1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጥቃቱ 6 ሰዎች ተገድለዋል

ሰኞ፣ መስከረም 21 2016

«በጥቃቱ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች ስድስት ሰዎች ደግሞ እስከ አሁን የደረሱበት አልታወቀም። ከሰማኒያ በላይ መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል። እንዲሁም ለጊዜው ግምታቸው ያልታወቁ ቁሳቁሶችና የቤት እንስሳት ተዘርፈዋል።»

https://p.dw.com/p/4X3Oe
Karte Sodo Ethiopia ENG

የታጣቂዎች ጥቃት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል

 በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ማረቆ ልዩ ወረዳ ታጣቂዎች ትናንት ፈጸሙት በተባለ ጥቃት ስድስት ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች አሥራ አንድ ቆሰሉ። ነዋሪዎች እንዳሉት ታጣቂዎቹ ጥቃቱ የተፈጸመው በክልሉ በማረቆ ልዩ ወረዳ እና በምሥራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በሚገኝ አዋሳኛ ሥፍራ ላይ ነው። ሁለቱን ወረዳዎች በሚያጎራበቱበት የምሥራቅ ዲዳ እና የሰሜን ዲዳ ቀበሌያት መኻል የምትገኘውና «ሳያ» የተባለችው መንደር የጥቃት አድራሾቹ ኢላማ መሆኗ ነው የተነገረው። 

በሳያ መንደር ምን ሆነ  ?

«ትናንት ጠዋት ምንም ባላሰብንበት ነው ሠፈሩበታጣቂዎች የተወረረው» ይላሉ የሳያ መንደር ነዋሪዎች። በጥቃቱ አምስት ሰዎች በጥይት ተመተው መሞቸውን እንደሚያውቁ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ሦስት የመንደሩ ነዋሪዎች «በርካቶች በጥይት ተመተው ቆስለዋል። የመኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል። በድንጋጤ ከመንደሩ ሸሽተው የጠፉ ሰዎችንም እስካሁን ማግኘት አልተቻለም» ብለዋል።
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ያደረሱባት የሳያ መንደር የማስቃንና ማረቆ ማህበረሰብ በይገባኛል ጥያቄ በሚወዛገቡባቸው ዘጠኝ ቀበሌያት መካከል ምሥራቅ ዲዳ እና የሰሜን ዲዳ በተባሉ ቀበሌያት አዋሳኝ ሥፍራ ላይ ነው የምትገኘው። ነገር ግን በመንደሯ የተፈጸመው ጥቃት ከቀበሌያቱ የአከላለል ጥያቄ ጋር የተያያዘ ይሁን ወይም አይሁን ማረጋገጥ አልተቻለም። ያም ሆኖ በመንደሩ የሸመቁት ታጣቂዎች  ትናንት ጥቃቱን ካደረሱ በኋላ ዛሬ ጠዋትም በድጋሚ ወደ  መንደሯ መተኮሳቸውን የጠቀሱት ነዋሪዎች አሁን ላይ ተጨማሪ ጉዳት ሊያደርስብን ይችላሉ በሚል ሥጋት ውስጥ እንደሚገኙም ተናግረዋል።


የደረሰው ጉዳት በተመለከተ  

በወረዳው ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መድረሱን ለዶቼ ቬለ ያረጋገጡት  የማርቆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሤ መኬ  ይህን አሰቃቂ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ከምሥራቅ ጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ የተነሱ ናቸው ይላሉ። ጥቃት አድራሾቹ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ የታጠቁ መሆናቸውን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው «በጥቃቱ ስድስት ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች ስድስት ሰዎች ደግሞ እስከ አሁን የደረሱበት አልታወቀም። ከሰማኒያ በላይ መኖሪያ ቤቶች ወድመዋል። እንዲሁም ለጊዜው ግምታቸው ያልታወቁ ቁሳቁሶችና የቤት እንስሳት ተዘርፈዋል። አሁን ላይ በነዋሪዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳያደርስ ከክልል ኃላፊዎች ጋር በመመካከር የመከላከያ ሠራዊት ወደ  አካባቢው እንዲገባ  እያደረግን እንገኛለን» ብለዋል።

መፍትሄ ያልተበጀለት የይገባኛል ጥያቄ 

የመስቃን እና ማረቆ ማኅበረሰብ ቀደምሲል «የማስቃን እና ማረቆ ወረዳ» በሚል በአንድ የአስተዳደር መዋቅር ሥር ሲተዳደሩ ቆይተዋል»። በ1994 ዓም «መስቃን ወረዳ» እና «ማረቆ ወረዳ» በሚል የተናጠል አስተዳደር ከመሠረቱ ወዲህ ግን አካባቢው ሄድ መለስ በሚል ግጭት ሰላም እንደራቀው ይገኛል። የማረቆ ልዩ ወረዳ የቀድሞው አስተዳደር ለሁለት ሲከፈል ዘጠኝ ቀበሌያት አለአግባብ ወደ መስቃን ወረዳ ተካለውብኛል ሲል ይከሳል። መሰቃን ደግሞ ይህን አይቀበለውም። የቀድሞው የደቡብ ክልልም ሆነ የአሁኑ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እስካሁን ለይገባኛል ጥያቄዎቹ ዘላቂ መፍትሄ ባለማበጀታቸው ጉዳዩ ዛሬም ድረስ እያነታረከ ይገኛል።
በሳያ መንደር  ተፈጽሟል በተባለው ጥቃትን በተመለከተ የምሥራቅ ጉራጌ ዞንንም ሆነ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የፀጥታ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ከትናንት ጀምሮ ጥረት ብናደርግም ኃላፊዎቹ ስብሰባ ላይ ናቸው በመባሉ ለጊዜው ምላሻቸውን በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም። 
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ