1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል የኢንተርኔት መቋረጥ በባንክ፣ በግብረ ሰናይና የምርምር ሥራ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ

ዓርብ፣ መስከረም 25 2016

በአማራ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ የተከሰተው የኢንተርኔት መቋረጥ በባንክ አገልግሎት፣ በግብረ ሰናይ ተቋማት እንቅስቃሴ እና በዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲዎች ባልደረቦች በኢትዮጵያ እና በውጭ አገራት ከሚገኙ ተቋማት እና ምሁራን ጋር የነበራቸው ግንኙነት መቋረጡን ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/4XD2f
የተቋረጠ የኢንተርኔት አገልግሎት
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባልደረቦች በኢትዮጵያ እና በውጭ አገራት ከሚገኙ ተቋማት እና ምሁራን ጋር የነበራቸው ግንኙነት መቋረጡን ይናገራሉ። ምስል Avishek Das/ZUMA Wire/picture-alliance

በአማራ ክልል የኢንተርኔት መቋረጥ ያሳደረው ተጽዕኖ

በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ በምርምር ስራ ላይ ጫና እየፈጠረ እንደሆነ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ተናገሩ።  በማህበራዊ አገልግሎት የተሰማሩ ባለሙያዎች ደግሞ ከሌሎች አካላት የሚደረግ የመረጃ መለዋወጥ በመቋረጡ እርዳታ ያገኙ የነበሩ አካላት ለጉዳት እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡ 

ከነሐሴ ወር መጀመሪያ ጀምሮ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎችና በመከላከያ ሰራዊት መካከል የተፈጠረውን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፣ የኢንተርኔት አገልግሎትም በሁሉም የአማራ ክልል ከተሞች ከተቋረጠ ወራት እየተቆጠሩ ነው።

የአማራ ክልል ፀጥታና ኢንተርኔት

ዓለም በቴክኖሎጂ ድጋፍ ወደ አንድ መንደር እየተለወጠች ባለችበት በዚህ ወቅት የኢንተርኔት መቋረጥ የተለያዩ ተቋማትን ስራ እየጎዳ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች እየተናገሩ ነው፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ በመተማ ከተማ የሚገኙ የባንክ ሰራተኛ የኢንተርኔት መቋረጥ በስራቸው ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ገልጠዋ። እንደ ባለሙያው ከዋና መስሪያ ቤት ወደ ቅርንጫፎች የሚደረግ የስራ ግንኙነትና የየእለት የጽህፈት ቤቶችን የስራ አፈጻፀም ማወቅ እንዳልተቻለ ነው የገለጡት፡፡ ግብረ መልስ ለመስጠትና ለመደገፍም አስቸጋሪ ሆኗል ብለዋል፡፡ 

ጠብመንጃ ያነገተ ታጣቂ
በአማራ ክልል በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂ ቡድን መካከል በነሐሴ 2015 ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል። ምስል AP/picture alliance

በባሕር ዳር ከተማ የአንድ ክፍለ ከተማ የሴቶች እና ህፃናት ባለሙያ በበኩላቸው 3000 የሚጠጉ ወላጅ የሌላቸው እና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች እርዳታ የሚያገኙት መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በሚደረግ የመረጃ ልውውጥ እንደነበር ጠቁመው አሁን ግን  አገልግሎቱ በመቋረጡ ድጋፉም ተቋርጧል ብለዋል፡፡ ለተማሪዎች የትምህርት ቤት ቁሳቁስ፣ ዩኒፎርምና ምገባ ማቅረብ እንዳልተቻለ ነው በምሬት የተናገሩት።

እየጨመረ የመጣው የኢንተርኔት አፈና በኢትዮጵያ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ሳምሶን ጫኔ የኢንተርኔት መቋረጡ የሁለተኛና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የሚፅፋቸውን የመመረቂያ ጽሁፎች ለማየት አላስቻለም፣ ተማሪዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካ ነው የሚገልፁት፡፡ አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲውን የምርምር ስራም አዳክሞታል ብለዋል፡፡

ሌላ በዩኒቨርሲቲው የጤና ባለሙያ የሆኑ መምህር በበኩላቸው የአገልግሎቱ መቋረጥ በግለሰቦችና በተቋማት ሠራ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል፡፡ በግላቸውም ኢንተርኔት መስራት ባለመቻሉ የውጪ ኮንፈረንስ እንዳመለጣቸው፣ የትምህርት እድሎችን የሚጋብዙ መልዕክቶችና ደብዳቤዎችን ማየት እንዳልተቻለ አብራርተዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደሚሰሩ የነገሩን ሌላ ባለሙያ የኢንተርኔት መቋረጥ በኢኮኒሚና ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ኪሳራ እያስከተለ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በአማራ ክልል ከኢንተርኔት መቋረጡ በተጨማሪ በበርካታ የክልሉ ከተሞች የስልክ አገልግሎትም ከተቋረጠ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡

ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ