1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ቴክኒክአፍሪቃ

በቲክቶክ የሚሰራጩ ምክሮች ምን ያህል ጠቃሚ ናቸው?

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ግንቦት 11 2015

ሌሎችም እንዲሞክሯቸው በሚል ብዙ ጠቃሚ የሚባሉ የቲክቶክ ምክሮች በመተገብሪያው ላይ በየዕለቱ ይሰራጫሉ። የውበት አያያዝ ፣ የምግብ አበሳሰል ወይም የቤት ማስዋቢያዎች ከነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው። ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከዚህ ምን ያህል ተጠቃሚ እየሆኑ ነው? ጠቃሚ እና ጎጂን መልዕክት እንዴት ይለያሉ?

https://p.dw.com/p/4RZLq
ምስል Michael Dwyer/AP Photo/picture alliance

በቲክቶክ የሚሰራጩ ምክሮች ምን ያህል ጠቃሚ ናቸው?

ቲክቶክ አጫጭር ቪዲዮዎች የሚሰራጩበት ከአለም ቀዳሚ የሚባል የማህበራዊ መገናኛ መድረክ ነው።  መተግበሪያ ላይ የተወሰኑ መፈለጊያ ቃላት በመስጠት በርካታ አጠር መጠን ባለ መረጃ የተቀናበሩ ቪዲዮዎችን ማግኘት ይቻላል።  «የእኛ ተልእኮ ለፈጠራ ማነቃቃት እና ደስታን መፍጠር ነው» ይላል ቲክቶክ ስለ አላማው ሲገልፅ።
የ 19 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት ቅድስት እንደገለፀችልን ከሜካፕ አቀባብ ስልቶች ፣ የቆዳ አያያዝ እና አለባበስ ብዙውን ጊዜ ቲክቶክ ላይ የምታያቸው ቪዲዮች ናቸው፤ « ምክንያቱም ራሳችንን በደንብ መንከከብ አለብን ብዬ አስባለሁ» ትላለች በወላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ቅድስት።   ወጣቷ ሌላም  ቲክቶክ ላይ ማየት ብቻ ሳይሆን መሞከር የምታዘወትረው ነገር አለ። «  በምግብ ዙሪያ የሚለቀቁ ቪዲዮችን ሳይ ብሰራቸው ፣ ብቀምሳቸው በሚል ይበልጥ ለመሞከር ያበረታቱኛል።»
ወጣት ፋሲካ አዝናኝ እና እግር ኳስን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ቲክቶክ ላይ ይመለከታል።  ዋንኛ እና ጠቃሚ የሚለው ደግሞ ከስራው ጋር የሚገናኝ እና ቴክኒክ ነክ ጉዳይ ሲሆን ነው። « የሳተላይት ዲሽ ቴክኒሽያን ነኝ። ስለዚህ ለዚያ ሙያ አዲስ ነገር ቪዲዮዎች ሲለቀቁ እከታተላለሁ። ይላል። ይሁንና የሚመለከታቸውን ጠቃሚ ነገሮች ለመስራት ግብዓቶቹን ለመግዛት አቅም ስለሚያንሰው እና በጊዜ  ፋሲካ የሚሞክራቸው ነገሮች ከስራው ጋር የተገናኙ ከሆነ ብቻ እንደሆነም ገልፆልናል። 
የ 20 ዓመቷ ልደታ  መንፈሳዊ የሆኑ እና በሀይማኖት ዙሪያ ያሉ ቪዲዮዎችን ቲክቶች ላይ ማየት እወዳለሁ ትላለች።  እንደ እሷ እየታም ለወጣቱ አስፈላጊ ናቸው። « ሌላ ነገር አይቼ ከምወጣ ቶክቶክ በምጠቀምበት ሰዓት ስብከት ባዳምጥ ስለ ሀይማኖቴ አዲስ ነገር እያወኩ ነው። » ስትል ታብራራለች።
ቲክቶክ ላይ ያሉት ይዘቶች ለተጠቃሚዎች ብዙ አዳዲስ እና ማነቃቂያ የሚሰጡ እንደመሆናቸው እና  ተጠቃሚው  መመልከት የሚያዘወትሯቸውን ርዕሶች ቲክቶክ እየለየ አከታትሎ በማቅረቡ የተነሳ ብዙ ወጣቶች ጊዜያቸውን ቲክቶክ ላይ ያጠፋሉ። ቲክቶክ ሱስ የሆነባቸው በርካታ ተጠቃሚዎችም አሉ። የኢንተርኔት አገልግሎት እንደሌሎች ሀገራት ፈጣን እና ርካሽ ቢሆን ኖሮ ፋሲካ ብዙ ጊዜውን ቲክቶክ ላይ  ያጠፋ እንደነበር ጥርጥር የለውም።  « አብዛኛው ወጣትም እንደዛ ነው። አያለሁ ሱስ ይሆናል።»
ቲክቶክ ላይ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር አበሳሰል አይነቶችን ኢትዮጵያውያን እያብራሩ እና እያበሰሉ ያሳያሉ። ሙያቸውን በቲክቶክ ለማሳየት ከሚያበስሏቸው ግብዓቶች በስተቀር የግድ ዝነኛ መሆን አይጠይቅም። «ብዙውን ጊዜ ቲክቶክ ላይ የማያቸውን ምግቦች መስራት እወዳለሁ» የምትለው ቅድስት  በተለይ የውጭ ሀገራት ምግቦችን ማብሰል እንደለመደች ትናገራለች። « የአበሻ ምግቦች ብዙውን ጊዜ ሲሰራ ስለማይ እና ስለማውቅ የውጭ ምግቦችን ነው ለመስራት የምሞክረው።» እሷም የራሷን ቪዲዮ እየሰራች በቲክቶች ትለቃለች።

Bildkombo Tik Tok Trend #BookTok

በቡራዩ ነዋሪ የሆነው ቀነኒሳም የራሱን ስራዎች ቲክቶክ ላይ ይለጥፋል። ቀነኒሳ አምቦ የሚል የቲክቶክ ገፅ አለው። « የኦሮምኛ የተለያየ ውዝዋዜ እሰራለሁ። አዲስ ዘፈኖች ሲለቀቁ እነሱን እሰራለሁ።»ቀነኒሳ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ቲክቶክ ላይ የሚያገኟቸውን ጠቃሚ ሀሳቦች ተመልክቶ ከማለፍ በቀር መተግበሩ በገንዘብ እና ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት እንደሚከብዳቸው ገልፀውልናል።
የቲክቶክ ጥናት እንደሚያመላክተው እድሜያቸው ከ 16 እስከ 24 ባሉ ወጣቶች ዘንድ መተግበሪያው ተመራጭነት አለው። አንዳንድ ፖለቲከኞች እንደውም እነዚህን ወጣቶች ለማግኘት የፖለቲካ አጀንዳቸውን በቲክቶክ ማሰራጨት እንደ አማራጭ እየተጠቀሙበት ነው። ትላልቅ የመገናኛ ብዙኃንም መረጃቸውን በዚሁ መተግበሪያ ማሰራጨት ጀምረዋል።  በደቡብ አፍሪቃ ነዋሪ የሆነው ተሾመ ፖለቲካዊ እና ስፖርት ነክ ዜናዎች ቲክቶክ ላይ የሚያዘወትራቸው እና ጠቃሚ የሚላቸው መረጃዎች ናቸው። « ዜና የሚያሰራጩ ቻናሎችን እከታተላለሁ። አንዳንድ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚሰሩ አፍሪቃውያን ኮሜዲያንንም እከታተላለሁ። »
መስፍን የአዲስ አበባ ነዋሪ ነው። እሱ ደግሞ ከህክምና ጋር የሚገናኙ መረጃዎችን ቲክቶክ ላይ ይፈልጋል፣ ያገኛልም። « ባለቤቴ እርጉዝ ናት እና አንድ ባለሙያ አለች እሷ በምታገኘው ገለፃ ብዙ ተምረናል።»
በተለይ ከጤና ጋር የሚያያዝ እና ቲክቶክ ላይ የሚሰራጭን የምክር ሀሳብ መጠንቀቅ ብሎ መፈተሽ ያስፈልጋል። ቪዲዮ የሚለጥፉት በሙሉ የጤና ባለሙያ አይደሉም። ቲክቶክ ላይ የሚጠቅሙ ብቻ ሳይሆን ሀሰተኛ ምርቶችን የሚያስተዋውቁ  ሰዎችም አልጠፉም። በቲኪቶክ ላይ በተሰራጩ የውበት ምክሮች ሆስፒታል ድረስ የገቡ  ተጠቃሚዎችም አሉ። ቅድስት ጥሩውን እና መጥፎውን መረጃ የምትለይበትን መንገድ ጠይቀናታል። « ማን ነው ቪዲዮውን የሰራው? ከቪዲዮው ስር ሰዎች ሞክረው የሰጡት አስተያየት ምን ይላል እያልኩ አጣራለሁ።» 

ልደት አበበ

Facebook, Twitter, Instagram, TikTok
ምስል Hideki Yoshihara/AFLO/IMAGO

ኂሩት መለሰ