1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከኦሮሚያ የተፈናቀሉትን ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ጅማሮ

ረቡዕ፣ የካቲት 13 2016

በተደጋጋሚ ጥቃት እና አለመረጋጋት በተለያዩ ጊዜያት ከኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች ተፈናቅለው ደብረብርሃን ከቆዩ ተፈናቃዮች የተወሰኑትን ወደ ነባር ቀዬያቸው የመመለስ ሥራ መጀመሩ ተገለጸ ። ሁድ ማለዳ 14 አውቶብሶች ተፈናቃዮቹን ጭነው መውጣታቸውም ተገልጧል ።

https://p.dw.com/p/4chLT
የተፈናቃዮች መጠለያ
የተፈናቃዮች መጠለያ፤ አማራ ክልልምስል Zinabu Melese/DW

14 አውቶብሶች ተፈናቃዮቹን ጭነው መውጣታቸውም ተገልጧል

በተደጋጋሚ ጥቃት እና አለመረጋጋት በተለያዩ ጊዜያት ከኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች ተፈናቅለው ደብረብርሃን ከቆዩ ተፈናቃዮች የተወሰኑትን ወደ ነባር ቀዬያቸው የመመለስ ሥራ መጀመሩ ተገለጸ ። ከአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት የተውጣጡ ባለስልጣናት ቀደም ሲል ከተፈናቃዮቹ ጋር ምክክር ማድረጋቸው ተገልጧል ። በምክክሩ ወቅትም ተፈናቃዮቹ የሚሰሟቸውን የፀጥታ ስጋቶች መግለጣቸውን አስተያየት ሰጪዎች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። ተፈናቃዮች ከተፈናቀሉባቸው አከባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖባቸዋል ወደተባሉ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ባለፈው እሁድ ማለዳ 14 አውቶብሶች ተፈናቃዮቹን ጭነው መውጣታቸውም ተገልጧል ። 

የተፈናቃዮች ፍላጎት

በ2013 ዓ.ም. በተፈጠረው የፀጥታ አለመረጋጋት ከምስራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ ተፈናቅለው ደብረ ብርሃን የተጠለሉትና አሁንም ድረስ በዚያው ያሉት ተፈናቃይ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት የፀጥታ ይዞታው ቢረጋጋና ወደ የቀድሞ ቀዬያቸው ቢመለሱ ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሁንም ድረስ ግን ወደ ነባሩ ቀዬያቸው የመመለስ እድሉን የሚጠባበቁት እኚህ ተፈናቃይ፤ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖበታል ወደ ተባለባቸው የኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች እሳቸው ከሚገኙበት የደብረ ብርሃን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ መጀመሩን አመልክተዋል፡፡

"ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ስም ዝርዝራቸው የመጣላቸው በፍላጎታቸው ተመዝግበው እየተመለሱ ነው” ያሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ በተፈናቃዮቹ ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ጉጉት እንጂ ተፈናቃዮችን በኃይል ተጭኖ የመመለስ አዝማሚያ አለማስተዋላቸውንም ገልጸዋል፡፡

መንግስት ከተፈናቃዮች ጋር ያደረገው ውይይት

አስተያየት ሰጪው ከሁለቱ ክልሎች እና ፌዴራል መንግስት የተውጣጡና ከተፈናቃዮቹ ጋር ምክክር ያደረጉት ባለስልጣናት አስቀድሞ ተፈናቃዮቹ ያነሱዋቸው የነበሩ ስጋቶችን ማንሳታቸውንም አክለው አብራርተዋል፡፡ "ከኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች እንዲሁም ከፌዴራል የመጡ ባለስልጣናት ሙሉ ሕዝቡን አወያይተው ነበር፡፡ ተፈናቃይ ህዝቡም የጥታ ስጋቱን በማንሳት ወደ ቀዬያቸው የመመለስ ፍላጎታቸውን አንጸባርቀውላቸዋል” ነው ያሉት፡፡

የተጀመረው ተፈናቃዮችን የመመለስ ሂደት

እሁድ ማለዳ ተፈናቃዮች ከተፈናቀሉባቸው አከባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖባቸዋል የተባሉ የምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ወረዳዎች እንዲሁም የምዕራብ ሸዋ ባኮ ቲቤ እና ዳኖ ወረዳዎችን መዳረሻ ያደረጉ 14 አውቶብሶች ተፈናቃዮቹን ጭነው መውጣታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

ተፈናቃዮች በአማራ ክልል፤ በከፊል
ተፈናቃዮች በአማራ ክልል፤ በከፊል ። ፎቶ ከማኅደርምስል Alemenw Mekonnen/DW

አስተያየታቸውን የሰጡን ሌላው የምስራቅ ወለጋ ተፈናቃይ በ2014 ዓ.ም. በአከባቢያቸው በተከሰተው የፀጥታ አለመረጋጋት ወደ ደብረብርሃን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፕ ቢገቡም፤ ከሰሞኑ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬያቸው ለመመለስ በተጀመረው ሥራ በመጀመሪያው ዙር ጉዞ ከደብረብርሃን ወደ ተፈናቀሉበት አከባቢ ተመልሰዋል፡፡ ተፈናቃዩ በአስተያየታቸው የተፈናቀሉበት የምዕርብ ሸዋ እና ምስራቅ ወለጋ አዋሳን አከባቢ አሁናዊ የጸጽታ ይዞታው ተሻሽሏል በሚል ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ በመንግስት በቀረበ ጥሪ መሰረት መመለሳቸውንም ነው የገለጹት፡፡ «አስቀድሞም የፀጥታ ችግሩ ሙሉ በሙሉ አለመፈታቱን አንስተን የመመለሱን ሁኔታ ሞግተናል፡፡ ግን ደግሞ መንግስት አወያይቶን ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ስላለን ተመልሰናል” ብለዋልም፡፡

እኚህ አስተያየት ሰጪ ተፈናቃይም እሳቸውን ጨምሮ ወደ ተፈናቀሉበት አከባቢ የተመለሱ ተፈናቃዮች በግዳጅ ሳይሆን በፍላጎታቸው መመለሳቸውን ነው ያስረዱትም፡፡

"ሌላ መጠለያ”

እኚህ ተፈናቃይ በአስተያየታቸው በአሁኑ ወቅት ከደብረብርሃን መጠለያ ወጥተው ወደ ትውልድ አከባቢያቸው እንዲመለሱ ቢደረግም፤ አሁንም ግን ወደ ቀዬያቸው አለመመለሳቸውን በማስረዳት በአከባቢው ሌላ መጠለያ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ "አንጻራዊ ሰላም አለ ብሎ ወረዳው ባመነበት ነው ያስቀመጠን፡፡ በቀጣይ ምን ሊሆን እንደሚችል ፈጣሪና መንግስት ያውቃሉ” ብለዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ተፈናቅለው በቆዩባቸው ካምፖች ከፍተኛ የምግብ እና ጤና ድጋፍ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱ ወደ ነባር ቀዬያቸው የመመለሱን ሃሳብ እንዲደግፉ እንዳነሳሳቸውም አልሸሸጉም፡፡

ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ይገኛሉ
ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ይገኛሉ ።ተፈናቅለው በቆዩባቸው ካምፖች ከፍተኛ የምግብ እና ጤና ድጋፍ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱም ይነገራል ምስል Privat

የተፈናቃዮች አመላለስ ሂደት ላይ ዶይቼ ቬለ ከኦሮሚያ ክልል የርዳታ ማስተባበሪያ (ቡሳ ጎኖፋ ጽ/ቤት) እና ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቢጥርም ኃላፊዎቹ በቅርቡ በጉዳዩ ላይ ሰፊ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ገልጸው፤ ለጊዜው ግን ተጨማሪ ማብራሪያ ሳይሰጡን ቀርተዋል ፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ