1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታገቱት የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ቤተሰቦች ተማሪዎቹ አልተለቀቁም ይላሉ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 4 2016

“ልጆቹ እስካሁን አልተለቀቁም በዚያው በአጋቾች እጅ ናቸው” ያሉት የታጋች ቤተሰብ ትናንት በመገናኛ ብዙሃን የተሰራጨው መረጃ ተጨባጭነት እውነታውን ማረጋገጥ አልተቻላቸውም፡፡ ከታጋች ተማሪዎች አንዷን በአጋቾች በኩል አግኝተው ማነጋገራቸውን የሚገልጹት የቤተሰብ አባል ከመቶ በላይ ተማሪዎች እስካሁንም ድረስ በዚያው እንደሚገኙ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4iBZW
 Abay-Flussbrücke ,Abay,Ethiopia,Äthiopien,Amhara region,Ethiopia,Äthiopien
ምስል Seyoum Getu/DW

የታገቱት የደባርቅ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ቤተሰቦች ተማሪዎች አልተለቀቁም ይላሉ

ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. ከአማራ ክልል ተነስተው ወደ አዲስ አበባ በሚያመሩበት ወቅት በታጣቂች ታግተው የተወሰዱት ከ160 በላይ ተማሪዎች ተለቀዋል ሲል የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አስታወቀ፡፡የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በትናንትናው እለት በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ ያወጣው መረጃ የታገቱት ተማሪዎቹ “ሸነ” ካለው ታጣቂ ቡድን የተለቀቁት “መንግስት እና ህዝብ በወሰዱት የተቀናጀ ኦፕሬሽን ነው” ብሏል የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሴ በኢትዮጵያ ስለታገቱት ተማሪዎች መግለጫ።፡በዛሬው እለት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የተማሪዎቹ ጓደኞችና ቤተሰቦች ግን እስካሁንም ድረስ ተማሪዎቹ ከታጣቂው ሳይለቀቁ አሰቃቂ ባሉት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

የኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን መግለጫ

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ከሰሞኑ በጉዞ ላይ እያሉ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እገታን በማስመልከት በትናንትናው እለት በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ የለቀቀው መረጃ በበርካታ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተስተጋብቷል፡፡ “የጸረ-ሰላም ኃይሎች ጥቃት በህዝብና መንግስት ቅንጅት ከሽፏል” በማለት የጀመረው አጠር ያለው መግለጫው ከሰሞኑ የታገቱት ተማሪዎች በህዝብ እና መንግስት የተቀናጀ ኦፕሬሽን መለቀቃቸውን ያስረዳል፡፡

መረጃው ከደባርቅ ኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደየቤተሰቦቻቸው እየተመለሱ ካሉ 167 ተማሪዎች 160 ማስለቀቅ መቻሉንና ቀሪዎቹንም ለማስለቀቅ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኝ ያትታል፡፡ አጠር ያለው መግለጫው ከዚህ በላይ ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጥም አሽባሪ ያለውን አጋች አካል በጎታችነት ከሷል፡፡

የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች አስተያየት

ዶይቼ ቬለ ከሰሞኑ አነጋግሮአቸው የነበረውን የታጋች ተማሪዎቹን ቤተሰቦች እና ጓደኞች በዛሬው እለት ባነጋገረበት ወቅት ግን የተማሪዎቹ ቤተሰቦች መሰል መረጃን ከአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ቢሰሙም የታገቱት ልጆቻቸው እስካሁንም አለመለቀቃቸውን ነው የገለጹት፡፡ ለታጋች ተማሪዋ ደህንነት ስባል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ የታጋች ተማሪ ቤተሰብ በዛሬው እለት አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ ሲሰጡ አሁንም ድረስ ታጋች ተማሪዎቹ በአጋቾች እጅ በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ ለሞትና እገታ የተጋለጡት ከጎንደር ወደ መተማ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሾፌሮች

“ልጆቹ እስካሁን አልተለቀቁም በዚያው በአጋቾች እጅ ናቸው” ያሉት አስተያየት ሰጪ የታጋች ቤተሰብ ትናንት በመገናኛ ብዙሃን የተሰራጨው መረጃ ተጨባጭነት እውነታውን ማረጋገጥ አልተቻላቸውም፡፡ ከታጋች ተማሪዎች አንዷን በአጋቾች በኩል አግኝተው ማነጋገራቸውን የሚገልጹት የቤተሰብ አባል ከመቶ በላይ ተማሪዎች እስካሁንም ድረስ በዚያው እንደሚገኙ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡

እገታው ከተፈጸመ ወዲህ አሁንም ድረስ እህታቸውን ፍለጋ ላይ መሆናቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡን የሃዋሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የሌላኛዋ ታጋች ተማሪ ወንድም በሰጡን አስተያየት ቤተሰብ በሙሉ እስካሁንም ታጋች እህታቸውን በመፈለግ ብቻ መጠመዳቸውን አስረድተዋል፡፡ “እኛ እስካሁን የት እንዳሉ በተጨባጭነት የሰማነው ነገር የለም” የሚሉት አስተያት ሰጪ እስካሁንም በእህታቸው ፍለጋ መጠመዳቸውን ገልጸዋል፡፡ መንግስት ሁኔታውን አጣርቶ ልጆቻቸውን እንዲያስለቅቅ እንደሚፈልጉ የገለጹት አስተያየት ሰጪው፤ መሳሪያ ታጥቀው ባልወጡ ንጹሃን ተማሪዎች ላይ ሊደርስ ያልተገባ ስቃይ መድረሱም የሚኮነን ተግባር ብለውታል፡፡ ትናት ተማሪዎቹን በማስመልከት በመገናኛ ብዙሃን በኩል የተሰራጨውን መረጃ በተመለከተም የመረጃውን ተጨባችነት እንዳላረጋገጡና ታጋች እህታቸው እስካሁን ድምጿ አለመሰማቱን ገልጸው መንግስት አስለቅቋቸውም ከሆነ የመጀመሪያው ተግባሩ ልጆችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክም ብሆን ማገናኘት ገባል ብለዋል፡፡ በቢሾፍቱ ከተማ በግድያ በዝርፊያና በእገታ የተሰማሩ ሁለት ሽፍቶች ተገደሉ

የታጋች ተማሪዎች ቤተሰቦች ጭንቀት

«በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በቅርቡ እና ተከታታይ እገታዎች» መከሰታቸው እንዳሳሰበው አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ትናንት ዐሳውቋል ።
«በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በቅርቡ እና ተከታታይ እገታዎች» መከሰታቸው እንዳሳሰበው አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ትናንት ዐሳውቋል ። ምስል Seyoum Getu/DW

የታጋች ተማሪዎቹ ቤተሰቦች ከዚህ በፊት የታገቱት ተማሪዎቹ እንዲለቀቁ በአጋቾች ከ300 ሺህ እስከ 700 ሺህ ብር መጠየቃቸውን ገልጸው ነበር፡፡ ይሁንና አጋቾች የጠየቁትን ገንዘብ ለመክፈል ምንም አይነት አቅም እንደሌላቸው የሚገልጹት ቤተሰቦች በከፍተኛ ጭንቀት እንደተዋጡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ “ትናንት አሁን ከአጋቾች አንዱ ደውሎልኝ አናግሬ ነበር፡፡ እኔ እህቷ ነን፡፡ እኔም ተማሪ ስለሆንኩኝ ስልክም ሽጬ ምን ብ 15 ሺኅ ብር አዘጋጀሁ ስላቸው ከፍተኛ ገንዘብ ጠየቁኝ” ብለዋል፡፡ አስተያየት ሰጪዋ በአስቸጋሪ ሁነታ ውስጥ ይገኛሉ የሚሉት የተማሪዎቹ ደህንነት በእጅጉ እነደሚያሳስባቸውም አመልክተዋል፡፡

ከእገታው ያመለጠ ተማሪ አስተያየት

እገታው በተፈጸመ እለት ታግቶ በዚያው እለት ከውስን ተማሪዎች ጋር ሆኖ ከእገታው ማምለጡን ገልጾ አስተያየቱን የሰጠን ተማሪ በፊናው ከትናንት ወዲያ ከታገቱት አንዱ ገንዘብ ከፍሎ መውጣቱን እንደነገረውና አብዛኛው ተማሪዎች ግን አሁንም ድረስ በአጋቾች እጅ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ “ከትናንት በስቲያ 30 ሺኅ ብር ለአጋቾች ከፍሎ የወጣ ጓደኛዬ አሁንም ድረስ በርካታ ታጋቾችን ከእለት እለት ከቦታ ቦታ እያንቀሳቀሱዋቸው መሆኑን አስረድቶኛል” ብለዋል፡፡

ዶይቼ ቬለ ይህንኑን ተከትሎ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ለሰሜን ሸዋ ዞን ፀጥታ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ሰለሞን አበበ፣ ለኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እና ለፌዴራል ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ኃላፊዎች ብደውልም ለዛሬ ጥረታችን አልሰመረም፡፡

ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓ.ም. አብዛኛው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚገኙበት ሦስት አውቶብሶች ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርባጉራቻ አከባቢ በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸው ተዘግቦ ነበር፡፡ ከእገታው ያመለጠው ተማሪም በግምት ከ25-30 የሚሆኑት አጋቾች በግምት ከ100 በላይ የሚሆኑት ተማሪዎቹን ይዘው ወደ ጫካ መውሰዳቸውን ተናግሯል፡፡

እገታውን ተከትሎ ከሰሞኑ መግለጫ ያወጣው አዲስ አበባ ውስጥ ያለው የአሜሪካ ኤምባሲ ያልተገባ በሚል የኮነነው ተግባሩ የተራዘመ ግጭት ውጤት ብሆንም ነገሩ አሳሳቢ ነው በማለት ግልጿል፡፡      

ሥዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ፀሐይ ጫኔ