1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የታኅሣሥ 8 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2016

በሻምፒዮንስ ሊግ 16ቱ ቡድኖች ድልድል ስዊዘርላንድ ኒዮን ውስጥ ዛሬ ይፋ ሆኗል። አራት ቡድኖችን በማሳተፍ ስፔን ቀዳሚ ሆናለች ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ የሊቨርፑልን ግስጋሴ ሲገታ፤ አርሰናል በአንድ ነጥብ ልዩነት የመሪነቱን ስፍራ ዳግም ተረክቧል። ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች በዓለም መድረክ ገነው የወጡበት ምክንያቱ ምን ይሆን?

https://p.dw.com/p/4aIpm
Schweiz Nyon 2023 | UEFA Champions League | Trophäe bei Achtelfinal-Auslosung
ምስል Salvatore Di Nolfi/KEYSTONE/dpa/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

በሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ፉክክር ስፔን አራት ቡድኖችን፤ ጀርመን እና ጣሊያን ሦስት ሦስት ቡድኖችን አሰልፈዋል ። እንግሊዝ ሁለት ቡድኖች ለጥሎ ማለፉ ሲያልፉላት፤ ቀሪዎቹ ፈረንሣይ፣ ኔዘርላንድ፣ ፖርቹጋል እና ዴንማርክ አንድ አንድ ቡድን አላቸው ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባለፈው ሳምንት ጉድ የሆነው ባየርን ሙይንሽን ሲጠበቅ በነበረው የትናንቱ ግጥሚያ በአስተማማኝ መልኩ አሸንፏል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ የሊቨርፑልን ግስጋሴ ሲገታ፤ አርሰናል በአንድ ነጥብ ልዩነት የመሪነቱን ስፍራ ዳግም ተረክቧል።  ማንቸስተር ሲቲ በቅርብ ርቀት ከዋንጫ ፉክክሩ አልወጣሁም ብሏል ። ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች በዓለም መድረክ ገነው የወጡበት ምክንያቱ ምን ይሆን? ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። 

አትሌቲክስ፦

የጎርጎርጎሪዮሱ 2023 ሊጠናቀቅ ከሁለት ሳምንት በታች ብቻ ይቀረዋል ። በሚገባደደው 2023 ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይ ሴቶች አትሌቶቻችን በዓለም የስፖርት መገናኛ አውታሮች በከፍተኛ ደረጃ ስማቸው ገኖ ሲነሳ ነበር ። ከእነዚህ አትሌቶች መካከል፦ የቤርሊን ማራቶን ላይ ክብረወሰን በመስበር ታሪክ ያስመዘገበችው አትሌት ትእግስት አሰፋ ትገኝበታለች ። ትእግስት የቤርሊን ማራቶንን ከ2 ሰከንዶች ማሻሻሏ ከዐርባ ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ነው ።

ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ፦ የዓለም አትሌቲክስ ምርጥ አትሌቶችን ለመምረጥ ባደረገው የድምፅ አሰጣጥ ለጥቂት አምስቱ ውስጥ ሳትገባ የቀረች ድንቅ አትሌት ነች ። ጉዳፍ በቡዳፔስት ሐንጋሪ የዓለም አትሌቲክስ ከእጃችን ሊወጣ ከጫፍ ደርሶ የነበረውን የ10,000 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ታግላ ወደ ኢትዮጵያ አስመልሳለች ። 

ኢትዮፕያውያን አትሌቶች በቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ  የ10,000 ሜትር ውድድር አሸንፈው
ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች ጉዳፍ ጸጋዬ (ከመሀል) ወርቅ፤ በስተግራ ለተሰንበት ግደይ ብር እንዲሁም ከግራ ደግሞ እጅጋየሁ ታየ የነሐስ ሜዳሊያ በቡዳፔስት የዓለም አትሌቲክስ የ10,000 ሜትር ውድድር አሸንፈው። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Antonin Thuillier/AFP

በዚሁ ውድድር አትሌት ለተሰንበት ግደይ በበኩሏ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ነበረች በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ሆላንዳዊ የሆነችው እና ብርቱ ተፎካካሪዋ አትሌት ሲፋን ሐሰንን ከወደቀችበት ሄዳ አንስታታለች ። በወቅቱ ላደረገችው መልካም ምግባርም ለሽልማት በቅታለች ።  በዓለም መድረክ ለድል ከመብቃትም ባሻገር የስፖርታዊ ጨዋነት ሽልማት አሸናፊ በመሆን የዓለማችን ድንቅ አትሌት መሆኗን አስመስክራለች ። በሚገባደደው 2023 አትሌቶቻችን በዓለም መድረክ ተሳትፎ እና እንቅስቃሴያቸው ምን ይመስል ነበር? በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ኤፍ ኤም ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥጋናው ታደሰ ።

 የታኅሣስ 1 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ ድልድል

በሻምፒዮንስ ሊግ በደርሶ መልስ ጥሎ ማለፍ የሚወዳደሩት 16ቱ ቡድኖች ድልድል ስዊዘርላንድ ኒዮን ውስጥ ዛሬ ይፋ ሆኗል ። ወደ ጥሎ ማለፉ ከተሻገሩ 16 ቡድኖች መካከል አራት ቡድኖችን በማሳተፍ ስፔን ቀዳሚ ሆናለች ። ባርሴሎና ከጣሊያኑ ናፖሊ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ ከጣሊያኑ ኢንተር ሚላን፤ ሪያል ማድሪድ ከጀርመኑ ላይፕትሲሽ እንዲሁም ሪያል ሶሲዬዳድ ከፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞ ጋ ለማጋጠም ስፔን አራት ቡድኖችን አሰልፋለች ።

ጀርመን ሦስት ቡድኖች ይዛ ትከተላለች ። ከጀርመን ቡድኖች መካከል ላይፕትሲሽ በእጣ ድልድሉ ከባዱ የሪያል ማድሪድ ቡድን ደርሶታል ። በምድባቸው አንደኛ ሆነው ያጠናቀቁት ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ባየርን ሙይንሽን በእጣው በአንጻሩ የተሻለ ቡድን ደርሷቸዋል ።   ባለፈው ሳምንት ከፓሪ ሳንጃርሞ ጋ አንድ እኩል ተለያይቶ የምድቡ መሪ ሆኖ ያለፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ በጥሎ ማለፉ የኔዘርላንዱ ፒኤስቪ አይንድሆቨን ደርሶታል ። ባዬርን ሙይንሽን የጣሊያኑ ላትሲዮን ይገጥማል ። 

ከምስጋናው ጋ የተደረገው ሙሉ ቃለ መጠይቅ እዚህ ይገኛል

የእንግሊዞቹ አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ከፖርቹጋሉ ፖርቶ እና፤ ከዴንማርኩ ኮፐንሀገን ጋር ይፋለማሉ ።  የመጀመሪያው ዙር የጥሎ ማለፍ ውድድሮች ማክሰኞ የካቲት 5፣ 6 እንዲሁም በሳምንቱ 12 እና 13 ይከናወናሉ ። ሁለተኛ የመልስ ግጥሚያዎች ማክሰኞ የካቲት 26 እና በነጋታው 27 እንዲሁም በሳምንቱ መጋቢት 3 እና 4 ይከናወናሉ ።  የአውሮጳ ሊግ እጣ ድልድልም ዛሬ ይፋ ሆኗል ። 

እግር ኳስ

ባለፈው ሳምንት «የባየርን ሙይንሽንን አምድ ነቀነቀው» በሚል በጀርመን የስፖርት ጋዜጦች አድናቆት የተቸረው አይንትራኅት ፍራንክፉርት ትናንት በባዬር ሌቨርኩሰን የ3 ለ0 ሽንፈት በተራው ተነቅንቋል ። በአንጻሩ ባዬርን ሙይንሽን ሽቱትጋርትን 3 ለ0 ድል አድርጎ የሽንፈት ሞራሉን አድሷል ። ይኼም ትናንት ነበር በአሊያንትስ አሬና ስታዲየም ። በባዬር ሌቨርኩሰን በ39 ነጥብ ደረጃውን ይመራል ። ባየርን ሙይንሽን በ35 ይከተላል ። 32 ነጥብ ይዞ በቡንደስሊጋው ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ ቅዳሜ ዕለት ሆፈንሀይምን 3 ለ1 ድል አድርጓል ። ሽቱትጋርት በ31 ነጥብ የአራተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ 26 ነጥብ ሰብስቦ አምስተኛ ነው ። ከትናንት በስትያ አውግስቡርግን ገጥሞ አንድ እኩል ተለያይቷል ።  ኮሎኝ በ10፤ ማይንትስ እና ዳርምሽታድት በ9 ነጥብ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ደረጃ ላይ ይቃትታሉ ።

የባየር ሙይንሽን እንግሊዛዊ አጥቂ ግብ አዳንነቱ ቀጥሏል
የባየር ሙይንሽን እንግሊዛዊ አጥቂ ግብ አዳንነቱ ቀጥሏል ። ሽቱትጋርትን ባሸነፉበት የእሁድ ታኅሣሥ 7ቀን፤ 2016 ዓ.ም ግጥሚያ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል ። ምስል Michaela Rehle/AFP/Getty Images

የኅዳር 24 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዘንድሮ ከጀርመኑ በተለየ የነጥብ ፉክክሩ እጅግ ተቀራራቢ በሆነ መልኩ ቀጥሏል ። በመሪው አርሰናል በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጠው የሚከተሉት ሊቨርፑል እና አስቶን ቪላ 38 ነጥብ ሰብስበዋል ። ማንቸስተር ሲቲ እና ቶትንሀም 34 እና 33 ነጥብ ይዘው አራተኛ እና አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። 

ፕሬሚየር ሊግ

ሊቨርፑል ትናንት በሜዳው አንፊልድ ማንቸስተር ዩናይትድን በጨዋታ ቢበልጥም ያለምንም ግብ ነጥብ ተጋርቶ ተለያይቷል ። ማንቸስተር ዩናይትድ አብዛኛውን ጊዜ  በመከላከል ላይ አተኩሮ መቆየቱ ከሽንፈት ታድጎታል ። ለአርሰናል ደግሞ የገና ሰሞን እፎይታ ሰጥቶታል ። ሊቨርፑል ትናንት ቢያሸንፍ ኖሮ ደረጃውን በ40 ነጥብ መሪ ሆኖ ይቆጣጠር ነበር ። አርሰናል ትናንት ብርቱ ተፎካካሪ የነበረው ብራይተንን 2 ለ0 አሸንፏል ። የማንቸስተር ዩናይትድ፣ እንዲሁም አስቶን ቪላ 2 ለ 1 ብሬንትፎርድን ባሸነፈበት ጨዋታ ከሦስቱም ቡድኖች ሦስት ተጨዋቾች በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተዋል ።  ዌስትሀም ዩናይትድ ዎልቨርሀምፕተንን፤ ኒውካስል ፉልሀምን 3 ለ0 አሸንፈዋል ።

የሊቨርፑል አጥቂ ሉዊስ ዲያዝም ሆኑ ሌሎቹ ቡድኑን ነጥብ ከመጣል አልታደጉም
ሊቨርፑል ትናንት በሜዳው አንፊልድ ማንቸስተር ዩናይትድን በጨዋታ ቢበልጥም ያለምንም ግብ ነጥብ ተጋርቶ ተለያይቷል ። አጥቂው ሉዊስ ዲያዝም ሆኑ ሌሎቹ ቡድኑን ነጥብ ከመጣል አልታደጉም ምስል Rui Vieira/AP/dpa/picture alliance

የፉልሀም አንድ ተጨዋችም የቀይ ካርድ ሰለባ ሆኗል ። ኤቨርተን በርንሌይን፤ ቸልሲ ሼፊልድ ዩናይትድን፤ እንዲሁም አንድ ተጨዋቹ በቀይ ካርድ የተሰናበተበት ቶትንሀም ኖቲንግሀም ፎረስትን 2 ለ0 ማሸነፍ ችለዋል ። የሉቶን ታወን እና የበርመስ ጨዋታ 65ኛ ደቂቃ ላይ አንድ እኩል ሳሉ ተቋርጧል ።  የሉቶን ታወን አምበል   ቶኒ ሎኪየር የልብ ምቱ በመቋረጡ ሜዳው ውስጥ ተዝለፍልፎ መውደቁ በርካቶችን አስደንግጧል ። ተጨዋቹ በዚህ መልኩ ሜዳ ላይ ሲዝለፈለፍ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑም ተዘግቧል ።

ኬንያ የ2024 ን የአፍሪቃ ዋንጫ ከታንዛኒያ እና ከኡጋንዳ ጋ በትብብር እንደምታዘጋጅ ዛሬ ይፋ ሆኗል ። በአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ቀደምቷ ኢትዮጵያ በስታዲየም የጥራት መስፈርት ጉድለት ተጨዋቾቿ ከሀገር ሀገር ለግጥሚያ ይንከራተታሉ ። በመጪው ጥቅምት ወር በሚካሄደው ግጥሚያ አፍሪቃ ውስጥ ያሉ ተጨዋቾችን ብቻ በማሰለፍ 16 ሃገራት ይሳተፉበታል ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ