1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቢሾፍቱ ከተማ በግድያ በዝርፊያና በእገታ የተሰማሩ ሁለት ሽፍቶች ተገደሉ

ሐሙስ፣ ሰኔ 27 2016

ባለስልጣኑ እነዚህ ግለሰቦች በጦር መሳሪያ የታገዘ ዝርፊያ እና ግድ ሲፈጽሙ እንደቆዩም አስረድተዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜ ፖሊስና የመንግስት ባለስልጣናት፣ ነጋዴዎችና የከተማው ነዋሪዎች ላይ የግድያ እርምጃ ስወስዱ እንደነበርም ነው የሚገለጸው፡፡ ባለሃቶችን በማስፈራራት ያሻቸውን በሚሊየን የሚቆጠር ብርም ስያስከፍሉ መኖራቸውን ነው የገለጹት፡፡

https://p.dw.com/p/4hstM
Äthiopien | Stadt Bishoftu
ምስል Seyoum Getu/DW

በቢሾፍቱ ከተማ በግድያ በዝርፊያና በእገታ የተሰማሩ ሁለት ሽፍቶች ተገደሉ

ከመዲናዋ አዲስ አበባ 47 ኪ.ሜ. ግድም ርቃ በምትገኘው ቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ለ20 ዓመታት ግድም ሲያስቸግር ነበር የተባለ በሽፍትነት መሰማራቱ የተገለጸ ሰዎችን የሚያግት ግለሰብ መገደሉን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡ከተማው በትናትናው እለት እንዳስታወቀው በሰዎች እገታ እና በዝርፊያ ላይ የተሰማራው ግለሰቡና ጓደኛው ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ እለት በከፍተኛ የፀጥታ ኃይሎች ክትትል ተገድለዋል። የቢሾፍቱ ከተማ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ሁሴን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት፤ ታጥቀው በሰዎች እገታና ዝርፊያ ላይ የተሰማሩ የተባሉት ግለሰቦቹ ላለፉት 20 ኣመታት በከተማዋ የተለያዩ ወንጀሎችን ሲከውኑ ቆይተዋል፡፡ “ሽፍታ” ያሏቸው እነዚህ ሰዎች ለዘመናት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው በመላው ከተማ ህዝብ ለመታወቅና ስጋት ለመሆን በቅተዋልም ነው ያሉት፡፡ቢሾፍቱ አቅራቢያ የተከሰከሰው የኢትዮጵያ አዉሮፕላን የምርመራ ዉጤት

 
“እነዚህ የሽፍታ ቡድን የሚባሉት ለየት የሚደርጋቸው እጅግ ለበርካታ ዓመታት መቆየታቸው ነው እነጂ ሽፍታ ተንቀሳቅሶ በመዝረፍ ሚታወቅ የትም ያለ ነው፡፡ እነዚህም አንዴ ሀዋሳ አንዴ ደግሞ ወደ ምንጃር እየተንቀሳቀሱ ቢሾፍቱ ከተማን ስያስቸግሩ የኖሩ ናቸው” ብለዋል፡፡ እንደ የከተማዋ ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ ኢብራሂም ማብራሪያ እነዚህ “የሽፍታ ቡድን መሪ” ያሏቸው ግለሰቦች የተገደሉት በጸጥታ አካላት ከፍተኛ ክትትል እየተደረገባቸው ከቆየ በኋላ እጅ ለመስጠት አሻፈረኝ በማለታቸው ነው፡፡

የቢሾፍቱ ከተማ
የቢሾፍቱ ከተማምስል Seyoum Getu/DW

እነዚህ ረጅም ዓመታት ጥፋት ስያደርሱ ነበር የተባሉት ግለሰቦች ለምን በጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር ማዋል እንዳልተቻለ ግልጽ አይደለም፡፡ አቶ ኢብራሂም ግን ትናንት የተገደለው መሪያቸው የሆነውና በቅጽል ስሙ ‘ምሳው’ በመባል በመላው ከተማዋ የሚታወቅና በስጋትም የሚታወቅ እንዳለማው በለጠ ሲሆን የተገደለውም ከጓደኛው ክሩቤል ግርማ ጋር ነው ብለዋል፡፡ 

ምርጫ ከአዋሽ እስከ ቢሾፍቱ
“ፖሊስ ለረጅም ጊዜ ስከታተላቸው በኋላ ነው የተገደሉት፡፡ ፖሊስ በህዝብ ጥቆማ መሰረት በቢሾፍቱ ከተማ ዱከም ክፍለ ከተማ ቤት በተከራየበት የሽፍቶቹን ኃላፊ አግኝተው እጅ እንዲሰጡ ቢጠይቋቸውም  አሻፈረኝ በማለታቸው የጸጥታ ሃይሎት በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ወታደራዊ እርምጃ ወስደውባቸው ተገድለዋል” ነው ያሉት፡፡  
ባለስልጣኑ እነዚህ ግለሰቦች በጦር መሳሪያ የታገዘ ዝርፊያ እና ግድያ ስፈጽሙ እንደቆዩም አስረድተዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜ ፖሊስና የመንግስት ባለስልጣናት፣ ነጋዴዎችና የከተማው ነዋሪዎች ላይ የግድያ እርምጃ ሲወስዱ እንደነበርም ነው የሚገለጸው፡፡ ባለሃቶችን በማስፈራራት ያሻቸውን በሚሊየን የሚቆጠር ብርም ስያስከፍሉ መኖራቸውን ነው የገለጹት፡፡ የፀጥታ አካላት ስያስሱ ቦታ በመቀያየር ለዚህ ረጅም ጊዜ መኖራቸውንም ገልጸዋል ሃላፊው፡፡“ሽፍቶቹ” በቢሾፍቱ ከተማ ዱከም ክፍለ ከተማ በሌላ ሰው ስም ቤት ተከራይተው ስኖሩ እንደነበርም ከተማው አስታውቋል፡፡ 

የቢሾፍቱ ኃይቅ
የቦሾፍቱ ኃይቅምስል Seyoum Getu/DW


የጸጥታ ኃይሎቹ የግድያ እርምጃ ከወሰዱባቸውም ለዝርፊያ ዓላማ ይጠቀሙበታል የተባለው የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች መገኘታቸውን ነው የከተማ አስተዳደሩ መረጃ ያሳየው፡፡ 
ተገድሏል ስለተባለው የሽፍታ መሪ ነው ስለተባለው ግለሰብ የከተማው ነዋሪዎች ምን ያህል ያውቃሉ በሚል ለአንድ የከተማው ነዋሪ ጥያቄ አቅርበን ነበር፡፡ “የፖሊስ መዋቅር መሃል ሆኖ እንኳ ሰወርባቸዋል ነው የሚባለው፡፡መልኩን ከቂት ሰው ውጪ አብዛኛው ሰው አያውቀውም፡፡ ምትሃታዊ ነገር አለው ተብሎ ነው የሚታወቀው” ብለዋል፡፡

የሀረ ሀር-ሰዴ የኢሬቻ በዓል በቢሾፍቱ ተከበረ
የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ ኢብራሂም ከተማው ውስጥ እየተንቀሳቀሰ የተለያዩ ወንጀሎች ሲፈጽም ቆየ ያሉት ግለሰቡ ማክሰኞ እለት በዱከም ክፍለ ከተማ ደደቻ ወረዳ ልዩ ቦታው ገብርኤል ቤተክርስቲያን ጀርባ ተከራይቶ ስኖር በነበረበት መኖሪያ ቤቱ መገደሉን ገልጸዋልም፡፡የቢሾፍቱ ከተማ በፌስቡክ ገጹ በለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስል ግድያውን ሲሰሙ ከተማዋ ነዋሪዎች ደስታቸውን ስገልጹ ይስተዋላል፡፡

ስዩም ጌቱ 

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር