1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ስደተኞች ወደ 3ኛ አገር መሄድ እንደሚፈልጉ ገለፁ

ሰኞ፣ ግንቦት 26 2016

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ከአውላላና ኩመር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከወጡ ከአንድ ወር በላይ ያስቆጠሩት የሱዳን ስደተኞች ወደ 3 ኛ አገር የመውጣት ፍላጎት እንዳላቸው ተናገሩ፡፡ ስደተኞቹ የርሀብ አድማ ላይ እንደሆኑ ቢናገሩም፣ የአካባቢው ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ግን ወደመጠለያ ጣቢያ መጥተው ምግብ ለመውሰድ አልፈለጉም ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4gaQ5
ፎቶ ማኅደር፤ ጦርነት ያፈናቀላቸዉ የሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያ
ፎቶ ማኅደር፤ ጦርነት ያፈናቀላቸዉ የሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያ ምስል Amanuel Sileshi/AFP

የሱዳን ስደተኞች ወደ 3ኛ አገር መሄድ እንደሚፈልጉ ገለፁ

የሱዳን ስደተኞች ወደ 3ኛ አገር መሄድ እንደሚፈልጉ ገለፁ

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ከአውላላና ኩመር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከወጡ ከአንድ ወር በላይ ያስቆጠሩት የሱዳን ስደተኞች ወደ ሶስተኛ አገር የመውጣት ፍላጎት እንዳላቸው ተናገሩ፡፡ ስደተኞቹ የርሀብ አድማ ላይ እንደሆኑ ቢናገሩም፣ የአካባቢው ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ግን ወደመጠለያ ጣቢያ መጥተው ምግብ ለመውሰድ አልፈለጉም እንጂ በርሀብ አድማ ላይ አይደሉም ብሏል፡፡ አዲስ የመጠለያ ጣቢያ ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አስታውቋል፣ ይሁንእንጂ ተመሳሳ ችግር ጋጥመናል በሚል ስደተኞቹ ከአሁኑ ወደ መጠለያው እንደማይገቡ እየተናገሩ ነው፡፡

ከአሳለፍነው  ወር መጨረሻ ጀምሮ ከአውላላና ከኩመር የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የፀጥታ፣ የንፁህ መጠጥ ውሀ፣ የምግብና የቦታ ችግር አለብን በሚል ወደ 1ሺህ 300 የሚሆኑ የሱዳን ስደተኞች ከመጠለያቸው ወጥተው አንድ ኪሎሜትር  ሜዳ ላይ እንደሆኑ ስደተኞች ቀደም ሲል ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡

የሚመለከታቸው አካላት የስደተኞችን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት እንዳደረጉ ቢገልፁም እስካሁን ተጨባጭ ውጤት እንዳልተገኘ ስደተኞቹ ገልጠዋል፡፡

አብዱሰመድ የተባለ ከመጠለያ ጣቢያው የወጣ ስደተኛ ስደተኞቹ በርሀብ አድማ ላይ መሆናቸውንና አዲስ መጠለያ ቢገነባም ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮ ሊቃለሉ ስለማይችሉ ወደ መጠለያው እንደማየሄዱ ጠቁሞ ወደ ሶስተኛ አገር መሄድ እንደሚፈልግ አስረድቷል፡፡

“ችግሩ አሁንም እንደቀጠለ ነው፣ ማንም መጥቶ ችግሮቻችን አልሰማልንም፣ አልፈታልንምም፣ የርሀብ አድማው እንደቀጠለ ነው፣ ስደተኞች ወደ መጠለያ ጣቢያው ሄደው እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ አይደሉም፣ አዲስ ይሰራል ወደሚባለው መጠለያም አንገባም፣ ተመሳሳይ ክልል፣ ተመሳሳይ አካባቢ ውስጥ ነው ይገነባል የተባለው መጠለያ፣ በመሆኑም ተመሳሳይ ችግሮች አሁንም ያጋጥሙናል፣ ፍላጎታችን በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር አካባቢ መስፈር ነው፣ ካለዚያ ደግሞ ከኢትዮጵያ መውጣት ነው፡፡” ብሏል፡፡

ይዘዲን የተባለ ሌላ ስደተኛም የርሀብ አድማው መቀጠሉን ጠቁሞ በአካባቢው ለመቆየት የሚያስችል ሁኔታ ስለሌለ  ወደሌላ ሶስተኛ አገር ለመሄድ እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡

“ስደተኞቹ ከ10 ቀናት በላይ በርሀብ አድማ ላይ ናቸው፣ ችግሮቻችን ለሚመለከታቸው ሁለም አካላት ብናደረስም የሰማን ግን የለም፣ ወደሌላ ሶስተኛ አገር መሄድ እንፈልጋለን፣ ከኢትዮጵያ መውተጣት ነው ፍላጎታችን፡፡” ሲል ተናግሯል፡፡

የአካባቢው ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ታምራት ደምሴ በበኩላቸው ስደተኞቹ ሌላ መጠለያ ይገንባልን ባሉት  መሰረት አዲስ መጠለያ ለመገንባት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፣ ሆኖም ከወዲሁ “ወደቦታው አንሄድም” የሚል አዝማሚያ አለ ነው ያሉት፡፡ መጠለያው ተገንብቶ “አንገባም” ካሉ ቀጣዩ እርምጃ ወደፊት ይታያል ብለዋል፡፡

“... እሱን አስበናል፣ መጠለያ ለመቀየር ሥራ እየተሰራ ነው ያለው፣ ወደ አዲሱ መጠለያ አንሄድም ሳይሆን የትም አንሄድም ነው ያሉት፣ ይህን ሊሉ እንደሚችሉ ግምቱ አለን፣ ከእኛም ሰዎች ጋር፣ ከመንግስትም ጋር ተማክሮ ምን ዓይነት እርማጃ እንውሰድ የሚለው ነገር የሚሆነው መጠለያ ጣቢያው ከተዘጋጀ በኋላ ሂደው እንዲገቡ ይነገራቸዋል፣ ለማግባባት ይሞከራል፡፡”

ስደተኞቹ “የርሀብ አድማ  አድርገናል” የሚሉትንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ሰሞኑን የርሀብ አድማውን ስለማረጋገጡ ያወጣውን መግለጫ አቶ ታምራት አይቀበሉትም፡፡

ፎቶ ማኅደር፤ ጦርነት ያፈናቀላቸዉ የሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያ
ፎቶ ማኅደር፤ ጦርነት ያፈናቀላቸዉ የሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያ ምስል Amanuel Sileshi/AFP

“ የርሀብ አድማ አይደለም ዝም ብለው ሲያስወሩ ነው፣ ... እህሉን አምጥታችሁ እኛው ጋ አምጥታችሁ ስጡን ነው፣ እኛ ደግሞ ወደ መጠለያው ተመልሳችሁ ውሰዱ ነው፣ እርቀው ሄደው እንደፈለግን እንሆናለን ባሉበትና ህጋዊ ባልሆነ ቦታ ስርጭት አናደርግም ነው፣ ስርጭት የሚካሄደው ህጋዊ በሆነ ቦታ ላይ ነው፣ መጥታችሁ ውሰዱ ነው ህጋዊ በሆነው ቦታ” ሲሉ የርሀብ አድማ ተባለውን ስሞታ ሀሰት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ስደተኞቹ ከኢትዮጵያ መውጣት እንፈልጋለን ያሉትን ጉዳይ የተጠየቁት አቶ ታምራት አንዳንድ ልዩ ተልዕኮ ያላቸው ስደተኞች “ኢትዮጵያ ስደተኞችን መቀበል አትችልም” ለማሰኘት ተፅኖና ግፊት በማድረግ ጥያቄው መነሳቱን አስታውሰው ግን ይህ በኢትዮጰያ መንግስት የሚወሰን አይደለም ነው ያሉት፡፡

“ከዚህ በፊት ወደ ሶስተኛ አገር እንሂድ የሚል ነገር አንስተው ነበር ይህ ደግሞ የራሱ የሆነ ሂደት አለው ያንን ደግሞ የሚያደርገው የኢትዮጵያ መንግስት አይደለም፡፡” ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን በመጠለያ ጣቢያ የወጡ ስደተኞች ጉዳይ እንዳሳሰበው ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ አመልክቷል፣ የፀጥታው ሁኔታ በእጅጉ እየተሸሻለ እንደሆነና ዘላቂ መፍትሔ ለመፈለግምከአካባቢው የመንግስት መዋቅርና ለሌሎች አጋር አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብሏል፡፡

ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን(UNHCR)  የኢትዮጵያ ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ ሉክሬዛ ቪቶሪ ያደረግሁት የስልክ ጥሪ አልተሳካም፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከኡጋንዳ ቀጥሎ ከፍተኛ  ስደተኛ ያለባት አገር ናት፣ በአገሪቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች በ26  የስደተኛ ጣቢያዎች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሰ