1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንክ እና በትይዩ ገበያ

ሰኞ፣ ኅዳር 24 2016

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ «በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜ እና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ» እቅድ እንደሌለው አስታወቀ። በኢትዮጵያ አንድ የአሜሪካ ዶላር በሕጋዊ ሥርዓት እስከ 55 ብር የሚመነዘር ሲሆን በጥቁር ገበያ ግን በእጥፍ ይመነዘራል።

https://p.dw.com/p/4ZlZi
አዲስ አበባ ግዙፉ የባንክ ሕንጻ
አዲስ አበባ ግዙፉ የባንክ ሕንጻ በከፊልምስል Solomon Muchie/DW

የምንዛሪ ተመን ማሻሻያ ቢደረግ ምን ይከሰታል?

 

የውጭ ምንዛሪ ተመን በባንክ እና በትይዩ ገበያ 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ «በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ በቅርብ ጊዜ እና በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ ለማድረግ» እቅድ እንደሌለው አስታወቀ። ባንኩ በሕጋዊው የውጭ ምንዛሪ ተመንና በትይዩ ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት በከፍተኛ ደረጃ ለማጥበብ ማቀዱ ሰሞኑን መዘገቡን ተከትሎ ዛሬ ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው ማስተባበያ «ይህንን ዘገባ ተከትሎ በዋጋ ላይ የሚፈጠር ማንኛውም ጭማሪ ተቀባይነት የለውም» ሲል የምንዛሪ ተመን ማሻሻያ ውጥን እንደሌለው ገልጿል። በኢትዮጵያ አንድ የአሜሪካ ዶላር በሕጋዊ ሥርዓት እስከ 55 ብር የሚመነዘር ሲሆን በጥቁር ገበያ ግን በእጥፍ ይመነዘራል።
ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሥርዓት ውስጥ ምን አስከትሏል ያልናቸው አንድ የምጣኔ ኃብት ባለሙያ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን እያበረታታ ፣ ወደ ውጭ የሚላኩትን ምርት እና ሸቀጦች ግብይትን እያቀጨጨ ስለመሆኑ ገልፀዋል። ባለሙያው እንዳሉት ብሔራዊ በንክ በሕጋዊ የባንኮች የውጭ ምንዛሪ እና በትይዩ ገበያ ያለው የምንዛሪ ልዩነት እንዲጠብ መመሪያ ቢያወጣ ለአጭር ጊዜ እንጂ በዘላቂነት ጉዳት እንደማይኖረው ገልፀዋል። ይህ የሚሆነው ግን መንግሥት በገበያው ከፍተኛ መጠን ያለውን የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ከተቻለ ነው ሲሉ ገልፀዋል።


የትይዩ ( ጥቁር ) ገበያ ምንዛሪ ነገር 
መሃል አዲስ አበባ፣ የብሔራዊ ባንክም ይሁን የሀገሪቱ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤቶች አካባቢ የሚያልፍ ሰው ብዛት ባላቸው ወጣቶች የውጭ ሀገር ገንዘብ ይዞ እንደሆንና መመንዘር ፈልጎ ከሆነ በግልጽ ይጠየቃል። አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ110 እንዲሁም አንድ ዩሮን በ120 ብር ለመመንዘር የሚያግባቡ ሰዎች ከልካይ ያላቸው አይመስሉም። ትናንት በኢሕአዴግ ፣ ዛሬም በብልጽግና። 
 

የምንዛሪ ተመን የማሻሻል እቅድ የለኝም  ብሔራዊ ባንክ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ «በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ ለውጥ የማድረግ» እቅድ እንደሌለው ዛሬ አስታውቋል። ባንኩ ይህንን ያለው በሕጋዊ እና በትይዩ ገበያ ያለው የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ማቀዱ ሰሞኑን መዘገቡን ተከትሎ በሰጠው የማስተባበያ መግለጫ ነው። በሕጋዊ እና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የምንዛሪ ተመን በእጥፍ መራራቅ ከውጪ የሚገቡ ምርቶች በገበያው ዋጋቸው እጅግ እንዲንር አድርጓል። የምጣኔ ኃብት ባለሙያ አቶ ኢድሪስ ሰዒድ እንደሚሉት ይህ የምንዛሪ ተመን ልዩነት ኢትዮጵያ ሻጭነቷ ቀንሶ ሸማችነቷ እንዲበረታታ አድርጓል።
የምንዛሪ ተመን ማሻሻያ ቢደረግ ምን ይከሰታል ?
መንግሥት በሕጋዊው እና በትይዩ ገበያው ያለውን የምንዛሪተመን ለማጥበብ መመሪያ ቢያወጣ በአዎንታም ሆነ በአሉታ ያለውን አድደምታ ምን እንደሚሆን ባለሙያውን ጠይቀናቸዋል። «በአጭር ጊዜ በገበያው ላይ መንገጫገጭ ቢፈጥርም በረጅም ጊዜ ግን ችግሩን ወደ መስመር እንደሚያስገባው» እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል። ኬንያ በዚህ ረገድ የወሰደችውን እርምጃም በአብነት ጠቅሰዋል። 
የውጭ ምንዛሪ ጥቁር ገበያ በሀገር ላይ ምን ችግር ፈጠረ ?

ፎቶ ከማኅደር፤ አዲስ አበባ የገበያ ስፍራ
ፎቶ ከማኅደር፤ አዲስ አበባ የገበያ ስፍራምስል Seyoum Getu/DW

የመግዛት አቅሙ ወይም ዋጋው የወረደ በርካታ ገንዘብ መኖሩ በተለይ ላኪዎች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሮባቸዋል ያሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ኢድሪስ ሰዒድ ይህም በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ስለማድረጉ ገልፀዋል። ብሔራዊ በንክ በሕጋዊ የባንኮች የውጭ ምንዛሪ እና በትይዩ ገበያ ያለው የምንዛሪ ልዩነት እንዲጠብ አዲስ አሰራር ወይም መመሪያ ቢያወጣ ለአጭር ካልሆነ በቀር በረጅም ጊዜ ጉዳት እንደማይኖረው ባለሙያው አመልክተዋል። እንደ እሳቸው አባባል ይህ የሚሆነው ግን መንግሥት በገበያው ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለውን የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ ከቻለ ነው።
አሁን ኢትዮጵያ የምትገኝበት የሰላም ሁኔታ እና የኢኪኖሚው ሀብት የማመንጨት አቅም ግን ሰፊ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦ በገበያው እንዲቀርቡ ማድረግ ይቻላል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።

ሰሎሞን ሙጬ

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ