1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ ድጋፍ ጥያቄ በምዕራብ ኢትዮጵያ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 8 2015

ከሁለት ሳምንት በፊት በምስራቅ ወለጋ ሶስት ወረዳዎች በተባባሰው ግጭት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች አሁንም የፀጥታ ስጋቱ ያልለየለት መሆኑ ለድጋፍ እጃቸውን እንዲዘረጉ እያስገደዳቸው መሆኑን አመለከቱ፡፡ እንደ የዞኑ አስተዳደር መረጃ በቅርቡ ከሶስት ወረዳዎች ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች የወደጎና ድጋፍ የሚያሻቸው ዜጎች 30 ሺህ ገደማ ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/4L6CM
Karte Äthiopien AM

የምዕራብ ወለጋ ተፈናቃዮች ስሞታ

በቅርቡ ከሁለት ሳምንት በፊት በምስራቅ ወለጋ ሶስት ወረዳዎች በተባባሰው ግጭት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች አሁንም የፀጥታ ስጋቱ ያልለየለት መሆኑ ለድጋፍ እጃቸውን እንዲዘረጉ እያስገደዳቸው መሆኑን አመለከቱ፡፡
እንደ የዞኑ አስተዳደር መረጃ በቅርቡ ከሶስት ወረዳዎች ተፈናቅለው በተለያዩ አከባቢዎች የወደጎና ድጋፍ የሚያሻቸው ዜጎች 30 ሺህ ገደማ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ ለነዚህ ተፈናቃዮች የሚውል ድጋፍ ነቀምቴ ድረስ ባጓጉዝም የፀጥታ ስጋቱ ለተጠቃሚዎች ማከፋፈሉ ላይ መዘግየት መፍጠሩን ነው የገለጸው፡፡

ከዛሬ ሁለት ሳምንታት በፊት በምስራቅ ወለጋ ዞን አንገር ጉቲን ከተማ በተከሰተው የታጣቂዎች ጥቃት የተፈናቀሉት የከተማዋ ነዋሪ አሁን ስለሚገኙበት የፀጥታ ሁኔታ እና የሰብዓዊ ድጋፍ አሳሳቢነት እንዲህ ሲሉ ገልጸውልናል፡፡ 

“አርሶአደሩ ወጣ ብሎ ምርቱን መሰብሰብ እና ከብቶቹን ማሰማራት እንኳ አዳጋች ሆኖ መቀጠሉ ያለውን አደገኛ የፀጥታ ሁኔታው እንዳለ ያሳያል፡፡ በርግጥ አሁን ከተማ ውስጥ የጥይት ድምጽ አይሰማም፡፡ ለጊዜው ግጭትም ቁሟል፡፡ ይህ ማለት ግን ሰላም ሙሉ በሙሉ ተመልሷል ማለት አይደለም፡፡ ከተሞች በፀጥታ ሃይል አባላት ነው እየተጠበቁ የሚገኙት፡፡ ከዚህ የፀጥታ ስጋት የተነሳ ህብረተሰቡ አከባቢውን የመልቀቅ እንጂ የተፈናቀሉት እምብዛም የመመለስ አዝማሚያ እስካሁን አልታየም፡፡ በምስራቅ ወለጋ ከተሞች እኮ አሁን መሰረቱን ገጠር ባደረጉ አርሶአደሮች ነው እየተጨናነቁ ያሉት፡፡ ይህም የሆነው በፀጥታ ስጋት ነው፡፡ አምርቶ ለሌላም ልተርፍ የሚችለው አርሶ አደር ከዚህ የተነሳ ይሄው የሰው እጅ እየተጠባበቀ ነው፡፡”

ከዚህች ከተማ ተፈናቅለው አሁን ላይ የሰብኣዊ ድጋፎች እንደሚሹ የሚገልጹት እኚህ ነዋሪ፤ አከባቢው በአገር መከላከያ ሰራዊት መረጋጋቱን ቢያረጋግጡም አሁንም ዘላቂ የሰላም ሁኔታ ባለመስፈኑ እሳቸውን ጨምሮ ከአከባቢው የተፈናቀሉቱ አምርተው እራሳቸውን ለመመገብም ያላቸው ተስፋ መሟጠጡን ያስረዳሉ፡፡
በምስራቅ ወለጋ በተለይም በቅርቡ በሶስት ወረዳዎች ባገረሸው የፀጥታ ችግር ከ30 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የሚገልጹት የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ገመዳ ተፈራ፤ ተፈናቃዮችን መልሶ ከማቋቋም ጎን ለጎን ድጋፉን ለማቀላጠፍ አስተዳደሩ አቢይ ትኩረት የሰጠው ጉዳይ ነው ባይ ናቸው፡፡ 
“አሁን የተፈናቀሉት የነዚህ አከባቢዎች አርሶ አደሮች ትርፍ አምራች የሆኑና ለሌላም የሚተርፉ ነበር፡፡ አሁን ግን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው መንገድ ላይ ወድቀዋል፡፡ እስካሁን በኪረሙ፣ ጊዳ አያና እና አንገር ጉቲን አከባቢ አንድ ዙር እርዳታ ቢደርስም በቂ አለመሆኑን ስለምንረዳ ከመንግስት በተጨማሪ መንግስታዊ ያልሆኑና ግለሰቦችም እንዲረባረቡ እየጠየቅን ነው” ብለዋልም፡፡ 
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 22 ሚሊዮን ዜጎች ገደማ እርዳታ ጠባቂ መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ፡ በተለይም በምእራብ ኦሮሚያ በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ከ220 ሺህ በላይ ዜጎች መኖራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ  መረጃ በምዕራብ ወለጋ ከ106 ሺህ በላይ፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ደግሞ 116 ሺህ ተፈናቃዮች ይገኛሉ። 
ከባለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ በምስራቅ ወለጋ ሶስት ወረዳዎች በተባባሰው ግጭት ደግሞ ከ30 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ድጋፍ የሚያሻቸው መሆኑ ይነገራል፡፡ የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር (ቡሳ ጎኖፋ) ቢሮ ለነዚህ ተፈናቃዮች ስለሚያደርገው ድጋፍ ለመጠየቅ ለቢሮው ኃላፊ በተደጋጋሚ ያቀረብንላቸው ጥያቄ ምላሽ አላገኘም፡፡ 
የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ እንደሚሉት ግን በቅርቡ ከምስራቅ ወለጋ ለተፈናቀሉ 30 ሺህ ገደማ ዜጎች የሚውል የእርዳታ ቁሳቁስ ነቀምቴ ቢደርስም በፀጥታ ችግር ምክኒያት የማከፋፈል ሁኔታ መዘግየቱን ገልጸዋል፡፡ 
ከኦሮሚያ በተጨማሪ በምዕራብ ኢትዮጵያ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ለ420 ሺህ ተረጂዎች የሚሆን የድጋፍ እህል መላኩን የተናገሩት አቶ ደበበ፤ በቅርቡ በክልሉ የተፈጠረው የመንግስት እና ታጣቂዎች የሰላም ስምምነት እርዳታዎችን ለማጓጓዝ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ 
በእንግሊዝኛ ምህጻሩ IRC በመባል የሚታወቀው የረድኤት ተቋም ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ዘገባ ላይ ከመላው ዓለም 20 ሃገራት ከምግብ አቅርቦት እጥረት ጋር በተገናኘ ያሳስቡኛል ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ከሶማሊያ በመቀጠል በሁለተኝነት አስቀምጦታል፡፡
ሥዩም ጌቱ 
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር