1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወለጋው ግጭት ያፈናቀላቸው ወገኖች የእርዳታ ጥሪ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 12 2015

ከሁለት ሳምንታት በፊት ከምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ተፋናቅለው በወረዳው ሀሮ ቀበሌ የተጠለሉ ተፈናቃዮች አስከፊ ያሉትን ሕይወት እየመሩ መሆኑን አመለከቱ። በአከባቢው ለዓመታት በቆየው፤ አሁን ደግሞ ከሁለት ሳምንታት በፊት ተባብሶ በርካቶችን ባፈናቀለው ግጭት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች የሚላስ የሚቀመስ እንደሌላቸው ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/4LHur
Karte Äthiopien Gutin AM

«ተፈናቃዮቹ ለርሃብ መጋለጣቸውን ይናገራሉ»

እንደ ተፈናቃዩ አስተያየት ከ100 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለውባታል ባሉት በዚህች የምሥራቅ ወለጋ ዞን ወረዳ በተለይም ሁለት ሳምንታትን ያለፈው የተባባሰው አለመረጋጋትን ተከትሎ ወደ አከባቢው የሚደርስ የእርዳታ ቁሳቀስም የለም። ነዋሪዎችም ከአካባቢው ከመሰደድ ሌላ የተፈናቀሉቱ ወደ አካባቢው ሲመለሱ አይስተዋልም ይላሉ። እንደ ተፈናቃዩ እንደውም በኪረሙ የተከማቹ የነጋዴዎች እና በተለያየ መልክ የተሰባሰበ እህል ወደ ሌሎች ወረዳዎች ይሸሻል።

«እኛ ያለነው ሀሮ ቀበሌ ነው። በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች ወደ ጊዳ እና ጉቲን ሲፈናቀል የአማራ ተወላጆች በብዛት በግጭቱ የተፈናቀሉት ወደዚህች ሀሮ ቀበሌ ነው፡፡ ወረዳው ተረጋግቷል እርዳታ እየገባ ነው የሚባለውን ብንሰማም ያየነው ነገር የለም፡፡ እንደውም በተለያየ መልክ በኪረሙ መጋዘኖች ተከማቸ እህል ወደ ሌሎች ወረዳዎች ሲጫን ነው የምናስተውለው፡፡ ህዝብ እዚህ ወድቆ ሲራብ ጠያቂም የለው» ሲሉም ሞግተዋል፡፡የአሙሩ ወረዳ ተፈናቃዮች ሮሮ

ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት አንድ የኪረሙ ወረዳ ባለሥልጣን እንደሚሉት ግን በኪረሙ ኅብረተሰቡ ሙሉ በሙሉ ከተፈናቀለ ከሁለት ሳምንታት በኋላ አንጻራዊ ሰላም በመኖሩ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ጥረት እተደረገ ነው። እንደ ባለሥልጣኑ ገለጻ የመጀመሪያ ዙር እርዳታም ከነቀምቴ በኩል ወደ ኪረሙ ገብቷል፡፡ ይሁንና ወረዳው አሁንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ በወረዳው መንግሥታዊ መዋቅር ስር ባለመሆኑ በተለይም እንደ ሀሮ ባሉ ቀበሌ ተንቀሳቅሶ ህብረተሰቡን ወደ መደበኛ ህይወት በመመለስ ደረጃ ላይ አልተደረሰም።

«በተለይም በሀሮ ለወረዳውም የፀጥታ ስጋት የሆኑት በሕጋዊ መንገድ ያልታጠቁ ሽፍቶች ናቸው፡፡ እኛ እንደ ወረዳው የሕግ አካል ለዚህ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ኅብረተሰቡ እንዲያረጋጋ የሚል አቋም ነው ያለን፡፡ እኛ ህዝብን ያለ ብሔር ልዩነት የማስተዳደር ግዴታ ነው ያለብን፡፡ የነካነው ሰላማዊ ህዝብም የለም፡፡ ህዝብና ንብረታቸውን ከኪረሙ ጭነው ተነካን ብሎ በማፈናቀል ወደ ሀሮ የወሰደው የታጠቀው ቡድን እንጂ እኛ ለይተን የጨቆነው ህዝብ የለም፡፡»

ከማንም ጋር ተቀራርበው እንደማይሠሩ የገለጹት ከኪረሙ ወረዳው ተፈናቅለው በዚያው በሀሮ ቀበሌ የተጠለሉት ተፈናቃይ ግን ታጣቂዎች ከሀሮ በመሄድ ኪረሙን አውድመዋል በሚል ክስ አይስማሙም።

«የመንግሥት ኃይል እያለ ከሀሮ ሄዶ ከተማዋን ለማፍረስ አቅሙ ያለው ታጣቂ የለም። ከሕጻን እስከ ሽማግሌ ሲጨፈጨፍ የወረዳው መንግሥት ከለላ አልሰጠም ነበር። ይህ በገለልተኛ አካልም ብጣራ ደስተኞች ነን። እርዳታም እየደረሰን ያልሆነው በዚሁ በመሆኑ መንግሥት ወርዶ ይየን ነው የምንለው።»

በቅርብ ጊዜው የኪረሙ ግጭት ከ60 ሺህ በላይ የአማራ ተወላጆች በሀሮ ቀበሌ ተፈናቅለው መሰብሰባቸውን ተፈናቃዮቹ ይገልጻሉ። አስቀድሞም ከ50 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኙበታል በሚባለው በዚህ ቀበሌ አሁን ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚፈለግ ነው የሚነገረው። ከኪረሙ እና ሌሎች ግጭት በተከሰተባቸው የምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ወረዳዎች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ቁጥር ከ230 ሺህ እንደሚልቅ ከአንድ ሳምንት በፊት የተመድ ሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮ ይፋ አድርጓል። ከእነዚህ አከባቢዎች ተፈናቅለው በተለያዩ ስፍራዎች የተጠለሉ ነዋሪዎች በተለይም በአሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ የተፈናቀሉቱ በተደጋጋሚ በሰጡን አስተያየት በአከባቢው የሚደርስ አንዳችም የእርዳታ ቁሳቁስ አለመኖሩ ፈተናቸውን አክብዶታል። የምሥራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ገመዳ ተፈራ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ግጭት የተከሰተባቸው የዞኑ ሦስት ወረዳዎች ኪረሙ፣ ጊዳ አያና እና ጉቲን ከተማ አንጻራዊ ሰላም ውስጥ መሆናቸውንና ማኅበረሰቡን ከተፈናቀሉበት ቀዬ በመመለስ እርዳታ ለማዳረስ የሚያስችል ዝግጅ ላይ ነን ብለው ነበር። በወለጋ ዞኖች እየቀረበ ያለውን የእርዳታ ፍላጎት እና ሊሰጥ ስለታቀደው ምላሽ ለመጠየቅ ለኦሮሚያ ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ከድር በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ምላሽ አላገኘንም፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ ግን በወለጋ በቅርብ ጊዜው ግጭት ለተፈናቀሉ 30 ሺህ ገደማ ወገኖች የመጀመሪያ ዙር የእርዳታ ቁሳቁስ ወደ ነቀምት ተልኮ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሳይከፋፈል መቆይቱን አመልክተዋል።

 ሥዩም ጌቱ ሸዋዬ ለገሠ ማንተጋፍቶት ስለሺ