1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል ከተሞች የሰዓት ዕላፊ ገደብና የዕለቱ እንቅስቃሴ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 4 2015

በአማራ ክልል ስድስት ከተሞች የሰዓት እላፊ ገደብ ተጥሏል። በቅርቡ የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ጣቢያ ከዛሬ ጀምሮ በየከተሞቹ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እና የመጓጓዛ አገልግሎቶች እንደሚጀመሩ አመልክቷል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች በአንዳንዱ አካባቢ መጠነኛ እንቅስቃሴ መኖሩን ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4V0zg
የደብረ ማርቆስ ከተማ
ከባሕር ዳር በ250 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረ ማርቆስ ሆቴሎች እና ሱቆች አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመሩ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የአማራ ክልል ከተሞች የሰዓት ዕላፊ ገደብና የዕለቱ እንቅስቃሴ

ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ከባድ ውጊያ በተደረገባት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ ባሕር ዳር መንገዶች እንደተዘጉ መሆናቸውን የከተማው ነዋሪዎች ተናገሩ። ባሕር ዳር ከተማ በውጊያ የሞቱ ሰዎች ሥርዓተ ቀብር ትላንት ረቡዕ በተለያየ ቦታ መፈጸሙን የዐይን እማኞች ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ባሕር ዳርን ጨምሮ ስድስት በአማራ ክልል የሚገኙ ከተሞች በጸጥታ አስከባሪዎች ቁጥጥር ሥር መግባታቸውን ገልጸዋል።

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የባሕር ዳር ነዋሪ ዛሬ ሐሙስ የሚገኙበት አካባቢ "ጸጥ እረጭ" ያለ እንደሆነ ገልጸዋል። "ትራንስፖርት የለም። አንዲት አንቡላንስ ስትሔድ ታይታለች" ሲሉ ነዋሪው ሁኔታውን አስረድተዋል።

በባሕር ዳር ከተማ የሚገኝ የገበያ አዳራሽ
በባሕር ዳር ከተማ መንገዶች እንደተዘጉ መሆኑን ተቋማትም አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸውን የከተማው ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Alemenew Mekonnen/DW

የከተማዋ መንገዶች በድንጋይ እንደተዘጉ መሆናቸውን የገለጹ ሌላ የባሕር ዳር ነዋሪ በተለምዶ ባጃጅ ተብለው ከሚጠሩት ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ውጪ እንቅስቃሴ እንደሌለ ገልጸዋል።

ከባሕር ዳር በ250 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረ ማርቆስ ሆቴሎች እና ሱቆች አገልግሎት መስጠት እንዳልጀመሩ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አብዛኛው እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት እንዳልተመለሰ የገለጹት የከተማዋ ነዋሪ ዛሬ ጠዋት ከደብረ ማርቆስ አንድ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት ወጥቶ ሔዷል፤ ከአዲስ አበባ ሁለት ተሽከርካሪዎች ገብተዋል የሚል ወሬ መስማታቸውን ተናግረዋል።

ባህር ዳር ሟቾችን ስትቀብር ዋለች

ከአዲስ አበባ በ100 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው በደብረ ብርሀን ከተማ ሱቆች እና የመጓጓዣ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ወደ እንቅስቃሴ መግባታቸውን አንድ የከተማው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "ትናትና ከሰዓት ጀምሮ ባጃጅ መንቀሳቀስ ጀምሮ ነበር። ዛሬ ሱቅም ተከፍቷል፤ ተቋሞችም አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል" ሲሉ የከተማው ነዋሪ የደብረ ብርሀንን ሁኔታ ገልጸዋል። የጸጥታ አስከባሪዎች በደብረ ብርሀን "ቤት ፍተሻ እያደረጉ ነው" ሲሉ እኚሁ ነዋሪ ገልጸዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ረቡዕ ነሐሴ 3 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ ባሕር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ላሊበላ፣ ጎንደር እና ሸዋ ሮቢት ከተሞች በመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ አስታውቋል። በስድስቱ ከተሞች እስከ ነሐሴ 17 ቀን 2015 የሚዘልቅ የሰዓት ዕላፊ ተደንግጓል።

ደብረ ብርሀን ከተማ
ከአዲስ አበባ በ100 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው በደብረ ብርሀን ከተማ ሱቆች እና የመጓጓዣ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ባይሆንም ወደ እንቅስቃሴ መግባታቸውን አንድ የከተማው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል Eshete Bekele/DW

የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ባወጣው መግለጫ መሠረት "ከባጃጅና ከሞተር ሳይክል በስተቀር ሁሉም ዓይነት የከተማ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ወደ አገልግሎት ይገባሉ።" የመንግሥት፣ የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ የንግድ፣ የጤና፣ የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግም የአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ገልጾ ነበር።

በባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች በመከላከያ ሠራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የየከተሞቹ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። እስካሁን በአማራ ክልል በአጠቃላይ ምን ያክል ሰዎች እንደተገደሉ የሚታወቅ ነገር የለም።

የአማራ ክልል እንዴት ዋለ?

ዓለምነው መኮንን 

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ