1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እሑድ በአዲስ አበባ የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ እና የገጠመው ስጋት

ረቡዕ፣ ኅዳር 26 2016

የፊታችን እሑድ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ጦርነት ይቁም ሰላም ይሰፈን በሚል መሪ ሃሳብ አዲስ አበባ ውስጥ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ መቅረቡ ተገለጸ። ሰልፉ የተጠራውም በፖለቲከኞች፣ ሲቪል ተቋማት እና በጎ ፈቃደኛ ግለሰቦች ነው ተብሏል። ይሁንና የሰልፉ አዘጋጆች ከመንግስት ሰልፉ እንዳይካሄድ ማስፈሪሪያ ደርሶናል ይላሉ።

https://p.dw.com/p/4ZqXt
አዲስ አበባ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

በአማራ ክልል ጦርነት ይቁም

«ሰላማዊ ሰልፉን እሑድ ኅዳር 30 ቀን 2016 ከአራት ሰዓት እስከ ስምንት ሰዓት እንዲካሄድ ብለን ነው የጠራነው፡፡ ዋና መልእክቱም ጦርነት ይቁም ሰላም ይስፈን ሚል ነው፡፡ ሀሳቡን ለሚደግፍ ማንኛውም ሰው ነው ጥሪው የቀረበው፡፡” ይህን አስተያየት ለዶይቼ ቬለ የሰጡት ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ ፖለቲከኛ የሺዋስ አሰፋ ናቸው፡፡

ሰላማዊ ሰልፉን ማን አዘጋጀው በሚል ከዶቼ ቬሌ ለቀረበላቸውም ጥያቄ አቶ የሺዋስ አሰፋ፤ “በብዛት ፖለቲከኞች ነን፡፡ ግን ያሰባሰበን ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ የተሰባሰብንበት አጋጣሚም በትግራዩ ጦርነት ላለቁ ወንድሞቻችን ሀዘን ስታወጅ ሀዘኑ የኛም ነው ብለን የሞቱትን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በዘከርንበት መድረክ ነው፡፡ በዚሁ ተነሳስተን ነው ጦርነት ይብቃ ለማለት የወሰነው” ሲሉ መልሰዋል፡፡

ይሁንና ይህን ሰልፍ የሚያስተባብር አዘጋጅ ኮሚቴ ሰኞ ህዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የመንግስት አካላትን ሰልፉ እንዳይደረግ የተለመደ ያለው ማስፈራሪያ ስለማድረጋቸው አስታውቋል፡፡ ሰልፉን የጠራው አስተባባሪ ኮሚቴው በሰኞው መግለጫው የፌዴራል ፖሊስ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም የከተማዋ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ከህገመንግስት መርህ ውጪ ዛቻ ሰንዝሮብኛል ብለዋል፡፡ ኮሚቴው ሰላማዊ ሰልፉን የማካሄድ ሂደቱ በህግ አግባብ ስርዓትን የተከተለ ነውም ብሏል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ
አዲስ አበባ ከተማ ምስል Seyoum Getu/DW

ስለዚሁ መግለጫ የተጠየቁት አቶ የሺዋስ አሰፋ፤ “ጦርነት ይቁም የሚል ሀሳብ መደገፍና መበረታታት የነበረበት ነው፡፡ እኛ የሀገሪቱን ህግ መሰረት አድርገን ኩለት ቀን በፊት የሚለውንም ከ12 ቀን በፊት ሰልፉን ማድረግ እንደምንፈልግ አሳውቀናል፡፡ ይሁንና ከንቲባ ጽ/ቤት ለዚህ መልስ አልሰጠንም፡፡ ከአዲስ አበባ እና ፌዴራል የፖሊስ አመራሮች አነጋግረውን ነበር፡፡ ሊያነጋግሩን ጥሪ ስያቀርቡልንም ቦታውና ቀኑን በተመለከተ የሚያወያዩን መስሎን ነበር፡፡ ይሁንና የተለመደውን ችግር ይፈጠራል ችግር ከተፈጠረ እርምጃ እንወስዳለን የሚል ማስፈራሪያ ውስጥ ገቡ በሉ ደህና እደሩ ብለን ወጣን፡፡” ብለዋል፡፡

እሑድ በአዲስ አበባ ይካሄዳል ስለተባለው ሰላማዊ ሰልፍ እና ቀርቧል ስለተባለው ማስፈራሪያ ዶቼ ቬለ ከፌዴራል ፖሊስ እና አዲስ አበባ ፖሊስ ባለስልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርጓል። የፌዴራል ፖሊስ ቃልአቀባይ አቶ ጄኢላን አብዲ አሁን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በዚህ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት እንደማይፈቅድላቸው ገልጸዋል።

ሥዩም ጌቱ 

ፀሐይ ጫኔ 

አዜብ ታደሰ