1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የኢንተርኔት አፈና በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ መስከረም 23 2016

ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሀገራት በኢንተርኔት አፈና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን መረጃ የማግኘት መብት ነፍጓል።አንጋፋው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ እንደሚለው የሰዎች መረጃ የማግኘት መብት ከሰብዓዊ መብቶች ውስጥ አንዱ በመሆኑ መረጃን ማገድ ሰብዓዊ መብትን መርገጥ ነው።

https://p.dw.com/p/4X5cY
የኢንተርኔት አፈናን መንግስታት መረጃ ለማፈን ይጠቀሙበታል
የኢንተርኔት አፈና በምርጫ፣በተቃውሞ እና በግጭት ወቅቶች ይበረታልምስል Avishek Das/ZUMA Wire/picture-alliance

የቀጠለው የኢንተርኔት አፈና በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያን ጨምሮ በስድስት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪቃ ሃገራት የኢንተርኔት የመዝጋት አፋኝ ልማድ እየጨመረ መምጣቱን ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን በቅርቡ አስታውቋል። በዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በኢትዮጵያ የሚታየው የኢንተርኔት አፈና መረጃ በማግኘት መብት እና በጋዜጠኞች ሥራ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ይቃኛል።  መስከረም 17 ቀን፣ በየዓመቱ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የመረጃ ተደራሽነት ቀንን አስመልክቶ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን /Reporters Without Borders/ በፈረንሳይኛ ምህጻሩ /RSF/ ያለፈው ዓርብ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ ስድስት የአፍሪቃ ሀገራት ሆን ተብሎ ኢንተርኔት በመዘጋቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መረጃ የማግኘት መብታቸው ተነፍጓል።
በኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዚያት በከፊል እና በሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎት ሲዘጋ የቆዬ ሲሆን፤ለአብነትም በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሃት መካከል የተካሄደውን ጦርነት ተከትሎ በትግራይ ክልል ከሁለት ዓመታት በላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል። በቅርቡ በአማራ ክልል የተፈጠረውን ውጥረት ተከትሎ በነሐሴ ወር የኢንተርኔት አገልግሎት ብዙ ጊዜ መቋረጡን የዓለምን የኢንተርኔት ትራፊክ ከሚከታተለው ክላውድፍሌር ራዳር/Cloudflare Radar/ ከተባለው ድርጅት መረጃ ማግኘቱን  ገልጿል። ይህ  አዝማሚያም በጋዜጠኞች ሥራ ላይ መዘዝ እንዳለው ድርጅቱ አመልክቷል።የአማራ ክልል ፀጥታና ኢንተርኔት
የዶቼቨለ የአማርኛው ክፍል ምክትል ሀላፊ አንጋፋው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ በወጣው መግለጫ ግኝት ይስማማል።«ድንበር የለሽ የዘጋቢዎች ወይም የጋዜጠኞች ቡድን ያወጣው መግለጫ ትክክል ነው።የሚያሳዝነው ነገር ይሄው ድርጅት በ2018 ወይም 2019 አካባቢ ኢትጵያ ከፍተኛ የሆነ የፕሬስ ነጻነት መሻሻል አሳይታለች ብሎ እንዲውም አንደኛው ጉባኤ አዲስ አበባ እንዲካሄድ እንደ ማበረታቻ እና እንደ ምሳሌ ተብሎ እዚያ ተደርጎ ነበረ ያኔ ሁላችንም ተስፋ አድርገን ነበረ።ከፖለቲካው ለውጥ ጋር ሚዲያው ወይም የጋዜጠኞች መብትም አብሮ ይከበራል፣ የሰዎች መረጃ የማግኘት መብትም ይከበራል እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ተመልሳ በፊት ወደነበረችበት እንዲያውም ከዚያ በከፋ ደረጃ መድረሱን የሚያሳይ ነው።» በማለት ገልጿል።
እንደ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ኢንተርኔት በመዝጋት የመረጃ ፍሰትን ማወክ እና የጋዜጠኞች ዜና እንዳይዘግቡ ማደናቀፍ እንዲሁም የመረጃ ድረ-ገጾችን ማገድ  እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከሰሃራ በታች ያሉ ሃገራት  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየጨመረ  መጥቷል።«በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ከሰብአዊ መብት አንጻር እንዴት ይታያል?»

አንጋፋው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ
ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ የዶቼ ቬለ የአማርኛው ክፍል ምክትል ሀላፊምስል Florian Görner/DW

ምርጫ ፣ግጭቶች እና ተቃውሞዎችን አስታኮ ኢንርኔትን መዝጋት

የኢንተርኔት መዘጋት ጫናዎቹ ከምንም ጊዜ በላይ በምርጫ እና በተቃውሞ  ወቅት እንደሚበረታ የገለፀው ድርጅቱ ፤ ከዚህ ዓመት መጀመሪያ አንስቶም  ኢትዮጵያን ጨምሮ በስድስት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት ማለትም /በሴኔጋል፣ ሞሪታኒያ፣ ጊኒ፣ ጋቦን፣ እና ዚምባብዌ/ ቢያንስ 12 ዋና ዋና የኢንተርኔት መዝጋቶች መመዝግባቸውን አክሰስ ናው/Access Now/  እና ኪፕ ኢት ኦን /#KeepItOn/ ከተባሉ  መንግሥታዊ ያልሆኑ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች መረጃ ማግኘቱን ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን አመልክቷል። ቡድኑ አያይዞም የእነዚህ ሃገራት መንግሥታት የተለያዩ አጋጣሚዎችን  የፕሬስ ነፃነትን እና የመረጃ ተደራሽነትን ለመገደብ እንደ መሳሪያ እንሚጠቀሙ ገልጿል።
የሰዎች መረጃ የማግኘት መብት ከሰብዓዊ መብቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን የሚጠቅሰው አንጋፋው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ በኢትዮጵያም የተለያዩ ግጭቶች ሲከሰቱ ኢንተርኔት፣ ስልክ እና የማኅበራዊ መገናና ዘዴዎች ዒላማ ሲሆኑ ታዝቧል።  
«በኢትዮጵያ ግጭትም ይሁን አለመግባባትም ይሁን ወይም የህዝብ ተቃዉሞ በተነሳ ቁጥር የመጀመሪያው ታርጌት የመገኛ ዘዴ ነው።በፊት የተለመደ ወይም ብዙ የሚወራለት ራዲዮ እና ቴሌቪዥን የመሳሰሉትን ጃም ማድረግ ወይም እዚያ አካባቢ እንዳይሰማ ማድረግ ነበር።አሁን ግን የመንግስት እርምጃ ምንም አይነት መረጃ እንዳሰራጭ ስልክም ጭምር መዝጋት ነው።ቀደም ሲል በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ አካባቢ ጥቃት እና ግጭት ደረሰ ሲባል ኢንተርኔት ስልክም ጭምር ተዘግቶ ነበር።» ካላ በኋላ  ከዚያ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አባቶች መካከል የተከሰተውን አለመግባባት ተከትሎ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መዘጋታቸውን አስታውሷል።ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ«የሰሜን ኢትዮጵያ በምንለው ጦርነት  ውጊያ በነበረባቸው አካባቢዎች በተለይ በትግራይ የስልክ መገናኛ ሁሉ ተቋርጦ ነበረ።»ሲል ተናግሯል።ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርኔት እንደታገደ ነው

የኢትዮቴሌኮም 5G የኢንተርኔት አገልግሎት
«ሌሎች የግል የቴሌኮም ኩባንያዎችን ማሳተፍ በኢትዮጵያ እየጨመረ ለመጣው የኢንተርኔት አፈና መፍትሄ ነው»ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ ምስል Solomon Muchiee/DW

የመረጃ ተደራሽነትን መገደብ እና የጋዜጠኞች እስር

 የመረጃ ተደራሽነትን ከመገደብ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የመረጃ አቅራቢ ጋዜጠኞችን ማሰርም ሌላው የጥቃት ገፅታ ነው።
«ሰዎች መረጃ የማግኘት መብት መንፈግ ብቻ ሳይሆን ጋዜጠኞችም  በአጠቃላይ የመገናኛ ዘዴ ባለሙያዎች ስራቸውን እንዳይሰሩ ነው የተደረገው።በነገራችን ላይ ኢንተርኔት በመዝጋት ብቻ አይደለም ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞችን ወይም ነፃ ነን ብለው በየ ማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰሩ ወይም መረጃ የሚያሰራጩ ሰዎችን ማሰር ጭምር አለ።በጣም አሳሳቢ ነው። የሰዎችን መረጃ የማግኘት መብትን መንፈግ ከሰብዓዊ መብት አንዱ ነው።ሰብዓዊ መብትን ከመርገጥ የሚቆጠር ነው።ይህም በጋዜጠኞች አቅም ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ህዝቡ መጠየቅ ያለበት ይመስለኛል።ሌላ ደግሞ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዚህ ረገድ ግፊት ማድረግ ያለበት ይመስለኛል።በጣም አሳሳቢ ነው።የወደፊቱ ሂደት እንዴት ሊቀጥል ይችላል የሚለውም ብዙ ሊያነጋግር ይችላል።»የመንግሥት ተቺ ጋዜጠኞች እስር መቀጠሉ
ከዚህ በተጨማሪ ዓለም ወደ ዲጅታል ቴክኖሎጅ እየሄደች ያለችበት ወቅት በመሆኑ እና ኢትዮጵያም ከዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውጭ መሆን ስለማትችል፤ የሀገሪቱ መንግሥትም ከዚህ እውነታ ጋር ራሱን ማስማማት እንዳለበትም ይገልፃል።
በመንግስት በኩል «ትክክለኛ የሆነ የፖለቲካ መርህ መጓደል ያለ ይመስለኛል»የሚለው ነጋሽ ምንም እንኳ መንግስት ትልቁን ድርሻ መውሰድ ቢኖርበትም፤ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ዘዴዎች አካባቢ የሚሰሩ እንዲሁም ሊሂቃን  ሊያስቡበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አብራርቷል።«ዓለም በጣም እየጠበበች አንደኛው ከአንደኛው ክፍል ጋር በቀላሉ የሚገናኝበት  ዘመን ላይ ነው ያለነው።ስለዚህ መረጃ በጣም ትልቅ ቦታ አለው።የመረጃ መጓደል ብቻ ሳይሆን መዘግየቱ ራሱ በሰዎች የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድርበት ዘመን ላይ ነው የደረስነው።» ዓለም ወደ ዲጅታል እየተገባ ነው ኢትዮጵያም «እኔ ራዲዮ ቢቀጥል ደስ ይለኛል።ዓለም ግን ይህንን የሚፈቅድበት ደረጃ አይደለም።ነገር ግን ወደ ዲጅታል የግድ እየተገባ ነው።ኢትዮጵያ ደግሞ ራሷን ደሴት አድርጋ ከሌላው ዓለም ተነጥላ ልትቀጥል አትችልም።»ካለ በኋላ፤ በፖለቲካ ስልጣን ላይ ያሉ ወገኖች  መረጃ ከመንፈግ አንፃር ራሳቸውን መፈተሽ አለባቸው ብሏል።ለዚህም ቀዳሚው የመንግሥት ሥራ ሰላም እና መረጋጋትን ማስፈን ነው ይላል።

ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ የዶቼቨለ የአማርኛው ክፍል ምክትል ሀላፊ
«የሰዎች መረጃ የማግኘት መብት ከሰብዓዊ መብቶች ውስጥ አንዱ በመሆኑ መረጃን ማገድ ሰብዓዊ መብትን መርገጥ ነው» አንጋፋው ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድምስል Solomon Muchie/DW

የኢንተርኔት መዘጋት በዶቼ ቬለ የአማርኛው ክፍል የፈጠረው ጫና 
ለመሆኑ እንደ አንድ የመረጃ አቅራቢ ድርጅት ዶቼቬለ በተለይም የአማርኛው ክፍል ምን ያህል የእነዚህ ችግሮች ሰለባ ነው? በቅርቡ የተሻሻለው አዲሱ ድረ-ገፅስ? ነጋሽ ማብራሪያ አለው።
«አዲሱ ዌብሳይታችን ስንጠቀምበት ከነበረው በጣም የተሻለ የዘመኑ ቴክኖሎጅ የፈቀደውን ሁሉ ሊያስተናግድ እና ሊፈቅድ የሚችለውን ሁሉ ያየዘ ነው።አንባቢዎች በጽሁፍ ማንበብ ለሚፈልጉ ያንን ማግኘት ይችላሉ።ድምጽ መስማት የሚፈልጉም መስማት ይችላሉ።ምናልባት በጥቂት ጊዜ ውስጥ በአንድ ወር በሁለት ወር ደግሞ በቪዲዮ ስርጭት እንጀምራለን የዩቱብ አይነት።»  ነገር ግን ዶቼ ቬለ መረጃ ለማድረስ የቱንም ያህል ቢተጋ በኢትዮጵያ በየ ጊዜው የሚደረገው የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎቶች መቋረጥ መረጃ ለማግኘትም ሆነ መረጃ ለማድረስ እንቅፋት በመሆኑ ዶቼ ቬለም የችግሩ ሰለቫ መሆኑን ጋዜጠኛ ነጋሽ መሀመድ አመልክቷል።ለዚህም በሀገሪቱ የተለያዩ  የግል የቴሌኮም አቅራቢ ኩባንያዎች መኖር መፍትሄ መሆኑን ጠቁሟል።ኢትዮ ቴሌኮም ስለ ኢንተርኔት ገደቡ ምን አለ?

በኢንተርኔት አፈና ላይ የድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን አቋም 
በአክሰስ ናው እና የ#KeepItOn ዘመቻ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ፌሊሺያ አንቶኒዮ በበኩላቸው የአፍሪቃ መንግሥታት የኢንተርኔት መዘጋት እንደ መሳሪያ በመጠቀም እንደ ምርጫ ፣ግጭቶች ወይም ቀውሶች እና ተቃውሞዎችን የመሳሰሉ  ሀገራዊ ኩነቶችን  አስታከው ፣የመረጃ ተደራሽነትን ያግዳሉ።
ይህም የሰዎችን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል እና የተከሰቱ ቀውሶችን በእጅጉ ሊያባብስ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ከዚህ የተነሳ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪቃ ሃገራት መንግሥታት የኢንተርኔት የመዝጋት አፋኝ ልማድን እንዲያቆሙ ድንበር የለሹ የጋዜጠኞች ቡድን ጠይቋል።
ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን  የበይነመረብ የዜና ማሰራጫዎች ላይ የሚደረገውን  ሳንሱር ለመቅረፍ በጎርጎሪያኑ 2015 ዓ/ም «ኦፕሬሽን ኮንላተራል ፍሪደም»የሚባል ዘመቻ ጀምሯል። ይህ ዘመቻ የዜና ማሰራጫዎች መዳረሻ ሲታገድ  ሳንሱር ከተደረጉባቸው ሀገራት ውጭ ባሉ ሰርቨሮች ላይ ትይዩ ጣቢያዎችን በመፍጠር ተደራሽ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን የጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ