና ሀማስ ጦርነት፣ አውሮጳ በራሺያ እና ዩክሬን አላባራ ባለው አውዳሚ ጦርነት ምክንያት ስደተኝነት እየጨመረ መሆኑ ተዘግቧል።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ