1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤች አይ ቪ አሳሳቢ የጤና ችግር ሆኖ መቀጠል

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 23 2016

ኤች አይ ቪ የዓለም ማሕበረሰብ ጤና እና ማሕበራዊ መስተጋብር በቀላል የማይታይ ጉዳት የሚያደርስ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ መዝለቁን የተባበሩት መንግሥታት ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ አስታውቋል። ኢትዮጵያም የኤች አይ ቪ ኤድስ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ሀገሮች አንዷ ናት።

https://p.dw.com/p/4it9F
የኤች አይ ቪ አሳሳቢ የጤና ችግር
የኤች አይ ቪ አሳሳቢ የጤና ችግርምስል AP

የኤች አይ ቪ አሳሳቢ የጤና ችግር ሆኖ መቀጠል

የኤች አይ አሳሳቢ የጤና ችግር ሆኖ መቀጠል 

ኤች አይ ቪ የዓለም ማሕበረሰብ ጤና እና ማሕበራዊ መስተጋብር በቀላል የማይታይ ጉዳት የሚያደርስ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ መዝለቁን የተባበሩት መንግሥታት ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ አስታውቋል። ቫይረሱ የሚያስከትለው በሽታ ባለፉት አራት አሥርት ዓመታት ግድም 42.3 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉም በዓለም ጤና ድትጅት ተገምቷል። 

"በአሁኑ ሰዓት ኤች አይ ቪ እንደማንኛውም ተላላፊ በሽታ ምንም እንኳን ማዳን ባይቻልም ሙሉ በሙሉ፣ ነገር ግን መታከም የሚችል፣ መቆጣጠር የሚቻል በሽታ እንደሆነ ተደርሷል ማለት ነው" ዶክተር ተስፋዬ ተፈራ ናቸው፣ ኤድስ ሄልዝ ፋውንዴሽን በተባለ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በኢትዮጵያ የብሔራዊ ሜዲካል ዳይሬክተር ሆነው ይሠራሉ። ይህ ድርጅት ባለፉት አሥር አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በኤች አይ ቪ መከላከል፣ ሕክምና እና ድጋፍች ዙሪያ በሥራ ላይ ይገኛል።   

የኤች አይ ቪ አሳሳቢ የጤና ችግር
የኤች አይ ቪ አሳሳቢ የጤና ችግርምስል Sylvain Grandadam/IMAGO

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሥር የሚገኘው የዓለም ጤና ድርጅት እንደሌላው ሁሉ ኤች አይ ቪን የተመለከቱ ወቅታዊ መረጃዎችን በየጊዜው ያወጣል። በዚህም መሠረት የኤች አይ ቪ ቫይረስ ከተከሰተበት ከአራት አሥርት ዓመታት ግድም በፊት ጀምሮ 88 ሚሊየን ሰዎች በኤች አይ ቪ ቫይረስ ተጠቅቶ ወደ ግማሽ የተጠጋው ሕዝብ ለሞት ተዳርጓል። በ 2023 መጨረሻ 39.9 ሚሊየን ሰዎች በምድሪቱ ላይ ከዚህ ቫይረስ ጋር እንደሚኖርም ጭምር ይሄው ተቋም አስታውቋል።

የሰዎች የጤና ሥጋት ሆኖ ዘልቋል ሲባልም 42.3 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎችን ህይወት እንደዋዛ መቅጠፉን በማስቀመጥ ጭምር ነው። ቫይረሱ በደማቸው ከሚገኝ ሚሊዮኖች ውስጥ 65 በመቶ የሚሆኑት ከብዙ ችግሮች ሊላቀቅ ባልቻለው የአፍሪካ አሕጉር ውስጥ ስለመሆኑም ተብራርቷል።

 

በመከላከል ረገድ የተስተዋለው ቸልታ

ከሁለት አሥርት ዓምታት በፊት - በተለይ የቫይረሱ ስርጭት በአስፈሪ ሁኔታ ሲዛመት፣ መገለል፣ አድሎ እና ማሕበራዊ መስተጋብር ላይ በእጅጉ ጉዳት ያደርስ በነበረበት ወቅት፣ በየ ዓመቱ ከ 20 እስከ 30 ሺህ ሰዎች በኤች አይ ቪይ ቫይረስ ተጠቅተው ይሞቱ ነበር። ይህ ቁጥር ባለፈው ዓመት ከ አሥር ሺህ በታች ዝቅ ብሎ በዓመት አስከ 8500 የሚሆኑ ሰዎች በዚሁ ቫይረስ እና ተዛማጅ በሽታዎች ለሞት ተጋላጭ ሆነዋል መባሉ ችግሩን ለማቃለል የተደረገው ጥረትን ያመለክታል።  

የኤች አይ ቪ አሳሳቢ የጤና ችግር
የኤች አይ ቪ አሳሳቢ የጤና ችግርምስል JOE KLAMAR/AFP/Getty Images

የመከላከያ መንገዶች ማነስ፣ ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው በየዓመቱ እስከ 40 ሺህ ሰው በቫይረሱ ይያዝ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ወደ 5700 ዝቅ ማለቱንም በዘርፉ ላይ ለብዙ ዓመታት የሠሩት ባለሙያው ዶክተር ተስፋዬ ተፈራ ተናግረዋል። አሁን የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ እንመልከት። 

"በኢትዮጵያም የኤች አይ ቪ ኤድስ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው ሀገሮች አንዷ ናት። በጣም ብዙ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ባለፉት ሃያ ሠላሳ ዓመታት ብዙ ታካሚዎቻችንን መድኃኒት ባለመገኘቱ ምክንያት፣ መመርመር ባለመቻል ምክንያት ሕይወታቸውን ሲያጡ ቆይተዋል" 

የኤች አይ ቪ አሳሳቢ የጤና ችግር
የኤች አይ ቪ አሳሳቢ የጤና ችግርምስል Jens Kalaene/dpa/picture alliance

እንደ ጎርጎረሲያን የዘመን አቆጣጠር በ1996 ዓ.ም ለዚህ በሽታ መከላከያ መድኃኒት መገኘቱ ብዙዎችን ከሞት ታድጓል። በኢትዮጵያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቫይረሱ አሁንም በደማቸው የሚገኝ ሲሆን የጸረ ኤች አይ ቪ ህክምና ክትትል ያገኛሉ። ሆኖም ግን መድኃኒት ባለመጀመርና በአግባበቡ ባለመከታተል የብዙ ሰዎች ሕይወት አሁንም እንደዋዛ ያልፋል። HIV ቫይረስ የሰዎችን በሽታ የመቋቋም አቅማቸውን የሚያዳክም ተኅዋሲ ነው። አስፈላጊ የሚባለው ክትትል ተደርጎ በጊዜ እርምጃ ካልተወሰደ ኤድስ ወደ መሆንና ሰውን ወደመግደልም ይሸጋገራል። 

የመመርመርያ መሣሪያዎች እጥረት፣ የሰዎች ንቃት እና ግንዛቤ አናሳ መሆን፣ የመከላከያ ቁሶች በተለይ የኮንዶም እጥረት፣ ዋና ዋና ችግሮች የነበሩ ሲሆን አሁን ሰዎች ይህንን ቫይረስ በራሳቸው መመርመር የሚችሉበት መሣሪያ ያለበት ዘመን ላይ መደረሱ አንድ በጎ ነገር ነው። ሆኖም ግን ይህ በሽታ የሚስፋፋባቸው አካባቢዎች፣ በሙያ ደረጃ ሰዎች ለዚህ ተጋላጭ የሚሆኑባቸው መስኮች ጥቂት አይደሉምና በዚያ ዙሪያ መበርታት ያሻል የሚለው የዶክተር ተስፋዬ ተፈራ ሀሳብ ነው።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ