1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሕወሃት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ውሳኔ ተቃወመ

ረቡዕ፣ ግንቦት 9 2015

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓት ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ የሰላም ሂደቱ የሚጓዳ ሲል የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ተቃወመ። ህወሓት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ ደግሞ እንዲያጤን ጠይቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለግዜው ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችል ገልጿል።

https://p.dw.com/p/4RVgj
Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)

ሕወሃት በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ላይ ያወጣው መግለጫ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓት ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ የሰላም ሂደቱ የሚጓዳ ሲል የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ተቃወመ። ህወሓት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያስተላለፈው ውሳኔ ደግሞ እንዲያጤን ጠይቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለግዜው ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችል ገልጿል። 

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፥ ህወሓት ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ያቀረበው አቤቱታ እንደማይቀበል ያስተላለፈው ውሳኔ፣ ከህወሓት ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ተቃውሞ እየገጠመው ነው። በዚሁ ጉዳይ ዙርያ ትላንት ማታ ይፋዊ መግለጫ ያወጣው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ህወሓት፣ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡ በማንሳት፣ ቦርዱ ግን 'ሕጋዊ ሰውነት የመሰረዝ ውሳኔ እንዲያነሳ ያቀረብንለት ጥያቄ የሰላም ስምምነቱ አላማ የሆኑ ሐሳቦች በሚፃረር ሁኔታ ምላሽ ሰጥቷል' በማለት ወቅሷል። ህወሓት የቦርዱ ውሳኔ የሰላም ስምምነቱ የማይቀበል፣ የሰላም ስምምነቱ አተገባበር ባለቤት አልባ የሚያደርግ፣ በቀጣይም ለሰላሙ እንቅፋት የሚፈጥር ሲል ተችቶታል። ህወሓት በመግለጫው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የማያበረታታ እና ለሌሎችም ተስፋ የማይሰጥ ነው ያለው ሲሆን፥ ቦርዱ ውሳኔውን ዳግም ያጤናል ብሎ እንደሚጠበቅ ገልጿል። በዚሁ ጉዳይ ዙርያ ያነጋገርናቸው የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባልና በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም፣ ከሰላም ስምምነቱ በኃላ ህወሓት ከአሸባሪነት ዝርዝር ተነስቷል፣ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር እየሰራ ነው፣ በስምምነቱ ደግሞ በአካታቹ ግዚያዊ አስተዳደር ሚናው እየተወጣ መሆኑ በማንሳት፥ በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት አካል የሆነው ምርጫ ቦርድ ፖርቲው ወደ ቀድሞ ሁኔታው ሊመልሰው እንደሚገባ ይሞግታሉ። 

Logo Äthiopiens Nationale Wahlbehörde
ምስል Ethiopian National Election Board

ከህወሓት ውጭ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደርም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት አልመልስም ያለበት ውሳኔ እንዲቀይር የሚጠይቅ መግለጫ አሰራጭቷል። ቦርዱ ህወሓት ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ በሕግም በፖለቲካም ተቀባይነት የለውም ያለው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር፥ ስምምነቱ ተከትሎ ህወሓት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ መምጣቱ በማንሳት የቦርዱ ውሳኔ ግን ለግዚያዊ አስተዳደሩ ጭምር እውቅና የሚነፍግ እና ባለቤት አልባ የሚያደርግ ብሎታል። ከዚህ በተጨማሪ ለዶቼቬለ ሀሳባቸው ያጋሩት የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ሐላፊ አቶ ረዳኢ ሐላፎም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ የሰላም ሂደቱ የሚያደናቅፍ ብለውታል። 

በዚሁ የህወሓት ቅሬታ ዙርያ ጥያቄ ያቀረብንል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በጉዳዮ ዙርያ በቦርዱ በኩል እስካሁን የተለየ ነገር አለመኖሩ፣ በቀጣይ የሚታይ ነገር ካለደግሞ በአሰራሩ መሰረት ይፋ እንደሚደረግ ያስታወቀ ሲሆን ለግዜው ግን ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት እንደማይችል ገልጿል። 

ከዚህ ውጭ ዶቼቬሌ ያነጋገራቸው የሕግ ሙሁሩ አቶ ሙስጠፋ ዓብዱ፥ ቦርዱ ሕጋዊ ሰውነት ዳግም ለመመለስ የሚያስችለኝ የሕግ አግባብ የለም ብሎ ያስተላለፈው ውሳኔ ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ ህወሓትን ለመሰረዝ የሄደበት ሂደት ጭምር የሕግ ክፍተት የነበረበት፣ የተጠቀሰው አዋጅ ያላከበረ እና ሂደቱ ያልጠበቀ ነበር በማለት ተችተውታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከህወሓት ውጭ የምዝገባ ሂደታቸው እንዲቀጥል በጠየቁ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ እና ባይቶና ፖርቲዎች ላይም ዳግም ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርጉ የሚጠይቅ ውሳኔ መስጠቱ ይታወሳል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ