1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ"ቱምሳ ላሚ" በጎ አድራጎት ድጋፍ

ነጋሳ ደሳለኝ
ቅዳሜ፣ ጥር 17 2017

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ያቋቋሙት የ"ቱምሳ ላሚ" በጎ አድራጎት ድርጅት በምስራቅ፣ምዕራብ እና ሆሮ ጉደሩ ወለጋ ዞን ውስጥ ከዚህ ቀደም በነበሩት ግጭት ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ነዋሪዎች ከ200 በላይ መኖሪያ ቤቶችን መገንባቱን ገለጸ፡፡

https://p.dw.com/p/4pcFa
ምስራቅ ወለጋ ነቀምት ከተማ
ምስራቅ ወለጋ ነቀምት ከተማምስል Negassa Desalegn/DW

የ"ቱምሳ ላሚ" በጎ አድራጎት ድጋፍ

በጎ አድራጎት ድርጀቱ ከዩኒቨርሲቲ ሠራተኞችና ማህበራዊ መገናኛ ዜዴን በመጠቀም በሚሊዩን የሚቆጠር ብር በመሰብሰብ ብዙ ህዝብ በተፈናቀላባቸው እንደ ኪረሙ፣ጊዳ፣አሙሩ፣ጃርዳጋ ጃርቴ እና ምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች የእህልና ልብስ ድጋፍ ማድረጉን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ስርዓተ ጾታ ኃላፊ እና የቱምሳ ላሚ አስተባባሪ ዶ/ር ሀሊማ ጅብሪል ጠቁመዋል፡፡


በቱምሳ ላሚ በኩል ከ200 በላይ ቤቶች ለተፈናቃዮች ተሰርቷል

ከሁለት ዓመት በፊት በወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በተከሰቱት ግጭቶች  ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማገዝ በማለም በወለጋ ዩኒቨርሲቲ አምስት መምህራን የተጀመረው ቱምሳ ላሚ የተባለው በጎ አድራጎት በወለጋ 3 ዞኖች ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎችን መደገፉን አመልክተዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እና ተቋማት እንዲሁም በበላይነት ደግሞ ማህበራዊ መገናኛ ዜዴ በመጠቀም ባጠቃላይ  23 ሚሊዮን ብር  ገንዘብ በማሰብሳብ በሆሮ ጉደሩ ወለጋ፣ በምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ውስጥ ከሁለት መቶ በላይ ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ነዋሪዎች መኖሪያ ቤት መስራታቸውን በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የስርዓተ ጾታ ጽ/ቤት ኃላፊና የቱምሳ ላሚ አስተባበሪ  የሆኑት  ዶ/ር ሀሊማ ጅብሪል ገልጸዋል፡፡ 


በተለይም ሰዎች በብዛት የተፈናቀሉበት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ እንደ ጃርዳጋ ጃርቴ፣አሙሩ እና ከምስራቅ ወለጋ ደግሞ ኪረሙ እና ጊዳ አያና ያሉ ወረዳዎች ድጋፍ ከተደረገላቸው አካባቢዎች መካከል ናቸው፡፡ ቱምሳ ላሚ በጎ አድራጎት በ2016 ዓ.ም 200 ኩንታል እህል ለሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አሙሩ ወረዳ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ ለሚገኙ የተፈናቀሉ ሰዎች ልብስና የእህል ድጋፍ መደረጉን ዶ/ር ሀሊማ ጠቁመዋል፡፡

የቱምሳ ላሚ በጎ አድራጎት


በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርዳጋ ጃርቴ ወረዳ 130 ሰዎች ድጋፍ አግኝቷል

በቱምሳ ላሚ በጉ አድራጎት ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርዳጋ ጃርቴ ወረዳ አንዱ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከዚህ ወረዳ ተፈናቅለው  በዞኑ ዋና መቀመጫ በሆነው ሻምቡ ከተማ ተጠልለው ቆይተዋል፡፡ የጃርዳጋ ጃርቴ ቡሳ ጎኖፋ ጽ/ቤት/የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ነሞምሳ በቱምሳ ለሚ ከዚህ ቀደም 100 ኩንታል በቆሎ ድጋፍ መደረጉንና ቤታቸው ለወደመባቸው ሰዎች ቤት መሰራቱን አመልክተዋል፡፡
" መኖሪያ ቤቶች ተሰርተዋል፡፡ ከተማ ላይ ነው የሰሩት፡፡ ቱምሳ ላሚ ቆርቆሮና ሚስማር ለ130 ሰዎችም ድጋፍ አድረጓዋል፡፡ ለእያንዳንዳቸው 30 ቆርቆሮና 3000 ብር ገንዘብ ሰጥተዋል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችም ከሻምቡ ተመልሰዋል፡፡ "


በኪረሙ ወረዳ የተወሰኑ ሰዎች ድጋፍ ማገኘታቸውን ተናግረዋል 

በ2014 እና በ2015 ዓ.ም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የተፈናቀሉባት ኪረሙ ወረዳም በወረዳው ስር የሚገኙ 10 ቀበሌዎች ውስጥ አብዛኛው ቤቶች መጎዳታቸውን ከዚህ ቀደም የወረዳው አደጋ ስጋት ስራ አመራር ወይም ቡሳ ጎኖፋ ጽ/ቤት ገልጸዋል፡፡ ከአካባቢው ያነጋርናቸው አንድ ነዋሪ በወረዳው ቤታቸው ሙሉ በሙሉ ለወደመባቸው ነዋሪዎች ለተወሰኑ ሰዎች ቤት መሰራቱን እና ለሌሎች ደግሞ 12 ፍሬ ቆርቆሮ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡


"የኪረሙ ወረዳ በግጭት በተጎዳበት ወቅት ከቡሳ ጎኖፍ ቀጥሎ አብዛኛው ሰዎች ጋር መድረሰ ባይቻልም ልብስና በቆሎ ጨምሮ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ድጋፍ ሲሰጥ ነበር፡፡ ምንያህል ድጋፍ እንደመጣ ባናውቅም ለመኖሪያ ቤት ማሰሪያ ቆርቆሮ ለአንድ አባ ዎራ እስከ 12 ፍሬ ሲሰጥ ነበር፡፡ ህዝቡ ተፈናቅለው ጊዳ አያና ላይ በነበረበትም ወቅት ድጋፍ ሲያደርጉ ነበር ተደራሽነቱ ለሁሉም የተፈናቀሉ ሰዎች ጋር ባሆንም ከመንግስት ተቋት ከቡሳ ጎኖፍ ቀጥሎ ለኪረሙ ድጋፍ ያረገው ከወለጋ ዩነቨርሰቲ ብቻ ነው፡፡"


የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ያቋቋሙት ቱምሳ ላሚ በጎ አድራጎት ድርጅትም የተፈናቀሉት ዜጎችን ለማገዝ ስራ የጀመረው ከ2 ዓመት በፊት ነበር፡፡ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋና ምስራቅ ወለጋ  የተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው በየከተማ ዙሪያ ተጠልለው የነበሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቸ ወደየ ቤታቸው መመለሳቸውን ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል፡፡ 


ነጋሳ ደሳለኝ
ልደት አበበ