1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢሰመኮ መግለጫ በጉራጌ ዞን የሰብአዊ ጉዳቶች ዙሪያ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 16 2016

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመዋቅር እና የአስተዳደር ጥያቄዎች ለሰላም እጦት ምክንያት መሆናቸው እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዐስታወቀ ፡፡ በክልሉ በጉራጌ ዞን እና በቀቤና ልዩ ወረዳ መካከል የነበረው አለመግባባት በአካባቢው የፀጥታ መደፍረስን ማስከተሉን ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው የምርመራ ሪፖርቱ ዐስታውቋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4aacA
የወልቂጤ ከተማ
የወልቂጤ ከተማ መንገድምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

በጉራጌ ዞን የግጭቱ መነሻ እና የደረሰው ጉዳት

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመዋቅር እና የአስተዳደር ጥያቄዎች ለሰላም እጦት ምክንያት መሆናቸው እንዳሳሰበው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዐስታወቀ ፡፡ በክልሉ በጉራጌ ዞን እና በቀቤና ልዩ ወረዳ መካከል የነበረው አለመግባባት በአካባቢው የፀጥታ መደፍረስን ማስከተሉን ኮሚሽኑ ዛሬ ባወጣው የምርመራ ሪፖርቱ ዐስታውቋል ፡፡

ኮሚሽኑ ከአካባቢው ነዋሪዎች ቀረበልኝ ባለው የአቤቱታ መነሻነት ከጥቅምት 20 እስከ 25 ቀን፣ 2016 ዓ.ም. በቦታው በመገኘት ምርመራ ማከናወኑንም ጠቅሷል፡፡ በተለይም ከተጎጂዎች እና ከምስክሮች ጋ ቃለ-መጠይቆች ማድረጉን በመጥቀስ ከጉራጌ ዞን፣ ከወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ፣ ከቀቤና ልዩ ወረዳ የሥራ ኃላፊዎች፣ በአካባቢው የሚገኘውን የኮማንድ ፖስት ኃላፊዎች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋ በተናጠል እና በቡድን መወያየቱንም ገልጿል፡፡

የግጭቱ መነሻ እና የደረሰው ጉዳት

የግጭቶቹ መነሻ በቅርቡ በልዩ ወረዳ እንዲዋቀር የተደረገው የቀቤና ብሄር የአስተዳደር መቀመጫው በወልቂጤ ከተማ እንዲሆን በሚደግፉና በሚቃወሙ ቡድኖች መካከል የተነሳው አለመግባባት ወደ ማህበረሰቡ በመዛመቱ መሆኑን ለማረጋገጥ መቻሉን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ጠቅሷል፡፡

በምርመራው ሂደት በተገኘው ውጤት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ለዶቼ ቬለ  የገለጹት በኮሚሽኑ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በጋሻው እሸቱ «በተለይ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ካለፈው የመስከረም ወር ወዲህ ብቻ በተነሱ ግጭቶች አንድ የፌደራል ፖሊስ አባልን ጨምሮ 4 ሰዎች ተገድለዋል ፡፡ አንዲሁም በሌሎች 114 ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል ጉዳት መድረሱን ለማረጋገጥ ቸችሏል» ብለዋል ፡፡

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የምርመራ ዘገባ ጉዳይ ዶይቸ ቬለ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ኃላፊዎችን ማግኘት ባለመቻሉ ሊሳካ አልቻለምምስል Solomon Muche/DW

ምክረ ሃሳብ

ኮሚሽኑ በቀጣይ በክልሉ መስተዳድር ሊከናወን ይገባል ያለውን ምክረ ሀሳብም በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በተለይ በግጭቱ የሞት እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ሊካሱ ይገባል ያሉት በኮሚሽኑ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ በጋሻው «የወደመባቸው ንብረትም ሊተካላቸው አንደሚገባ ጠቁመናል ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በግጭቱ ተዋናይ በመሆን በንጹሃን ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላት በህግ እንዲጠየቁም አሳስበናል» ብለዋል ፡፡

ዶቼ ቬለ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ ) የምርመራ ሪፖርት ዙሪያ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ኃላፊዎችን ማግኘት ባለመቻሉ ሊሳካ አልቻለም ፡፡ ይሁን እንጂ የክልሉ ምክር ቤት በቅርቡ አካሂዶት በነበረው የምክር ቤት ጉባዔ ላይ በክልሉ ግጭቶችን አስቀድሞ ለመከላከልና የሕግ ተጠያቂነት ለማስፈን አቅዶ እየሠራ እንደሚገኝ ርእስ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገልጸው ነበር ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ