ከሠላሳ በላይ የፊንጫ ስኳር ፍብሪካ ሠራኞች ታሰሩ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30 2017በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሱሉላ ፊንጫ ወረዳ ውስጥ ከ30 በላይ የፊንጫ ስኳር ፍብሪካ ሠራተኞች መታሰራቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች ለዶይቸ ቬለ ተናገሩ ። ሠራተኞቹ የታሰሩት በፋብሪካው ይዞታ ውስጥ በሕገ ወጥ የእርሻ ተግባር ተሠማርታችኋል በሚል መሆኑ ተገልጿል ። በፋብሪካው ይዞታ ውስጥ ሕገ ወጥ እርሻ መታረሱን እና በዚህ ዓመት በተደጋጋሚ በፋብሪካው ሸንኮራ አገዳ ላይ ቃጠሎ መድረሱን ተከትሎም በቅርቡ በአካባቢው በሕገ ወጥ መንገድ እርሻ አረሱ የተባሉ ሰዎችም ምርታቸው በወረዳው አስተዳዳር መወረሱን እና የፋብሪካውን ሠራተኞች ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችና ነጋዴዎች መታሰራቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጠዋል ። በአካባቢ በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ የፍብሪካው ሠራተኞች እንዳሉም አንድ ነዋሪ ጠቁመዋል ። ለዝርዝሩ የአሶሳ ወኪላችን ነጋሣ ደሳለኝ ።
ሠራተኞችን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ታስረዋል
በፊንጫ ስኳሪ ፍብሪካ ይዞታው ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ በእርሻ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል ከተባሉት ነዋሪዎችንና የፋብሪካው ሠራተኞች መካከል ግማሹ ከታሰሩ ሦስት ሳምንታት መቆጠሩ ተገልጸዋል ፡፡ አንድ የፋብሪካው ሠራተኛ ባለቤታቸው በቅርቡ መታሰራቸውን የነገሩን ነዋሪ በፋብሪካው ይዞታ ላይ ጫካ በመመንጠር አርሰዋል በሚል ተጠርጥሮ ባለቤታቸው መታሰሩን አመልክተዋል፡፡ በአካባቢው በሕገ ወጥ መንገድ እርሻ መታረሱትን ተከትሎ የፋብሪካው የአገዳ ምርት ለውደመት ተዳርገዋል በማለት የወረዳው አስተዳዳር ከ3 መቶ በላይ ሰዎችን ከዚህ ቀደም ማሰሩን የገለጹት ነዋሪዋ ባለበታቸው የረጅም ጊዜ የፋብሪካው ሠራተኛ መሆኑን በእርሻ ሥራ አለመሳተፉን ጠቁመዋል፡፡
«በፋብሪካ ይዞታ ውስጥ አረሳችሁ ብለው ነው ያሰሩት፡፡ ከታሰረ 3 ሳምንት ሆኖታል ያረሱት ሌሎች ናቸው ጉዳያቸውን ከሳምንት በኃለ እናጣራለን ብለውናል፡፡ በሕገ ወጥ መንገድ እርሻ አርሳችሀል በማለት ነው ብዙ ሰው የታሰረው፡፡ በእዛ ቦታ ላይ በህገ ወጥ መንገድ አረሱ የተባሉ ሰዎች ምርት ተጭነዋል፡፡ በትክክል በፋብሪካ ይዞታ ላይ ያረሱ የታሰሩ ሰዎች አሉ፤ ሌሎችም ሰዎች ደግሞ በጀምላ ታስረዋል፡፡»
ሕገ ወጥ እርሻ በፋብሪካው አገዳ ምርት ላይ ጉዳት አድርሰዋል
በህዳር ወር 2017 ዓ.ም ሁለት ጊዜ በተነሳው የእሳት አደጋ ከ60 በላይ ሄክታር የፋብሪካው የሸንኮራ አገዳ ምርት ላይ ጉዳት መድረሱ ተዘግበዋል፡፡ በወቅቱ በአካባቢው በሕገ ወጥ መንገድ በፋብሪካው ይዞታ ላይ የተዘራው ምርት ሲሰበሰብ ለወረዳው አስተዳደር ገቢ እንዲሆን መደረጉን ተከትሎ በቦታው በዚሁ ድርጊት የተነሳሱ ግሰለቦች በአገዳው ምርት ላይ ጉዳት አድርሰዋል በማለት ሰዎች መታሰራቸውን ሌላው አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካቢው ነዋሪ ገልጸዋል፡፡ በፋብሪካው ይዞታ ውስጥ በእርሻ ሥራ ተሰማሩ ከተባሉ ግለሰቦች ጋር ይሠራሉ የተባሉ ሠራተኞችም ተጠርጥረው መታሰራቸውን ገልጸው በፋብሪካው ይዞታ ላይ የተመረቱ የምርት ግብዓቶችንም የወረዳው አስተዳዳር መውሰዱን አክለዋል፡፡
ታሰሩ የተባሉ የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞችን በተመለከተ የፋብሪካው ሠራተኞች ማኅበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ጠና ሙሌታ የታሠሩ ሠራተኞች መኖራቸውን በማረጋገጥ ስለ ጉዳዩ ዝርዝር መረጃ የለንም ብሏል፡፡
የታሰሩት ተጠርጣሪዎች ናቸው ተብሏል
«የታሰሩ ሰዎች ብዙ ናቸው ተጠርጣሪ ናቸው ተብሎ ነው የተያዙት የተጠረጠሩበትን ምክንያት እና የታሰሩት ሰዎችን ብዛት ለጊዜ አላወቅነም» የሚል ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በወረዳው ታሰሩ የተባሉ ሰዎችንና በሕገ ወጥ መንገድ እርሻ ሥራ ላይ ተሳትፈዋል የተባሉ ሰዎች ምርት ወረዳው አስተዳደር ተወስዷ መባሉን አስመልክቶ ማብራሪያ የጠቅናቸው የሱሉላ ፍንጫአ ወረዳ አስተዳደሪ አቶ ፋንታሁን ታዬ በጉዳዩ ላይ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ምላሽ እንደሚሰጡን ቃል ቢገቡም በተባለው ሰዓት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡
በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሱሉላ ፍንጫ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ሰው ሠራሽ ጉዳቶች እየደረሰበት እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኙት የስኳር ፋብሪካዎች መካከል ከፍተኛው የስኳር ምርት የሚገኝበት የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ አንዱ መሆኑን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ነጋሣ ደሳለኝ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ