አሳሳቢው የኤድስ አስተላላፊ ተኀዋሲ ስርጭት
እሑድ፣ መስከረም 21 2010ኤች አይቪ ኤድስ አሁንም በኢትዮጵያ አሉ ከሚባሉት ዋነኞቹ የጤና ተግዳሮቶች አንዱ ነው። እርግጥ፣ በስርጭቱ መስፋፋት አንፃር የመጀመሪያው ፖሊሲ በ1990 ዓም ገቢራዊ ከሆነ እና በሽታውን የሚያስተላልፈው ተኀዋሲ በደማቸው የሚገኙ ሰዎችን የመንከባከቡ እና ነፃ ህክምና አገልግሎት የመስጠቱ፣ እና ሰዎች ራሳቸውን መከላከል የሚችሉበት ምላሽ በ1997 ዓም መሰጠት ከጀመረ ወዲህ የተኀዋሲው ስርጭት በጉልህ ቀንሶ ነበር። ግን ካለፉት ጥቂት ጊዚያት ወዲህ የተኀዋሲው ስርጭት እንደገና በመስፋፋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በብሔራዊ ኤች አይ ቪ መቆጣጠሪያና መከላከያ ጽህፈት ቤት የብሔራዊ ኤች አይ ቪ መቆጣጠሪያና መከላከያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
በብሔራዊ ኤችአይቪ መቆጣጠሪያና መከላከያ ጽህፈት ቤት ዘገባ መሰረት፣ ባለፈው ዓመት ብቻ 27,000 ሰዎች ከተኀዋሲው ጋር እንደሚኖሩ ተመዝግቧል።በአሁኑ ጊዜም በመላይቱ ሀገር ከተኀዋሲው ጋር የሚኖረው ሰው ቁጥር ቢያንስ 718,000 እንደሆነ ይገመታል።እርግጥ፣ ከ2000 ዓም ጋር ሲነፃፀር አዲስ ከተኀዋሲው ጋር የሚኖረው ሰው ቁጥር በ90% ቀንሷል። በኤድስ በያመቱ እስከ 20,000 ሰው እንደሚሞት ነው የተነገረው። የኤድስ አስተላላፊ ተኀዋሲ ስርጭት ባንዳንድ አካባቢ ቅናሽ ቢያሳይም፣ በተለይ በአዲስ አበባ፣ በሐረሪ፣ እና በድሬዳዋ፣ በጋምቤላ ከፍ ብሎ እንደሚገኝ ተገልጿል። በኢትዮጵያ የስርጭቱ መጠን በወቅቱ 1,18 ከመቶ ሲሆን፣ በዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት መስፈርት መሰረት የስርጭቱ መስፋፋት መጠን ከአንድ ከመቶ ካለፈ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያመለክታል። ስለተኀዋሲው ስርጭት እንደገና መስፋፋት፣ ምክንያቱ እና መፍትሔው ውይይት አካሂደናል።
አርያም ተክሌ
ተስፋለም ወልደየስ