1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወንጀል መባባስ በኢትዮጵያ ፥ የግድያ ሙከራ በትራምፕ

ዓርብ፣ ሐምሌ 12 2016

በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞችና ገጠሮች የወንጀል ድርጊቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው አሳሳቢ ሆኗል ። ዶናልድ ትራምፕ ላይ ባለፈው ቅዳሜ የ20 ዓመቱ ወጣት እንዴት በቅርብ ርቀት የመግደል ሙከራ ሊያደርግ ቻለ? የበርካቶች ጥያቄ ነው ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ ልየታ ጉዳይም አነጋግሯል ። አስተያየቶችን አሰባስበናል ።

https://p.dw.com/p/4iU62
USA Butler Wahlkampf Trump Zwischenfall
ምስል Evan Vucci/AP Photos/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የተሰጡ ዐበይት አስተያየቶች

እገታ፤ ግድያ፤ ስወራ፤ አስገድዶ መድፈር፤ ዘረፋ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች መንሰራፋቱ በርካቶችን ተስፋ ያስቆረጠ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል ። በኢትዮጵያ የወንጀል ድርጊት መባባስ ብዙዎችን በእርግጥ መንግሥት አለ ወይ አስብሏል ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በሦስት ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ ልየታ መርሀ- ግብር እንደሚያስጀምር መግለጡ ሆኖም በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ግን «ጥረት» እያደረገ መሆኑን ማሳወቁ የመወያያ ርእስ ሆኗል ። ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፦ በዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚደንት እና የሪፐብሊካን እጩ ተፎካካሪ ዶናልድ ትራምፕ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ አወያይቷል ። አስተያየቶችን አሰባስበናል ።

የወንጀል መባባስ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞችና ገጠሮች የወንጀል ድርጊቶች እየተበራከቱ መምጣታቸው አሳሳቢ ሆኗል ። በጠራራ ፀሐይ ግድያ፤ ነጠቃ እና ዝርፊያ በተደጋጋሚ መስማት የተለመደ ሆኗል ። ተማሪዎች ታግተው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ተጠየቀባቸው፤ ሴት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በደቦ ተደፈሩ፤ የሚሉ ዜናዎችም ተደጋግመው ይሰማሉ ።  የማኅበረሰብ አንቂዎች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የችግሩን አሳሳቢነት በመግለጥ በተደጋጋሚ ይወተውታሉ ። የወንጀል ድርጊቱ ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ እየተባባሰ መጥቷል ።

ቻሌ አያሌው የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፦ «ለዚህ ሁለም ነገር ገዢው ፓርቲ መጠየቅ አለበት» ብለዋል ። «መንግስት ደካማና አቅመ ቢስ ሆኗል» ያሉት ደግሞ ንቡረ እድ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ናቸው ። «የፀጥታ አካላትም ሙስና እና ብልሹ አሠራር ውስጥ ተዘፍቀዋል። በእነሡ ተባባሪነት የሚፈፀሙ አንዳንድ ወንጀሎችም አሉ» ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል ። «ኅብረተሠቡ ከቻለ መንግስት ላይ ጫና ማድረግ ነው ግብር እየከፈልክ ደህንነትህ ካልተረጋገጠ ችግር ነው» በማለትም አስተያየታቸውን አጠናቀዋል ።  «ወንጀል ፈጻሚው ራሱ ፀጥታ ኃይሉ አይደል» ሲሉ ያጠየቁት ደግሞ ዮሐንስ ጴጥሮስ አንቦ ናቸው በፌስቡክ ።

ትዮጵያ ውስጥ በተለይ ሴቶች ላይ የሚደርሱ በደሎች እንዲቆሙ የሚጠይቅ ሰልፍ በትግራይ ክልል
ፎቶ ከማኅደር፦ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ሴቶች ላይ የሚደርሱ በደሎች እንዲቆሙ የሚጠይቅ ሰልፍ በትግራይ ክልል ምስል Million Haileselassie/DW

የወንጀል ድርጊቱ መደጋገም  እና መባባስ ያሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በበኩሉ ትናንት መግለጫ አውጥቷል ። «መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ሕጋዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ሲልም አሳስቧል ።

«በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ እገታና አፍኖ የመሰወር ተግባር በሀገራችን በአሳሳቢ ደረጃ እየተስፋፋ ያለ ጉዳይ» ነው ያለው ኢሰመጉ ለመፍትኄው ግን የሚመለከታቸው አካላት ዳተኛ መሆናቸውን ጠቁሟል ።  በወንጀል ድርጊቱም «የተነሳ የሰዎች በሕይወት የመኖር መብት፣ የአካል ደህንነት መብት እና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ መሆኑን በመረጃ በማስደገፍ በተደጋጋሚ መግለጫዎችን ያወጣ» መሆኑንም ገልጧል።  ሆኖም «የሚመለከታቸው የፌደራል እና የክልል መንግስታት በግዛት ክልላቸው የሚፈጸመውን ግድያ፣ እገታ እና አስገድዶ መሰወር ለማስቆም በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ባለማድረጋቸው ይህ ድርጊት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋና እየተባባሰ ማኅበረሰቡን ለከፍተኛ ምሬት እና እንግልት እየዳረገው» እንደሚገኝ ገልጧል ። 

«በእኔ አሳብ መንግስት ከላይ እስከታች መዋቅሩን መፈተሽ አለበት ባይ ነኝ» ይላሉ ሐሚድ ሐሙ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ። ምክንያታቸውን ሲያሰፍሩም፦ «ከአጋቾቹ ጋር ተናበው እሚሠሩ የመንግሥት ደሞዝ እሚከፈላቸው አሉ በሁለት ማሊያ ከሚጫወተው ብዙዎቹ ናቸው » ብለዋል ። ዶይቸ ቬለ ሰኞ ረፋዱ ላይ በዚሁ ርእሰ ጉዳይ ላይ በፌስቡክ አወያይቶ ነበር ። እስከ ትናንት ሐሙስ ድረስ ከ180 በላይ ሰዎች አስተያየታቸውን በመስጠት በውይይቱ ተካፍለዋል።  አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች  መንግሥት እና የፀጥታ ኃይሉ ራሱን መፈተሽ እንዳለበት የሚጠቁሙ ናቸው ። ጎይትኦም ዘሚካኤል በተባሉ አስተያየት ሰጪ ይህን ርእሰ ጉዳይ እንቋጭ እና ወደ ሌሎቹ እንሻገር ። «ተው ተው የለውጡ አካል ነው፤ 27 ዓመት ሙሉ በጨለማ ተውጠን ነበር፤ አሁን ነው የበራልን»  አሉ ጎይትኦም በስላቃዊ ጽሑፋቸው ። «ፈጣሪ ጸሎታችን ሰምቶ የተመኘነውን ሰጠን» አከሉ ።  «ገና ይቀጥላል» ሲሉ ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)ምስል Ethiopian Human Rights Council

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ ልየታ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሦስት ክልሎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር የአጀንዳ ልየታ መርሀ- ግብር እንደሚያካሂድ ያሳወቀው ከትናንት በስትያ ነበር ። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ረቡዕ፤ ሐምሌ 10 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ከአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ፦ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚቀጥለው ሳምንት የአጀንዳ አሰባሰብ መርሀ-ግብር እንደሚካሄድ ተናግረዋል ። ኮሚሽነሩ የአጀንዳ ልየታው በቀሪዎቹ ክልሎች ከነሐሴ 30 በፊት እንደሚጠናቀቅ፣ ሆኖም በአፋር ክልል ወደ መስከረም ሊሻገር እንደሚችል ተናግረዋል ። በትግራይና በአማራ ክልል ደግሞ የተሳታፊዎች ልየታ ለማከናወን «ጥረት» እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል ። በዚህ መረጃ ላይ በዶይቸ ቬለ የፌስቡክ ገጽ በርካቶች አስተያየት ሰጥተዋል። 

«ትግራይ እና አማራ የሌለበት ምክክር ምኑ ምክክር ሆነ?»  ፌይር ፕሌይ በሚል ስም የፌስቡክ ተጠቃሚ አስተያየት ነው ።

ፎቶ ከማኅደር፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ተሳታፊዎች
ፎቶ ከማኅደር፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ስብሰባ ተሳታፊዎችምስል Solomon Muchie/DW

«በሐሣብ የበላይነት ለውጥ እንዲመጣ ብዙ ጊዜ ሕዝብ ጠይቆ ከመንግስት ተገቢ ምላሽ በማጣቱ መሣሪያ ካነሣ በኋላ ምክክር ብሎ መሣሪያን ለማስጣል መሞከር ሕዝብ መሣሪያ ያነሣበትን መሠረታዊ ሐሣብ እንደመናቅ ይቆጠራል» ያሉት ወርቅነህ ጎልድ የተባሉ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ ናቸው ።

«አይ መከራ አሁንም የአጀንዳ ልየታ፤ ሁልጊዜ የአጀንዳ ልየታ ስትሉ አታፍሩም እንዴ ያሉት ብርሃኑ አስናቀ ናቸው ፌስቡክ ላይ በሰጡት አስተያየት ። ፋኖስ ኢትዮጵያ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ፦ «እኛ የናፈቀን ሰላም ነው» ብለዋል ። «ጦርነት አቁሞ ሰላም ሲኖር ነው ምክክር የሚያምር፤ ምን ላይ ተሁኖ ነው ምክክር የሚደረግ» ሲሉም ይጠይቃሉ ። «እርስ በእርስ የአንድን አገር ዜጋ አፋጃችሁት» ሲሉም መልእክታቸውን አጠናቀዋል ።

በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ባለፈው ቅዳሜ የ20 ዓመቱ ወጣት እንዴት በቅርብ ርቀት የመግደል ሙከራ ሊያደርግ ቻለ?  የበርካቶች ጥያቄ ነው ። ቶማስ ማቲው ኩሩክስ የተባለው የ20 ዓመት ወጣት ተኳሽ ፔንሲልቫኒያ ከተማ ውስጥ ዶናልድ ትራምፕ ከነበሩበት መድረክ 135 ሜትር ርቀት ላይ  ሆኖ  ነበር ተኩስ የከፈተው ።  «እንዴት» በሚለው ጥያቄ ብቻም አላበቃም ። የዩናይትድ ስቴትስ የፕሬዚደንቶች እና የቀድሞ ፕሬዚደንቶች ጥበቃ ጓዶች የጥበቃ ሁኔታ እየተመረመረ ነው ። የዩናይትድ ስቴትስ የሀገር ውስጥ ደሕንነት ጽ/ቤት ዋና መርማሪ ምርመራው መከፈቱን ረቡዕ ዕለት ዐሳውቀዋል ።

የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ
የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕእጃቸውን ከፍ አድርገውምስል Brendan McDermid/REUTERS

«አፍሪቃ ውስጥ የተለመደ ቁማር በታላቋ አሜሪካም!?» ሲሉ ጠይቀዋል ነጻነት በዛብህ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ። «አይ ፖለቲካ አሜሪካም እንደዚህ?»  ያሉት ቅርብነህ መለሠ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፦ «እንደ ሸቀጥ ሱቅ ውስጥ ሽጉጥ እየሸጡ ምን ጠብቀው ነበር ብለዋል ። ናቲ ላቭ የተባሉ አስተያየት ሰጪ፦ «እንዴት ሊሆን ይችላል ሲሉ ግራ በመጋባት ጠይቀዋል።  «አሁንም ትራምፕ ኃይለ ቃል የተሞላበት ንግግራቸውን ካለቆሙ  ዕጣቸው እንደ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ነው የሚሆነው» ያሉት ደግሞ ወዲ ፍትዊ ናቸው ።

ከሩብ ሚሊዮን በላይ ተከታይ ያለው «አፍሪካን» የሚል ስም ያለው የትዊተር መልእክት ክስተቱን ከአፍሪቃ ፖለቲካ ጋ አነጻጽሮ ተሳልቋል። እንዲህ ሲል፦ «አሜሪካ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ነውጥ ደረጃ አሳስቦናል ።» በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተጽፎ በስፋት ሲዘዋወር የነበረው መልእክት፦ «አሜሪካውያን ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ እናሳስባለን» ሲልም ይነበባል ። ይቀጥላል በመሳለቅ፤ እንዲህ እያለ፦ «አሜሪካ ውስጥ ያሉ አፍሪቃውያን በአጠቃላይ ከየሃገሮቻቸው ኤምባሲዎች ጋ ግንኙነት ሊያደርጉ ይገባል ።» የስላቅ ጽሑፉ ሲጠናቀቅም እንዲህ ብሎ ነው ። «በዚህ ወቅት አፍሪቃውያን ወደ አሜሪካ ከሚያደርጉት ጉዞ እንዲታቀቡ እንመክራለን ።» የስላቅ ጽሑፉ በዚሁ ይጠናቀቃል ። እኛም በዚሁ አጠናቀቅን።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ