1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስሰሜን አሜሪካ

የቲክ ቶክ ዕገዳ አሜሪካውያንን እያወዛገበ ነው

ረቡዕ፣ መጋቢት 11 2016

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባለፈው ሳምንት ቲክቶክን በመላ ሀገሪቱ ለማገድ የሚያስችል ረቂቅ ህግ ይፋ አድርገዋል።የባይት ዳንስ ኩባንያ ንብረት የሆነው እና በአሜሪካ 170 ሚሊዮን የሚደርሱ ተጠቃሚዎች ያሉትን ቲክቶክን፤አሜሪካ ለምን ማገድ ፈለገች?

https://p.dw.com/p/4duaI
ቲክ ቶክ በአሜሪካ ወደ 170 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎች አሉት
ቲክ ቶክ በአሜሪካ ወደ 170 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎች አሉትምስል Joly Victor/abaca/picture alliance

አሜሪካ ቲክቶክን ለምን ማገድ ፈለገች?


የአሜሪካ የህዝብ እንደራሴዎች የቻይናው ኩባንያ የባይትዳንስ ንብረት የሆነውን ቲክ ቶክ፤  እንዲሸጥ ግፊት የሚያደርግ ውሳኔ ባለፈው ሳምንት አስተላልፈዋል።ይህ ካልሆነ ግን በመላው አሜሪካ መተግበሪያው በስድስት ወራት ውስጥ ይታገዳል።ታዋቂው የአጫጭር የቪዲዮ መተግበሪያ ቲክ ቶክ በዩናይትድ ስቴትስ የሕግ አውጭዎች ፊት ሲቀርብ በአራት ዓመታት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ከጎርጎሪያኑ 2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት ባይትዳንስ መተግበሪያውን በ90 ቀናት ውስጥ እንዲሸጥ የሚያስገድድ  ማስፈፀሚያ ትዕዛዝ  በወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተላልፎበት ነበር። ያም ሆኖ ውሳኔው ህጋዊ ተግዳሮቶች ስለገጠሙት ሳይሳካ ቀርቷል። ከሰሞኑ ደግሞ የአሜሪካ ህግ አውጭዎች ባይትዳንስ በቲክ ቶክ ያለውን ድርሻ እንዲሸጥ ለማስገደድ አልያም ለማገድ  ረቂቅ ህግ አፅድቀዋል። ያለፈው ሳምንት ረቡዕ 352 ለ 65 በሆነ ድምጽ የፀደቀው ይህ ረቂቅ ህግ፤ ኩባንያው ቲክቶክን  በስድስት ወራት ውስጥ ካልሸጠ አሜሪካ ውስጥ ከአፕ ስቶር እና ከጎግል ስቶር ይታገዳል።ረቂቅ ህጉ፤ ህግ ሆኖ ስራ ላይ ለመዋል  የህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ /የሴኔቱ/ ይሁንታ ያስፈልገዋል።ያ ከሆነ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ህጉን በፊርማቸው እንደሚያጸድቁት ቃል ገብተዋል።

ቲክ ቶክን የሚያግደው ረቂቅ ህግ በህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ይሁንታ ካገኘ ፤የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ህጉን በፊርማቸው እንደሚያጸድቁት ቃል ገብተዋል
ቲክ ቶክን የሚያግደው ረቂቅ ህግ በህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ይሁንታ ካገኘ ፤የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ህጉን በፊርማቸው እንደሚያጸድቁት ቃል ገብተዋልምስል Andrew Harnik/AP/picture alliance

በዕገዳው ላይ የአሜሪካውያን አስተያየት 

ቲክ ቶክ በአሜሪካ ወደ 170 ሚሊዮን የሚጠጉ ተጠቃሚዎች ያሉት በጣም ተወዳጅ መተግበሪያ ሲሆን፤ የሶስተኛ ወገን መረጃ  እንደሚያሳየው የአሜሪካ የቲክ ቶክ ተጠቃሚዎች በአማካይ በቀን ከ60 እስከ 80 ደቂቃዎች መተግበሪያው ላይ ያሳልፋሉ።ይህም በቀን ከ30-40 ደቂቃዎች ከሚያሳልፉት ከተቀናቃኙ ኢንስታግራም ጋር ሲነፃፀር በዕጥፍ ብልጫ አለው።በቲክቶክ የሚሰራጩ ምክሮች ምን ያህል ጠቃሚ ናቸው?

ከዚህ አንፃር ውሳኔው በአሜሪካውያን የዲጂታል ይዘት አጠቃቀም ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር የሚችል በመሆኑ አብዛኛው አሜሪካዊ ተጠቃሚ በዕገዳው ላይ የራሱ አስተያየት አለው። የአንዲት የሀገሬው ሰው ቲክ ቶክን በተመለከተ እንዲህ ትላለች።
«ሁሉንም መረጃዎቼን  በቲክ ቶክ አገኛለሁ።የማላውቃቸውን እና ልጠቀምባቸው የምችላቸው ነገሮች፣ ለምሳሌ የጉዞ ቦታዎች፣ የመመገቢያ ቦታዎች፣ ሌሎች ነገሮችንም አገኛለሁ።»

ሁለተኛዋ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ጉዳዩን ከሙያዋ አንፃር ታየዋለች።«ሙዚቀኛ እንደ መሆኔ መጠን በእኔ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። ምክንያቱም ያ ሙዚቃዬን በመለጠፍ እና በማጋራት የምደሰትበት ቦታ ነው። እና ያ ማህበራዊ ስሜት ይሰጠኛል።ስለዚህ መታገዱ ማግኘት ወደ ምፈልጋቸው ሰዎች ለመሄድ ተፅዕኖ ይኖረዋል»ሌላኛዋ አሜሪካዊት በበኩሏ የቲክ ቶክ ተጠቃሚ ባትሆንም ከመብት አንፃር ትክክል አይደለም ትላለች። 
«ቲክ ቶክን አልጠቀምም። እውነት ለመናገር በእኔ ላይ ተፅዕኖ አያሳድርም። ፣ ምክንያቱም በጣም ሱስ የሚያስይዝ ነገር ሆኖ አግኝቼዋለሁ።እና በሱስ ቶሎ የሚጠቃ ስብዕና እና  ባህሪ  ስላለኝ አልጠቀምም። ነገር ግን ስለ መናገር ነፃነት አጥብቄ እቆጫለሁ። ስለዚህ እዚህ ያለመፈቀዱን ሀሳብ አልወደድኩትም።»

የአሜሪካ የቲክ ቶክ ተጠቃሚዎች በአማካይ በቀን ከ60 እስከ 80 ደቂቃዎች መተግበሪያው ላይ ያሳልፋ
የአሜሪካ የቲክ ቶክ ተጠቃሚዎች በአማካይ በቀን ከ60 እስከ 80 ደቂቃዎች መተግበሪያው ላይ ያሳልፋምስል picture alliance / PHOTOPQR/VOIX DU NORD/MAXPPP

አሜሪካ ለምን ቲክ ቶክን ማገድ ፈለገች?
የአሜሪካ የመረጃ ደህንነት ባለስልጣናት፤ ቲክ ቶክ የቻይና መንግስት መሳሪያ ሆኗል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።መተግበሪያው የአሜሪካን ዲሞክራሲ አደጋ ላይ ይጥላል የሚል ስጋትም አላቸው።የብሔራዊ መረጃ ዳይሬክተር ቢሮ ሰሞኑን እንዳስጠነቀቀው የቻይና ረዥም የፕሮፓጋንዳ ዕጅ በ2022 ከተካሄደው የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በፊት የዴሞክራት እና ሪፐብሊካን እጩዎችን ኢላማ አድርጓል።ከዚህ አንፃር መተግበሪያው በመጭው ህዳር ወር የሚካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመቀልበስ ሊውል ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።የአሜሪካ የደህንነት ባለስልጣናት ስጋት ከምንም የሚነሳ አይለም።ምክንያቱም በቻይና ብሄራዊ ደህንነት ህግ መሰረት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የቲክ ቶክ ባለቤት ባይትዳንስ በማንኛውም ጊዜ የአሜሪካን ተጠቃሚዎች መረጃ እንዲያቀርብ መንግስት የማስገደድ ስልጣን አለው እና።ቲክ ቶክ በባለሥልጣናት ዘንድ ለምን ስጋት አሳደረ?

ያም ሆኖ የቲክ ቶክ ሃላፊዎች የአሜሪካን የተጠቃሚዎች መረጃ ለቻይና ባለስልጣናት አጋርተን አናውቅም  ለወደፊቱ አሳልፈን አንሰጥም ሲሉ፤ የተጠቃሚዎችን መረጃ የመጠበቅ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ደጋግመው ተናግረዋል። የአሜሪካ ህግም  አንድ መተግበሪያ ለዩናይትድ ስቴትስ እንደ ባላንጣ በሚቆጠር ሀገር ቁጥጥር ስር ከሆነ፤ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ብሎ የመወሰን ስልጣን ለሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ይሰጣል።

ዕቅዱ ሰፊ ድጋፍ አለውን?
ረቂቅ ህጉ በተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ማለፉ፤ እጅግ በጣም በፖለቲካ በተከፋፈለው የዋሽንግተን ምክር ቤት ውስጥ ያልተለመደ የሁለትዮሽ ትብብር ነው። እናም የቲክ ቶክ እገዳ የሁለትዮሽ ድጋፍ ካገኙ በጣም ጥቂት ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሆኗል። ነገር ግን ረቂቅ ህጉ በህግ መወሰኛ ምክር ቤቱ /ሴኔቱ/ ለማለፍ ያለው ዕድል ብዙ አይመስልም።ምክንያቱም አንዳንድ የሕግ አውጭዎች በምርጫ ወቅት እንደዚህ ዓይነቱን ተወዳጅ መተግበሪያ ማገድ አይፈልጉም የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ አለ።

የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን እንደተናገሩትም የረቂቅ ህጉ ግብ ቲክቶክን ማገድ ሳይሆን ከቻይና ባለቤትነት ማውጣት ነው።- «ቲክ ቶክ እንደ ዲጅታል መድረክ፣ በአሜሪካ ኩባንያ በባለቤትነት  ወይስ በቻይና እንዲያዝ እንፈልጋለን? በቲክ ቶክ - የልጆች መረጃ ፣ የአዋቂዎች ውሂብ -እዚህ አሜሪካ ውስጥ እንዲቆይ ወይስ ወደ ቻይና እንዲሄድ እንፈልጋለን? » ሲሉ ጠይቀዋል።ለመሆኑ የቲክ ቶክ ስለተቀመር ወይም /Algorithm/ኢንስታግራም እና ከፌስቡክ ከመሳሰሉ የተለዬ ነውን?።መረጃን አሳልፎ በመስጠት ረገድስ የስጋት ደረጃው ምንያህል ነው? የሶፍትዌር መሀንዲሱ  አቶ ይግረማቸው እሸቴ  ማብራሪያ አላቸው። «የአሜሪካ ኮንግረንስ አባላት ስጋት ቲክ ቶክ ከጀርባ የዜጎችን መረጃ ይሰበስባል ነው።ይህንን ካየን እንግዲህ የቲክ ቶክ አልጎሪዝምን እስካሁን ባለው በብዙ ባለሙያዎች በታየው መሰረት ቲክ ቶክ እስካሁን አንድም መረጃ እና ማስረጃ አልተገኘበትም።»በማለት ገልፀዋል። ነገር ግን ቲክቶክ እንደማንኛውም የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የራሱ ችግሮች እንዳሉት አስረድተዋል።

የአሜሪካ የሲቪል ነጻነቶች ህብረት (ACLU) በወጣው መግለጫ እገዳው «መተግበሪያውን በየቀኑ ለመግባባት እና ሀሳባቸውን ለመግለጽ የሚጠቀሙትን በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን  የመጀመሪያ ደረጃ መብት ይጥሳል» ሲል አስጠንቅቋል።
በህብረቱ  ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ የሆኑት ጄና ሌቬንቶፍ «መሪዎቻችን የመጀመሪያ ደረጃ መብቶቻችንን ለዘንድሮ ምርጫ በርካሽ የፖለቲካ ነጥብ ለመቀየር  መሞከራቸው በጣም አዝነናል» ብለዋል።

የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን እንደተናገሩትም የረቂቅ ህጉ ግብ ቲክቶክን ማገድ ሳይሆን ከቻይና ባለቤትነት ማውጣት ነው
የዋይት ሀውስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን እንደተናገሩትም የረቂቅ ህጉ ግብ ቲክቶክን ማገድ ሳይሆን ከቻይና ባለቤትነት ማውጣት ነውምስል The Canadian Press/AP/dpa/picture alliance

ለሲቪል ነፃነት፣ ለዲጂታል መብቶች እና ለፀረ-ሳንሱር  የሚታገሉ በርካታ ድርጅቶች፡-በቅርቡ ለምክር ቤቱ  በፃፉት ደብዳቤ እንደገለፁት። የቲክ ቶክ እገዳ ህግ በምክር ቤቱ ከፀደቀ፤ በመላው ሀገሪቱ በዲጂታል መብት እና ሀሳብን በነጻ የመግለፅ መብትን የመሳሰሉ  ፣የአሜሪካውያንን የመጀመሪያ ደረጃ መብቶችን የሚጥስ እና በበይነመረብ ተጠቃሚዎች ላይ ሳንሱርን የሚጨምር  ጠንካራ እና አሳሳቢ ቅድመ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል። የዲሞክራሲ እና የቴክኖሎጂ ማዕከል አቤቱታቸውን በደብዳቤው ለምክር ቤቱ ካሰሙ ድርጅቶች አንዱ ነው።የድርጅቱ ባልደረባ ኬት ራውኒ ስጋታቸውን ይገልፃሉ።«እነዚያ 150 ሚሊዮን ሰዎችን ከዚህ በፊት ሲሳተፉ የቆዩበት ዓለም አቀፍ ውይይት ተደራሽ እንዳይሆን ያግዳል። እና ይህ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ መረጃ የማግኘት መብታቸውን ጭምር ይጎዳል።»በቲክቶክ ገንዘብ የሚያገኙ በርካታ አሜሪካውያንም የአዋጁን መጽደቅ ተቃውመው አደባባይ ወጥተዋል።ቲክ ቶክ ቀነገደብ በዩናይትድ ስቴትስ 

የቲክ ቶክ ተጠቃሚዎች የአከባቢ ተወካዮቻቸውን እንዲያነጋግሩ የሚያበረታታ መልዕክት  በመተግበሪያው ደርሰዋቸዋል። ይህም ከፍተኛ ቅሬታ እንዲፈጠር አድርጓል።ይህ ረቂቅ ህግ  የውጭ ድረ-ገጾችን እና መተግበሪያዎችን እንዲዘጉ የሚያደርግ በመሆኑ፤ የቴክኖሎጂ ተንታኞች «ትሮጃን ፈረስ» የሚል ስያሜ እሰጡት ይገኛል።ሌሎች ደግሞ እርምጃው የቲክ ቶክ ተጠቃሚ የሆኑ ወጣት አሜሪካውያን መራጮችን የማጣት አደጋ እንዳለው ያምናሉ።ከዚህ አንፃር ውጤቱ የበለጠ የተወሳሰበ በመሆኑ በዋይትሃውስ ቆይታቸው ቲክቶክን ለማዘጋት ጥረት ያደረጉት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፤ አዋጁን  በመቃወም አቋማቸውን ከወዲሁ ቀይረዋል። ትራምፕ ቲክ ቶክ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት እንደሚፈጥር  ቢገነዘቡም፤ እገዳው ለ2020 የምርጫ ሽንፈታቸው በከፊል ተጠያቂ የሚያደርጉትን ባላንጣቸውን ፌስቡክን እንደሚጠቅም አስጠንቅቀዋል።

ባይትዳንስ፣እና ቻይና ለእገዳው ምን ምላሽ ሰጡ?
ብሉምበርግ ኒውስ ያለፈው ሳምንት ባወጣው ዘገባ ፤ ባይት ዳንስ ቀነ ገደቡ ደርሶ መተግበሪያውን ለመሸጥ ከማሰቡ በፊት ሁሉንም የህግ አማራጮች ይጠቀማል። የዜና ምንጩ ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎችን ጠቅሶ እንደገዘገበው ቲክቶክን ለሌላ የአሜሪካ ኩባንያ ማዛወር ለቻይናው ኩባንያ የመጨረሻ አማራጭ ተደርጎ ይወሰዳል።
የቲክ ቶክ የህዝብ ፖሊሲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሚካኤል ቤከርማን ህጉን ለሚደግፉ በፃፉት በደብዳቤ «ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት ፣የሕዝብ ይሁንታ  ሳያገኝ የወጣው ይህ ረቂቅ ሕግ ፣ከባድ የሕገ-መንግሥታዊ ጥሰትን ያስከትላል» ብለዋል ።
መተግበሪያው በአሜሪካ ቢታገድ ሶስት ሚሊዮን አሜሪካዊያን ስራ አጥ ይሆናሉ ሲሉም የቲክ ቶክ ሀላፊዎች አስጠንቅዋል። የቻይና መንግስት በበኩሉ ተጨማሪ ዝርዝር መግለጫ ሳይሰጥ እገዳው «አሜሪካን መልሶ መጉዳቱ የማይቀር ነው»ሲል አስጠንቅቋል።

መተግበሪያው በአሜሪካ ቢታገድ ሶስት ሚሊዮን አሜሪካዊያን ስራ አጥ ይሆናሉ ሲሉም የቲክ ቶክ ሀላፊዎች አስጠንቅዋል
መተግበሪያው በአሜሪካ ቢታገድ ሶስት ሚሊዮን አሜሪካዊያን ስራ አጥ ይሆናሉ ሲሉም የቲክ ቶክ ሀላፊዎች አስጠንቅዋልምስል Jim Watson/AFP

ምንም እንኳን አሜሪካም ቲክቶክ መረጃዋን ለቻይና አሳልፎ ስለመስጠቱ እና ቲክ ቶክ የአሜሪካን የብሄራዊ ደህንነት ስጋ ስለመሆኑ፤ማስረጃ አቅርባ ባታውቅም ቲክ ቶክን ማፈን አላቆመችም ሲሉ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን  ተናግረዋል።
«እንዲህ አይነት በፍትሃዊ ውድድር ማሸነፍ የማይቻልበት የጉልበተኝነት ባህሪ የኩባንያዎችን መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያውክ፣ ዓለም አቀፍ ባለሃብቶችን በመዋዕለንዋይ ፍሰት ላይ ያላቸውን እምነት እና፤ መደበኛውን የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና የንግድ ስርዓት ይጎዳል» ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ሀላፊ ስቴቨን ሙንሽን ቲክቶክን ለመግዛት እንዳቀዱ በዚህ ሳምንት የወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል። እሳቸው ይህን ይበሉ እንጅ ባይትዳንስ ቲክቶክን ስለመሸጡም ሆነ ስለቀጣይ እቅዱ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
በዓለም ዙሪያ 1 ቢሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት፤ቲክ ቶክ ከዚህ ቀደም በሶማሊያ፣ በኢራን፣ በኔፓል እና  በአፍጋኒስታን የታገደ ሲሆን አንዳንድ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን እና አንዳንድ  የአውሮፓ ሀገራትም ለስራ በሚጠቀሙበት የመንግስት ዲጅታል መሳሪያዎች ላይ ቲክቶክን መጫን ከልክለዋል።

ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ