1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአፍሪቃ የዘር ሐረግ የሚመዘዙት ድንቅ የአውሮጳ ተጨዋቾች

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 6 2016

በእሁዱ የዩሮ 2024 የፍጻሜ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን ትገጥማለች ። ከአፍሪቃ የዘር ሐረግ የሚመዘዙት እንደ ላሚን ያማል፣ ኒኮ ዊሊያምስ እና ቡካዮ ሳካ ያሉ ተጫዋቾችም ውድድሩን አድምቀዋል ። በእሁዱ የፍጻሜ ፍልሚያ የትኛውም ቡድን የአሸናፊነት ክብሩን ይቀዳጅ ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ግን ማንነታቸውን ከወዲሁ አስመስክረዋል ።

https://p.dw.com/p/4iF0k
አዳጊው ላሚን ያማል ባቆጠረው ድንቅ ግቡ ስፔንን ለፍጻሜ አብቅቷል
አዳጊው ላሚን ያማል ባቆጠረው ድንቅ ግቡ ስፔንን ለፍጻሜ አብቅቷልምስል Manuel Blondeau/AOP.Press/IMAGO

አፍሪቃ፦ የእግር ኳስ ጠቢባን መፍለቂያ

«ዩሮ 2024፦ አፍሪቃ የእግር ኳስ ጠቢባን ሲራቀቁ ዕያየች ነው» ይለናል በካይ ኔቤ የቀረበው ዘገባ ። እንደሚከተለው ለአድማጭ በሚመች መልኩ አሰናድተነዋል ።

በእሁዱ የዩሮ 2024 የፍጻሜ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን ትገጥማለች ። ከአፍሪቃ የዘር ሐረግ የሚመዘዙት እንደ ላሚን ያማል፣ ኒኮ ዊሊያምስ እና ቡካዮ ሳካ ያሉ ተጫዋቾችም ውድድሩን አድምቀዋል ። በእሁዱ የፍጻሜ ፍልሚያ የትኛውም ቡድን የአሸናፊነት ክብሩን ይቀዳጅ ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ግን ማንነታቸውን ከወዲሁ አስመስክረዋል ።

ሁለቱ የስፔን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የክንፍ ተጨዋቾች  በዩሮ 2024 ግጥሚያ  እንዲያቆሟቸው የተመደቡ የየትኛውም ሀገር ተከላካዮች ፈርዶባቸዋል ማለት ይቻላል ። የፍጻሜ ግጥሚያው እስከተደረገበት ቀን ከ16ኛ ዓመቱ ያልዘለለው ላሚን ያማል ከኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሞሮኮ ወላጆች ነው የተወለደው ። ይህ ድንቅ የኳስ ጥበበኛ 17ኛ ዓመቱ የሚሞላው በአውሮጳ ፍጻሜ ጨዋታ ማግስት ነው ።  ይህ የባርሴሎና ቡድን አዳጊ ተጨዋች በዩሮ ታሪክ ትንሹ ተሰላፊ ነው ። ያም ብቻ አይደለም በግማሽ ፍጻሜው ፈረንሳይ ላይ ድንቅ ግብ በማስቆጠርም በዩሮ የእግር ኳስ ታሪክ ትንሹ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ተመዝግቧል ።

«ያማል ገና ብሩኅ ተስፋ ያለው አፍላ ጮርቃ ተጨዋች ነው ዛሬ ግብ ያስቆጥራል ብዬ እገምታለሁ »

ጨቅላው ላሚኔ ያማል ሲጠመቅ
ባለ ረጅም ፀጉሩ ወጣት ሊዮኔል ሜሲ ከጨቅላው ላሚኔ ያማል ጋር ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2007 የባርሴሎናውን ኮከብ ለማግኘት በተደረገ እጣ የላሚኔ ያማል ወላጆች አሸንፈው ነበር ከሊዮኔል ሜሲ ጋ በላሚኔ ያማል ጥምቀት ወቅት ፎቶ የተነሱት ። አሁን ላሚኔ ያማልም ሆነ ሊዮኔል ሜሲ ሁለቱም በየአኅጉራቸው ሃገራቸውን ለድል ለማብቃት ጫፍ ደርሰዋል ምስል Joan Monfort/AP Photo/picture alliance

ስፔናዊው የላሚን ያማል አድናቂ ላሚን ግብ ባስገባበት ቀን ከጨዋታው በፊት የሰጠው ግምት ነው ። በእለቱ በእርግጥም የስፔኑ ደጋፊ ግምት ሠርቷል ። ያማል ስፔንን ለፍጻሜ ያበቃትን ድንቅ ግብ ከመረብ አሳርፏል ።  ሌላኛው የስፔን ድንቅ ኒኮ ዊሊያምስ የተወለደው አሰቃቂውን  የሰሐራ በረሃ አቋርጠው ስፔን አዲስ ሕይወት ከጀመሩ ጋናውያን ቤተሰቦች ነው ። ኒኮ በአትሌቲኮ ቢልባዎ ቡድን በስፔን ላሊጋ ከታላቅ ወንድሙ ኢናኪ ዊሊያምስ ጋ በመሰለፍ ቡድኑ የነበረበትን ዋንጫ የማንሳት ድርቀት ባለፈው የጨዋታ ዘመን ወደ ታሪክነት ቀይረውታል ። ኢናኪ ዊሊያምስ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2022 ለጥቋቁር ከዋክብቱ የጋና ብሔራዊ ቡድን በመሰለፍ ብቃቱን አስመስክሯል ። 

ታናሽ ወንድሙ ዘንድሮ ዋንጫ ለማንሳት ጫፍ ደርሷል ። በእርግጥ የስፔን ቡድን ጨዋታ ውጤት በላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ብቻ የሚገደብ አይደለም ።  ግን ደግሞ እነ ያማልም ሆኑ ሌሎች ከአፍሪቃ ሐረግ ከሚመዘዝ ቤተሰብ የሚወለዱ የዩሮ 24 ተሳታፊ ሃገራት ተጨዋቾች ለአውሮጳው እግር ኳስ ልዩ ቅመም ናቸው ። ይህን ያሉት ጃኮብ ሙሌ ናቸው፤ የኬንያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኝ  ።

ስፔን የዩሮ 2024 ክብርን ለመቀዳጀት በምታደርገው ጥረት ሁለቱ ምርጥ ተጨዋቾች ማለትም ላሚኔ ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ እጅግ ወሳኝ ናቸው
ስፔን የዩሮ 2024 ክብርን ለመቀዳጀት በምታደርገው ጥረት ሁለቱ ምርጥ ተጨዋቾች ማለትም ላሚኔ ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ እጅግ ወሳኝ ናቸው ምስል Irakli Gedenidze/REUTERS

«ከአፍሪቃ የዘር ሐረጋቸው የሚመዘዝ ተጨዋቾች ምናልባትም በርካታ የአውሮጳ ተጨዋቾች ያጡት ነገር አላቸው ። ምክንያቱም አፍሪቃውያን ተጨዋቾች ኳስ ሲጫወቱ የደነሱ ያህል ነው ። መድረክ ላይ የወጡ ነው የሚመስለው ። ለጨዋታው የሚሰጡት የተለየ ውበት አለ ። ማለቴ ጄጄ ኦካቻን ተመልከቱ፤ እንደ ኬሊያን እምባፔ ያሉ ተጨዋቾችን እዩ፤ ቡካዮ ሳካን ሳይቀር ተመልከቱ፤ ለጨዋታው የሚሰጡት የተለየ ቅመም አለ ። ያን የተወገደ ጊዜ ጨዋታው በሙሉ ወዝ አልባ ነው የሚሆነው ባይ ነኝ ።»

እነዚህ እና ሌሎች ከአፍሪቃውያን ቤተሰቦች የሚወለዱ ተጨዋቾች በውድድሩ ላይ መድመቃቸው በአፍሪቃ ልዩ ትኩረትን ስቧል ።

እንግሊዝ በዘንድሮ ውድድር ለውጥ ዐሳይታለች፤ ግን ደግሞ የቀድሞውን ዩሮ ፍጻሜ ሽንፈት መቀልበስ ትሻለች
እንግሊዝ በዘንድሮ ውድድር ለውጥ ዐሳይታለች፤ ግን ደግሞ የቀድሞውን ዩሮ ፍጻሜ ሽንፈት መቀልበስ ትሻለችምስል BEAUTIFUL SPORTS/Orangepictures/picture alliance

«በአሁኑ ወቅት  ዩሮ 2024  ጀርመን ውስጥ እየተካሄደ ነው ። ፍላጎት ከፍተኛ ነው ። አብዛኞቹ የሬዲዮ ጣቢያዎች የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን እየሰጡ ነው ። ሰዉ በሙሉ በዩሮ ወቅት ቴሌቪዥን ላይ ተለጥፎ ነው የሚውለው ።»

በአውሮጳ ምድር ገንነው የወጡት ከአፍሪቃ ዘራቸው የሚመዘዝ ተጨዋቾች በእየ ፊናቸው ቡድናቸውን ለልዩ ክብር አብቅተዋል ። ያም ብቻ አይደለም ። የእነዚህ ተጨዋቾች ስኬት ለብዙዎች በአፍሪቃ ምድር ላሉ አዳጊዎችም ራሳቸውን ወደፊት አሻግረው የሚመለከቱበት አንዳች ተምሳሌት በመፍጠር አርአያነቱ እጅግ ላቅ ያለ ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ