1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወሲብ ጥቃት ሰለባዎች በሱዳን

ቅዳሜ፣ ሰኔ 29 2016

«እናቴንና አክስቴን ሊተኩስባቸው ሽጉጡን ጥይት ሞላበትና አክስቴ ላይ ተኮሰ ። ሆኖም አክስቴ ከጥይቱ አመለጠች። እኔም ከርስዋ ይልቅ እኔን ተኩስብኝ አልኩት።አንቺን አልገልሽም ፤ ውጭ ያሉትን ወንድሞችሽን ነው የምገለው አለ። እኔንም በአለንጋ በዱላና በኮዳ ከደበደበኝ በኋላ አልጋ ላይ ወርውሮኝ ይደፍረኝ ጀመር።» ሀሊማ፣የሱዳን የወሲብ ጥቃት ሰለባ

https://p.dw.com/p/4hx5D
Frauen Sudan sexueller Missbrauch Vergewaltigung Symbolbild
ምስል Abd Raouf/AP/picture alliance

የወሲብ ጥቃት ሰለባዎች በሱዳን

የወሲብ ጥቃት ሰለባዎች በሱዳን

ሀሊማ (ስሟ ተቀይሮ ነው)፣ እስከምታስታውሰው ድረስ በተለያዩ የስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ ኖራለች። መጠለያ ባገኘች ቁጥር ደኅንነቷ የተጠበቀ ቢመስላትም ሌላ ጥቃት እየደረሰ በተደጋጋሚ ከነበረችባቸው ስፍራዎች ተፈናቅላለች። በየጊዜው የደረሰባት ስቃይ ለሊት እንቅልፍ ይነሳታል። ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር እርስዋና ቤተሰቦቿ በሚኖሩበት የምዕራብ ዳርፉር ግዛት ዋና ከተማ ኤል ጌኔይናና አካባቢ የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ተዋጊዎች ጥቃት ሲያደርሱ ቤቷ ውስጥ ነበረች

«ክፍሌ ውስጥ ነበር ያገኙኝ አራት ሆነው በሽጉጥ አስፈራሩኝ ፤ከመካከላቸው አንዱ አነቀኝ ሌሎቹ ክፍሉን ጥለው ወጡ። ወደ ኋላ የቀረው ደፈረኝ። ብዙ ታግዬ ነበር እንዲደፍረኝ አልፈለግኩም። ግን ደግሞ የደገነብኝ ሽጉጥ አስፈራኝ ።ከዚያ በኋላ የተሰማኝ ነገር ቢኖር ህመም ነው።»

ሰውነቷ በተለያየ ስፍራ ቢቆስልም በመጨረሻ እንደምንም ድንበር አቋርጣ ወደ ቻድ ማምለጥ ችላለች ።ይሁንና ለተፈጸመባት ጥቃት የሚያስፈልጋትን የሕክምና እርዳታ ማግኘት አልቻለችም።

ቻድ በሚገኙ የተለያዩ መጠለያዎች ውስጥም በርካታ ሴቶችና ህጻናት የወሲብ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ተናግረዋል። እነዚህ በመጠለያዎች ውስጥ የሚፈጸሙት ወሲባዊ ጥቃቶች ደግሞ እየተባባሱ ነው።  ለምንድነው ዓለም የሱዳንን የእርስ በእርስ ጦርነት ችላ ያለው?

ዘርን መሠረት ያደረገ ጾታዊ ጥቃት

ከሱዳን ድንበር አቋርጠው ከተሰደዱት አብዛኛዎቹ አድሬን በመሳሰሉ ምሥራቅ ቻድ በሚገኙ መጠለያዎች ውስጥ ነው ያሉት።  ከመካከላቸው አንዷ ሀሊማ ናት። ሀሊማ እንደምትለው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ሚሊሽያ በዋነኛነት የደፈረኝ ማሳሊት ከሚባለው ጎሳ በመሆኔ ነው ብላ ታምናለች ። ባለፈው ዓመት ቡድኑ ነዋሪዎቿን ከማጥቃቱ በፊት ከኤል ጌኔይና ህዝብ አብዛኛው የማሳላት ጎሳ ነበር። ሌላዋ በመጠለያ የምትኖረው ወጣቷ ሀዲጃ (ስሟ ተቀይሯል) የሀሊማን አመለካከት ትጋራለች። እርስዋ እንደምትለው ጥቃት የፈጸመባት ሰው የየትኛው ጎሳ አባል እንደሆነች ጠይቋት ነበር።

ሱዳንና ኢትዮጵያ ውስጥ የወሲብ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች ምልክት
ሱዳንና ኢትዮጵያ ውስጥ የወሲብ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች ምልክትምስል Nariman El-Mofty/AP/picture alliance

«ከየትኛው ጎሳ ነሽ ብሎ ጠየቀኝ። ከማሳሊት ነኝ አላልኩትም ።ይልቁንም ከፉር ነኝ ብዬ መለስኩለት  እርሱም ማሳሊት ከሆንሽ አንገትሽን ነው የምቆርጠው አለኝ።»

ከማሳሊት ጎሳ ብትሆን ግን ይገላት እንደነበር የዛተባት ይኽው ሚሊሽያ ማሳሊቶች ወደፊት በሱዳን የመሬት ባለቤት እንደማይሆኑም ነግሯታል። የወሲብ ጥቃት ሰለባ የሆነችው ሌላዋ ወጣት ሀዋ (ስምዋ ተቀይሮ ነው) ባለፈው ዓመት ሰኔ ነበር ተመሳሳይ ጥቃት የደረሰባት።ለዶቼቬለ እንደተናገረችው የፈጥኖ ደራሹ ሚሊሽያ ቤታቸው ገብቶ የ20 ዓመቷ ወጣት የአክስቷ ልጅ ላይ ተኮሰባት ከዚያም እናትና አክስቷን መደብደብ ጀመረ ፤በዚህም አላበቃም።

«እናቴንና አክስቴን ሊተኩስባቸው ሽጉጡን ጥይት ሞላበትና አክስቴ ላይ ተኮሰ ። ሆኖም አክስቴ ከጥይቱ አመለጠች። እኔም ከርስዋ ይልቅ እኔን ተኩስብኝ አልኩት ።እሱ ግን አንቺን አልገልሽም ፤ ውጭ ያሉትን ወንድሞችሽን ነው የምገለው አለ። እኔንም በአለንጋ በዱላ እና በኮዳ ከደበደበኝ በኋላ አልጋ ላይ ወርውሮኝ ይደፍረኝ ጀመር።»

ሀዋ ከቀናት በኋላ ነበር ሆስፒታል ያገኘችው። ቀዶ ህክምና ያስፈልጋት ነበር ከጥቃቱ በኋላ አሁንም ቢሆን ስትራመድ ህመም ይሰማታል። የነዚህ የወሲብ ጥቃት ሰለባዎች ታሪኮች የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ  ሂዩመን ራይትስ ዋች በሰነዳቸው በርካታ ተመሳሳይ ባህርይ ባላቸው ወንጀሎች የሚደገፍ ነው። በምዕራብ ዳርፉር በማሳሊት ጎሳ አባላት ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ወደ ዘር ማጥፋት ሊደርስ እንደሚችል ድርጅቱ አስጠንቅቋል። እነዚህን ወንጀሎች በመፈም የሚከሰሰው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መልስ እንዲሰጥ ዶቼቬለ ጥያቄ ቢያቀርብም መልስ አልሰጠም።የሱዳን ቀውስ፡ የዘር ማጥፋት አደጋዉ ጠንክሯል

የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህጻሩ UNHCR ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሲል ባlለፈው ታኅሳስ መጨረሻ ላይ ባወጣው ዘገባ  እንደጠቀሰው በየቦታው ጥገኝነት በመጠየቅ ላይ ካሉት አብዛኛዎቹ የሱዳን ተፈናቃዮች ደኅንነታቸው የሚጠበቅበት ስፍራ ለመድረስ ጉዞ ላይ ሳሉ ወከባ ፣እገታ ፣መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ የወሲብ ብዝበዛ እና ሌሎች ጥቃቶች ተፈጸሙባቸዋል። የሱዳን ጦር ሀገሪቱን መልሶ ለመቆጣጠር ከፈጥኖ ደራሹ ኃይል ጋር ጭካኔ የተሞላበት ውጊያ ማካሄድ ከጀመረ አንድ ዓመት አልፏል።

ካለፈው ዓመት ሚያዚያ አንስቶ በሚካሄደው ግጭት የተፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ወደ 12 ሚሊዮን ተጠግቷል። ከመካከላቸው ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት በጎረቤት አገራት ተጠግተዋል።ሆኖም ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት አሁንም ሱዳን ውስጥ ናቸው። ይህም በዓለማችን ትልቁ መፈናቀል ተብሏል። የእርዳታ ድርጅቶች በሱዳንና በአካባቢው ሀገራት የተፈጠረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመቋቋም የሚያስፈልገው እርዳታ ከፍተኛ እጥረት አለ።

የተባባሰው አስገድዶ መድፈር

አብዱራህማን አሊ ኬር የተባለው ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት የሱዳን ተጠሪ ጾታን መሠረት ያደረገው ጥቃት በመላ ሱዳን በፍጥነት እየጨመረ መሄዱን አረጋግጠዋል።

«ትክክለኛው ቁጥር የለኝም ሆኖም ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት በመላ ሱዳን በተለይም  ከዳርፉር አንስቶ በካርቱም በአል ጀዚራ እና በሌሎች በአሁኑ ጊዜ ግጭት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በሙሉ መጨመሩ እየተነገረ ነው። »

የርስ በርስ ጦርነት ያመሰቃቀላት ሱዳን
የርስ በርስ ጦርነት ያመሰቃቀላት ሱዳን ምስል AP/PICTURE ALLIANCE

በተለይ በስደተኞች መጠለያዎች በሴቶችና በልካገረዶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አይሏል። እርሳቸው እንደሚሉት የምግብ እርዳታ የንጽህ ውሀ የጤናና የተመጣጠነ ምግብ  እጦትም ተባብሷል። ከሁሉም አስቸጋሪ የሆነው የጤናና የምግብ አቅርቦቶችን ከቻድ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወዳሉበት ወደ ሱዳን ማጓጓዙ ነው።የሱዳን ስደተኞች ወደ 3ኛ አገር መሄድ እንደሚፈልጉ ገለፁ

«በውጊያው ምክንያት መሄድ ያልቻልንባቸው ወይም እርዳታ ማቅረብ ያልቻልንባቸው አካባቢዎች አሉ። የእርዳታ ሰራተኞች እነዚህ ሰዎች የሚፈልጉትን እንዳናቀርብ የሚያደርጉን ገደቦች አሉብን።

ከሱዳን ድንበር ተሻግረው ከሚሰደዱት 90 በመቶው ሴቶችና ህጻናት ናቸው። ከመካከላቸው ከአምስት ህጻናት አንዱ በአጣዳፊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጠቁ ናቸው።

ወደ ቻድ መሸሽ

በጦርነቱ ከህዝቡ 25 ሚሊዮኑ የእርዳታ ጥገኛ ሆኗል። አሁን ቻድ የሚገኙት ተፈናቃዮች ከ600 ሺህ በላይ ናቸው።  ከጦርነቱ በፊት ቻድ 400 ሺህ የሱዳን ስደተኞችን ታስተናግድ ነበር።  

አሊ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች በሙሉ ለዓለም አቀፍ ሕግ በመገዛት ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲያደርጉ  ጥሪ አቅርበዋል።

«በመካከለኛ እና በረዥም ጊዜ ቀውሱን መግታት ፍፁም አስፈላጊ ነው። የግጭቱ ተሳታፊዎች በጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር ግጭቱን ማስቆም መቻላቸውን ማረጋገጥ አለባቸው ።ሁኔታው በሱዳን ህዝብ ላይ እስከዛሬ ተነግሮ የማያውቅ የሰው ልጆች ስቃይ እያደረሰ ነው።»

የስልቦና ችግር የደረሰባቸው ሃዋና ሀሊማ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ለመመለስ ተስፋ ያደርጋሉ። ሃዋ የኤኮኖሚክስ ትምህርትዋን ካጠናቀቀች በኋላ በሂሳብ ሠራተኝነት ወይም በንግድ ድርጅት ሃላፊነት ለመስራት እያለመች ነው። ሃላማም ወደ ቀድሞ ሕይወትዋ መመለስ ትፈልጋለች።

ሁኔታው ከተሻሻለ ዩኒቨርስቲ መግባት እፈልጋለሁ።አዋላጅ ነኝ ሆኖም ሐኪም መሆን እፈልጋለሁ ። ብላለች

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር