1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኅዳር 24 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ኅዳር 24 2016

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስፔን ውስጥ ትናንት በቫለንሺያ ማራቶን በወንዶችም በሴቶችም አመርቂ ድል አስመዝግበዋል ። ድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ የጀርመን ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ማንሳት ችሏል ። የኢትዮጵያ ጁዶ ፌፌሬሽን ምሥረታ ውዝግብ አስነስቷል ። የሚመለከታቸውን አናግረናል ።

https://p.dw.com/p/4ZlKb
እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ የጀርመን ቡድን
እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ የጀርመን ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ማንሳት ችሏል ምስል Achmad Ibrahim/AP Photo/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ስፔን ውስጥ ትናንት በቫለንሺያ ማራቶን በወንዶችም በሴቶችም አመርቂ ድል አስመዝግበዋል ። በውድድሩ እንደ እነ አትሌት ቀነኒሳ እና ዓልማዝ አያና እጅግ ተጠብቆ የነበረው ዩጋንዳዊ አትሌት ጆሹዋ ቼፕቴጊ 37ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ። እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ የጀርመን ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ማንሳት ችሏል ። ጀርመን በምታዘጋጀው የአውሮጳ እግር ኳስ ውድድር የምድብ ድልደላ እጣ ወጥቷል ። ጀርመን በመክፈቻው ስኮትላንድን ትገጥማለች ። ስፔን እና ጣሊያን ያሉበት ድልድል ጠንካራ ምድብ ከተባሉት ውስጥ ይገኛል ።  የኢትዮጵያጁዶ ፌፌሬሽን ምሥረታ ውዝግብ አስነስቷል ። 

በቫለንሺያ ማራቶን የኢትዮጵያውያን ድል

ስፔን ውስጥ እሁድ ኅዳር 23 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በተከናወነው የቫለንሺያ ማራቶን ፉክክር ኢትዮጵያውያን በወንድም በሴትም ድል ተቀዳጅተዋል ። ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች  ወርቅነሽ ደገፋ፤ ዓልማዝ አያና እና ሕይወት ገብረ ኪዳን ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ተከታትለው በመግባት ደማቅ ድል አስመዝግበዋል ። ወርቅነሽ ውድድሯን በአንደኛነት ለማጠናቀቅ የፈጀባት  2:15:51 ነው ። አልማዝ ከ31 ሰከንዶች፤ ሕይወት ከ2 ደቂቃ ከ8 ሰከንዶች በኋላ ተከታትለው ገብተዋል ።

የኅዳር 17 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በወንዶች ፉክክር ሁለተኛ እና ዘጠነኛ ላይ ኬንያዊ እና ፈረንሳዊ አትሌቶች ጣልቃ ከመግባታቸው በስተቀር ከአንደኛ እስከ ዐሥረኛ በኢትዮጵያውያን ተይዟል ። ውድድሩን ኢትዮጵያዊው አትሌት ሲሳይ ለማ 2:01:48 በመሮጥ አሸንፏል ። ዳዊት ወልዴ ኬኒያዊው አሌክሳንደር ሙቲሶን ተከትሎ ለጥቂት ሦስተኛ ወጥቷል ። ዳዊት የገባበት 2:03:48 ጊዜ ከአሌክሳንደር በ37 ሰከንድ ብቻ ነው ልዩነቱ ። በዚህ ውድድር ቀነኒሳ በቀለ 2:04:19 በመሮጥ አራተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል ።  

በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፦ እሁድ በነበሩ ጨዋታዎች ማንቸስተር ሲቲ ከቶትንሀም ጋ  ሦስት እኩል፤ በርመስ ከአስቶን ቪላ ሁለት እኩል እንዲሁም ዌስትሀም ከክሪስታል ፓላስ ጋ አንድ እኩል ተለያይተው ነጥብ ተጋርተዋል ። ሊቨርፑል ፉልሀምን 4 ለ3 ድል አድርጎ  ነጥቡን 31 በማድረስ የሁለተኛ ደረጃውን ከማንቸስተር ሲቲ ተረክቧል ።  ልዩነታቸው የአንድ ነጥብ ነው ።  ቅዳሜ ዕለት ዎልቨርሀምፕተንን 2 ለ1 ያሸነፈው አርሰናል በ33 ነጥብ የፕሬሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥን ይመራል ።

የቫለንሺያ ማራቶን
የቫለንሺያ ማራቶን፤ በ2021 ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል Meurer/BEAUTIFUL SPORTS/imago images

በጀርመን ቡንደስሊጋ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋ ትናንት አንድ እኩል የተለያየው ባዬር ሌቨርኩሰን የደረጃ ሰንጠረዡን በ35 ነጥብ ይመራል ። ከዑኒዬን ቤርሊን ጋ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ባዬር ሙይንሽን በ32 ነጥብ ይከተላል ። ቅዳሜ ዕለት ቬርደር ብሬመንን 2 ለ0 ያሸነፈው  ሽቱትጋርት 30 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ሐይደንሀይምን 2 ለ1 ያሸነፈው ላይፕትሲሽ እና ዶርትሙንድ በ26 እና 25 ነጥብ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ተከታትለው ሰፍረዋል ።

የጀርመን አዳጊ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ አነሳ

እድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ የጀርመን ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ ማንሳት ችሏል ። የጀርመን ቡድን ቅዳሜ ዕለት በፍጻሜ ግጥሚያው ከፈረንሳይ አቻው ጋ ሁለት እኩል ተለያይቶ በመለያ ምት 4 ለ3 ማሸነፍ ችሏል ። የጀርመን ዋናው ብሔራዊ ቡድን በሚንገታገትበት በአሁኑ ወቅት አዳጊ ቡድኑ የመጀመሪያ ዋንጫውን ማንሳቱ በብዙዎች ዘንድ መነቃቃትን ፈጥሯል ።

የኅዳር 10 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ጀርመን በምታዘጋጀው የአውሮጳ እግር ኳስ ውድድር የምድብ ድልደላ እጣ ቅዳሜ ዕለት ወጥቷል ። ጀርመን በመክፈቻው ስኮትላንድን ትገጥማለች ። በምድቡ ሐንጋሪ እና ስዊትዘርላንድም ይገኙበታል ። ስፔን እና ጣሊያን ያሉበት ድልድል ጠንካራ ምድብ ከተባሉት ውስጥ ይገኛል ። በዚህ ምድብ ክሮሺያ እና አልባንያም አሉበት ። ምድብ «ሐ» ውስጥ ስሎቬኒያ፣ ዴንማር፣ ሰርቢያ እና እንግሊዝ ይገኛሉ ። በምድብ «መ» ኔዘርላንድ፤ ኦስትሪያ እና ፈረንሳይ ሲገኙ፤ ከዌልስ፤ ፊንላንድ፤ ፖላንድ እና ኤስቶኒያ አንዱ አሸናፊ ይህን ምድብ ይቀላቀላል ። ይህም ከባዱ ምድብ ነው ።  በምድብ «ሠ» ቤልጂየም፣ ስሎቫኪያ እና ሮማኒያ እንዲሁም በምድብ «ረ» ቱርኪዬ፣ ፖርቹጋል እና ቼክ  አንድ አንድ ቡድን ይቀላቀላቸዋል ።

በኢትዮጵያ የጁዶ ፌዴሬሽን ምስረታ አወዛግቧል

በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የተመሠረተው የጁዶ ፌዴሬሽን ከሕግ እና ከመመሪያ ውጪ ነው የሚል ቅሬታ ተሰነዘረበት ። ቅሬታ አቅራቢዎች፦ ፌዴሬሽኑ የኦሮሚያ ክልል እና ድሬዳዋ የተገለሉበት የአማራ ክልል ጭራሽ ያልተጋበዘበት አግላይ ነው ብለዋል ። የኢትዮጵያ ባሕል እና ስፖርት ሚንስትር በበኩሉ ፌዴሬሽኑ በተገቢው ሁኔታ ጥናት ተደርጎ የተቋቋመ ነው ሲል ተከራክሯል ። ከቅሬታ አቅራቢዎች መካከል በፌዴሬሽኑ ውስጥ ለፕሬዝዳንትነት ተወዳድሮ በመውደቁ፤ አለያም ፌዴሬሽኑ ውስጥ ሥልጣን ለማግኘት ሕጉ የማይፈቅድላቸው ሰዎች ይገኙበታል ብለዋል ። ቅሬታ አቅራቢዎቹ ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ እንኳን ፌዴሬሽን ሳይኖር፤ የኢትዮጵያ ፌዴሬሽንን አቋቋምን ማለት ለተለየ የግል ጥቅም የታሰበ ሕገወጥ ተግባር ነው ሲሉ ሞግተዋል ።   

አሰልጣኝ ሠይፉ መኮንን በኦሮሚያ ክልል እና አዲስ አበባ የጁዶ ፌዴሬሽን መስራቾች ከሆኑት መካከል አንዱ ናቸው ። በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ጁዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚደት ሆነውም ያገለግላሉ ። የጁዶ ስፖርት ኢትዮጵያ ውስጥ ረዥም እድሜ የማስቆጠሩን ያህል የተጠቀሰውን ያህል በቂ ሰልጣኞች የሉትም ሲሉ ቅሬታ ያቀርባሉ ።  ፌዴሬሽኑ ሲመሠረትም ከሌሎች የትግል ስፖርት አይነቶች ስፖርተኞችን በማምጣት ስለሆነ ምሥረታው ተገቢ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ ።

«የሌላ ስፖርት ባለሞያዎች፤ የጁትኩንዱ፤ የአይቲኤፍ ያሉትን ቁጥር በማስገባት ቁጥሩን ከፍ ማድረግ አይቻልም ። ምክንያቱም ስፖርቱ ለያንዳንዱ የሚገባው ስርዓት እና ሕግ ስላለው ። ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ካለው ዕድሜ ጠገብነት አዘውታሪው ቁሳቁስ ፤ መለማመጃ ምንጣፍ፤ ከምንም በላይ ደግሞ ዕውቀት ያስፈልገዋል ። ይህ ዕውቀት በሌለበት እና ዝም ብሎ በስመ ጁዶ አቋቁመናል በሚል የግል ሥልጣን ለማግኘት የበዛበት ስፖርቱ በማይዘወተርባቸው፤ ስፖርቱ አለ ተብለው ስፖርቱን በማያውቁት ክልሎች አሉ ተብለው የስፖርቱን ፌዴሬሽን ለማቆም እና በማይሆን መንገድ ለመበልጸግ የተጀመረ የጁዶ አደረጃጀት ነው ።»

ቡርኪናፋሶ ኢትዮጵያን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ አሸነፈች

አሰልጣኝ ሠይፉ፦ የጁዶ ፌዴሬሽን ምሥረታ ሲደረግ 5,500 ሠልጣኞች አሉ የተባለው ሐሰት ነው ብለዋል ።

ዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን
ዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን ዓርማምስል Jonas Güttler/dpa/picture alliance

አምባሳደር መሥፍን ቸርነት በባሕል እና ስፖርት ሚንስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ናቸው ። ጁዶ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ ሕጋዊ መሠረቱን ጠብቆ አይደለም የተመሠረተው የሚል ቅሬታ መቅረቡን መሠረተ ቢስ ብለዋል ።  ጥያቄው በእርግጥ በቀጥታ መቅረብ ያለበት በስፖርት ማኅበራት አደረጃጀት መሰረት ሥራውን በቀጥታ የሚከታተለው በባሕል እና ስፖርት ሚንስቴር የስፖርት ማኅበራት ድጋፍ እና ቁጥጥር የሥራ አስፈጻሚ ዘርፍ እንደሆነ ገልጸዋል ።  በበኩላቸው ግን ፌዴሬሽኑ ሕጉን መሠረት አድርጎ ተቋቁሟል ብለዋል ። 

«እኛ ዕስከምናውቀው ድረስ ከአምስት በላይ ክልሎች እንደራጅ ብለው ጥያቄ አቅርበው፤ ጥያቄያቸውን ደግሞ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰይመው፤ ሥራውን የሚያስመርጥ አስመራጭ ነገር በሕጋዊ መንገድ ተሰይሞ እያንዳንዱ ክልል የሚያቀርበው እጩ ተመርምሮ፤ ታይቶ ለዚህም ደግሞ በአየር ላይ በቂ የሆነ ጊዜ ተሰጥቶ፤ እያንዳንዱ እጩ ማን ነው? ከየት ክልል ነው የመጣው? በኢትዮጵያ ስፖርት ሕግ መሰረት ሊመረጥ ይችላል ወይንስ አይችልም የሚለው ነገር ተጣርቶ ለይግባን ጊዜ ጭምር በአየር ላይ ጥያቄ ቀርቦ ይህንን አልፎ ነው ብሔራዊ የስፖርት ማኅበራት የሚደራጀው እንጂ ዝም  ብሎ ከሩቅ ሆኖ ችግር ይሆናል ብለው የሚያስቡትን  ነገሮች በማንሳት የሚሆን አይደለም ። ስለዚህ ጠቅለል አድርጌ ስነግርህ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያውቀ፤ በሕጋዊ አሠራር የስፖርት ማኅበራት መመሪያ 907/2014ን መሠረት ያደረገ አዲስ የስፖርት የጁዶ ፌዴሬሽን ተመስርቷል በሕጋዊ መንገድ ነው የምልህ ።»

አሠልጣኝ ሰይፉ በበኩላቸው፦ የጁዶ ስፖርት አደራጅ ኮሚቴ ሲቋቋም ምክትል ሰብሳቢ እንደነበሩ በመግለጽ፦ በወቅቱ «የተባባልነው ስፖርቱን አደራጅተን ወደፊት ፌዴሬሽን እንሆናለን እንጂ ፌዴሬሽን እናቋቁማለን የሚለው አልነበረም» ሲሉም ተቃውሞዋቸውን ገልጸዋል ። ፌዴሬሽን ለማቋቋም ጊዜው አለመሆኑንም አብራርተዋል ።  

«በኢትዮጵያ ፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን አደረጃጀት መሰረት በአምስት ክልል ፌዴሬሽን ሆኖ፤ ዳኛ እና ቡድን ያለው ይላል ። ግን ምንም ዳኛም ሆነ ቡድን ወይንም አሰልጣኝ የሌላቸው ፌዴሬሽን ሆነው መጥተዋል ። ለሚንስትር ዴኤታውም ቅሬታችን አቅርበናል ። የሚፈለገውን መልስ ደግሞ እየጠበቅን ነው ። ቢያንስ በአምስት ክልል ከ250 በላይ ሰልጣኞች ያስፈልጋሉ ። እንደገና ደግሞ ቢያንስ በአንድ ክልል አሰልጣኞች ዐሥር፤ ዳኞች 15 ያስፈልጋሉ፤ አባላት ሙሉ 250 ይላል ።  አሁን እኔ ክልል መጥራት ስለማልፈልግ ነው እንጂ፤ ስፖርቱ ጁዶ ብለህ ብትጠይቃቸው ኳስ የሚያመጡልህ ክልሎች ስፖርቱ አለ ብለው ቀጥታ ኃላፊነታችን ነው ብለው ተቀብለው ገብተዋል ። ግን ዝቅ ብለህ እታች ስታይ ስፖርቱ ዐይታወቅም ።»

አዲስ አበባ እንኳን ፌዴሬሽን አለመኖሩን፤ አምስት አሰልጣኞች ብቻ እንደነበሩ፤ አደራጅ ማኅበር ተብሎ የተቋቋመው በ2014 መሆኑን አብራርተዋል ። ማኅበር እንኳን የሆነው ባለፈው ዓመት በ2015 ነው፤ ፌዴሬሽን የሚለው ከየት እንደመጣ እንጃ ሲሉም አክለዋል ።   

የጁዶ ስፖርት ስልጠና በኢትዮጵያ
የጁዶ ስፖርት ስልጠና በኢትዮጵያ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል privat

የጥቅምት 27 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

አምባሳደር መሥፍን ቅሬታ በማንኛው ጊዜ መቅረብ እንደሚቻል በመግለጽ ለስፖርቱ ቀና አስተሳሰብ እና ጥሩ አመለካከት ቢኖር ኖሮ በምርጫ ሒደቱ ወቅት ቀደም ብሎ ቅሬታ ማቅረብ ይቻል ነበር ብለዋል ። አብረው ሥራውን ሲሠሩ የነበሩ ሰዎች፦ «ወደ ውድድር ከገቡ በኋላ በተፈጠረ ያለመግባባት የተፈጠረ ነው»  ብለዋል ውዝግቡን በተመለከተ ። አያይዘውም፦ የኢትዮጵያ ጁዶ ፌዴሬሽን ምሥረታ ከመከናወኑ በፊት ቀደም ሲል ሌላ «ጁዶ እና ጁጂትሱ» የሚባል ፌዴሬሽን በስፖርት ማኅበራት ሕግ ሳይሆን በሲቪል ማኅበራት ሕግ ድጋፍ ከሲቪል ማኅበራት ወስዶ ከተመሰረተ መቆየቱንም ጠቅሰዋል ። ዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽንም መመዝገቡን አክለዋል ።  ሆኖም ሲቪል ማኅበር ሆነው በዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን መመዝገባቸው ዋናው ችግር የተፈጠረው በዚህ ምክንያት ነው በማለት ጉዳዩ የሀገር ሉዓላዊነትንም የሚመለከት ነው ብለዋል ።

«በዚህ አጋጣሚ ላነሳልህ የምችለው የዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን አባል የመሆን መብት የላቸውም ። የዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን የስፖርት ማኅበር እንጂ የሚመዘግበው የሲቪል ማኅበርን አይደለም የሚመዘግበው ።  በመሠረቱ ይህ ትክክል አይደለም ። እና እነ ዶ/ር ፀጋዬን እና በዚያ ደረጃ ያሉትን የጀርመን የስፖርት ቤተሰቦች እንፈልጋቸዋለን አብረን ተጋግዘን መሥራት እንፈልጋለን ። ለኢትዮጵያ ጁዶ መልማት አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን ። ግን ዋናው መጀመሪያ ድጋፍ ሊያደርጉ ከእኛ ጋ ነው እንጂ መሆን ያለባቸው የኢትዮጵያን መንግሥት ወክለናል ብሎ ፤ የኢትዮጵያን ስፖርት ወክለናል ብለው በዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን መወከል፣ መቀመጥ እንዴት ሊፈቀድ ይችላል? ይኼ እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ የሶቨርኒቲ ጥያቄ ነው ። የሉዓላዊነት ጥያቄ ነው ። የኢትዮጵያን ስፖርት ተጻሮ፤ የሆነ አካል፤ ሌላ ሀገር ዜግነት ያለው አካል ተባብሮ በኢትዮጵያ መንግሥት፤ በኢትዮጵያ ስፖርት ስም የሆነ ቦታ ላይ ተመዝግቦ ቁጭ ማለት ። »

ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል በጀርመን ሀገር በአንድ የተሽከርካሪ ኩባንያ በዳይቨርሲቲ እና አካታችነት ዘላቂነት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ ይገኙበታል ። በዓለም አቀፍ የጁዶ ፌዴሬሽን የአፍሪቃ ጁዶ የፕሮሞሽን ኮሚሽን ናቸው ። በዓለም አቀፍ ጁጂትሱ ፌዴሬሽን  የሥነ ምግባር እና ዘላቂነት ምክትል ፕሬዚደንትም ናቸው ።

ከጀርመናዊው ባለ 7 ዳን ዮሐንስ ዳክስባህር ጋ ለኢትዮጵያ የባሕል እና ስፖርት ሚንስትር ጥቅምት 23፣ ቀን 2016 ዓ.ም በጻፉት ደብዳቤ የፌዴሬሽኑ አግላይነት በመግለጽ እንደ አሰልጣኝ ሠይፉ ሁሉ አብራርተዋል ። «ኢ-ፍትኃዊ እና ወገናዊ የሆነ ችኩል» ያሉት አካሄድ «በአስቸኳይ» እንዲቆም እና «የጠለቀ ምርመራ» እንዲካሄድ ጠይቀዋል ። የደብዳቤያቸውን ግልባጭ ለጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት፤ ለኢትዮጵያ አገር አቀፍ ስፖርት ምክር ቤት፣ ለክልል ስፖርት ጽ/ቤቶች እንዲሁም ቤርሊን ለሚገኘው ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ማስገባታቸውን ገልጸዋል ።  ስለተነሳባቸው የሉዓላዊነት ጥያቄ ሲመልሱም፦ «ብዙም ክብደት የሚያነሳ አይደለም» ብለዋል ። ከዓመታት በፊት ጁዶና ጁጂትሱ ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ በወቅቱ የነበረው መመሪያ ነው ብለዋል ። መመሪያው አምስት ፌዴሬሽን ይል ስለነበረ እና ያን ማድረግም ስላልተቻለ በወቅቱ የነበሩት የስፖርት ባለሥልጣናት በመከሩት መሰረት ተወስዶ በሲቪክ ማኅበራት መመዝገቡን አብራርተዋል ። ለዚያ ደግሞ የተጻጻፉዋቸው ደብዳቤዎች መኖሩን አክለዋል።  ከፊል ደብዳቤዎቹንም የስፖርት ክፍላችን ተመልክቷል ። ዶ/ር ጸጋዬ ማብራራታቸውን ይቀጥላሉ ።

ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ
ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ የጁዶ ስፖርት ስልጠና ሲሰጡ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል privat

«የዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን ይህን ሁሉ ያውቃል ። ከፍትሕ ሚንስትር ፈቃድ እንዳለው ያውቃል ። የዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን በኢትዮጵያ ስፖርቱን ይሄ መተዳደሪያ ደንቡን ካየነው ስፖርቱን ለማዳበር የሚሆን ነው ። ወደ ፌዴሬሽንነት ለማሳደግ፤ ለማዳረስ እንደሆነ ያውቃል ይህንን እንጂ የዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን አንድ ትምሕርት ቤት አባል መሆን ይችላል፤ አንድ ቡድን አባል መሆን ይችላል፤ አንድ ማኅበር አባል መሆን ይችላል ። እነሱ ራሳቸው ናቸው የሚመርጡት እና  ሲቪክ ሆነ ስፖርት ሆነ  ሳይሆን እነሱ ራሳቸው በሚመርጡት የሚሆን ነገር ነው ። በነገራችን ላይ ይህንን በምናይበት ሰአት ትውልደ ኢትዮጵያዊ ጀርመን ምናምን የሚባል ነገር አለ ። እኔ ድሮ የቦርድ አባል ሲመሠረት ከላይ በቦርድ አባል የበላይ ጠባቂ በነበርሁበት ሰአት የኢትዮጵያ ዜግነት ያለኝ ሰው ነበርሁ እስከሚቀጥሉትም ጊዜያቶች ድረስ ። እና ከጀርመን ጋ ሉዓላዊነት የሚለው ነገር ብዙም ክብደት የሚያነሳ አይደለም፤ ጊዜም ወስዶ እዚህ ላይ ብዙ መነጋገር ያስፈልጋል ።»

 የጥቅምት 19 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

አምባሳደር መሥፍን አዲስ ስለተቋቋመው የኢትዮጵያ ጁዶ ፌዴሬሽን ጉዳይ ለዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን መቅረቡን ገልጸዋል ። ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ ስም የተመዘገበ ሌላ ፌዴሬሽን ስላለ ሁለት ፌዴሬሽን እንዴት ሊሆን ይችላል የሚል ጥያቄ ማቅረቡንም አክለዋል ። ጉዳዩን ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽኑ እንዲረዳ የማድረግ ጥረት እንደሚቀጥልም ገልጸዋል ። አሰልጣኝ ሠይፉ ቅሬታ አቅርበው መልስ እየጠበቁ መሆኑን «ካልሆነ በሕግ» አግባብ የሚሄዱበትን ሁኔታ እየተነጋገሩበት መሆኑን ገልጸዋል ። በሌላ በኩል የባሕል እና ስፖርት ሚኒስቴር የቀረቡለትን ቅሬታዎች እየተመለከተ መሆኑም ተዘግቧል ።  አዲስ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ጁዶ ፌዴሬሽን በዓለም አቀፍ ጁዶ ፌዴሬሽን እስካሁን ድረስ ዕውቅና አለማግኘቱም ታውቋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ