1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ የወጣቶች በጅምላ መታሠር

ረቡዕ፣ ኅዳር 14 2015

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ወጣቶች በጅምላ እየታሠሩ ነው ሲሉ የከተማይቱ ነዋሪዎችና የታሳሪ ቤተሰቦች ገለጹ፡፡ በአሁኑወቅት በከተማው አይሪሽ ተብሎ በሚታወቀው አዳራሽ ውስጥ ብቻ ከ200 በላይ ሰዎች ታስረው እንደሚገኙ ነው የተሳሪ ቤተሰቦች ነን ያሉ ለዶቼ ቬለ DW የገለጹት፡፡

https://p.dw.com/p/4JxXZ
Äthiopien Gurage Streik
ምስል privat

የጅምላ እሥር በጉራጌ 

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ወጣቶች በጅምላ እየታሠሩ ነው ሲሉ የከተማይቱ ነዋሪዎችና የታሳሪ ቤተሰቦች ገለጹ፡፡ የጅምላ እሥሩ ባለፈው ዓርብ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዶ ከነበረው በቤትስ ውስጥ የመቀመጥ አድማ ጋር  የተያያዘ ሳይሆን እንዳልቀረ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ መደረጉን ተከትሎ በወጣቶች ላይ የጅምላ እሥር እየተፈጸመ እንደሚገኝ የከተማው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በከተማው ከባለፈው ዓርብ ጀምሮ አሁን ድረስ የፀጥታ አባላት በመንደር ውስጥ ባደረጉት አሰሳ በርካታ ወጣቶችን ይዘው ማሠራቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ በተለይም በከተማው በተለምዶ አይሪሽ ተብሎ በሚጠራው አዳራሽ ብቻ ከ200 በላይ ሰዎች ታስረው እንደሚገኙ የታሳሪ ቤተሰቦች ተናግረዋል፡፡ 

«ሳሙና ሊገዛ የላኩት ልጄ በዛው ተይዞ ታሠረብኝ» ሲሉ ለዶቼ ቬለ የገለጹት ሩቂያ አብዱራዛቅ የተባሉ የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ «ልጄ ከትናንት በስቲያ ሰኞ በፀጥታ አስከባሪዎች እየተደበደበ ነው የተወሰደው ፡፡ ሱቅ በተላከበት ከመንገድ ከመያዙ በስተቀር የታሠረበትን ምክንያት እንኳን አላውቅም ፡፡  አሁ ንላይ የማደርስለትን ምግብ ከመቀበል ውጪ እንዳገኘው እንኳን አልተፈቀደልኝም።» ብለዋል፡፡

አቶ ረመዳን ሰሙ የተባሉ ሌላው የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ  በቤተሰብ አባላቸው ላይ እሥር ተፈጽሞብኛል በሚል ቅሬታ ካሰሙት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ አንዋር ሰሙ የተባለ ታላቅ ወንድማቸው ሰኞ ዕለት እንደታሰረባቸው የሚናገሩት አቶ ረመዳን «ወንድሜ አይሪሽ በተባለው አዳራሽ ውስጥ መታሠሩን ከመስማቴ በስተቀር ላገኘው አልቻልኩም፡፡ አብረን ከመስጅድ በመውጣት ላይ እንዳለን ነበር በፓትሮል ተሽከርካሪ በመጡ የፀጥታ አባላት የተከበብነው ፡፡ እኔን ጨምሮ አብዛኞቻችን ሮጠን ብናመልጥም ወንድሜና ሌሎች ሰዎች ግን ተይዘው ተወስደዋል።» ብለዋል፡፡ተቃውሞ እና እስር በወልቂጤ

ዶቼ ቬሌ DW እየተፈጸመ ይገኛል በተባለው የጅምላ እሥር ዙሪያ ያነጋገራቸው የዞኑ ባለሥልጣናት ሥለጉዳዩ በቀጥታ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ምላሹ በማን ይሰጥ የሚለው ያሳሰባቸው ይመስላል፡፡

የጉራጌ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊው አቶ ያቆብ ግርማ ሰዎቹ የታሰሩት በወልቂጤ ከተማ ፖሊስ በመሆኑ መረጃውን መውሰድ ያለባችሁ ከዚያው ነው ሲሉ የከተማው ሰላምና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ትዕግስቱ ፋጂዎ ደግሞ ምላሹ መሰጠት ያለበት በዞኑ ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ነው ብለዋል ፡፡ ምላሽ ይሰጣሉ ወደ ተባሉት የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ቅባቱ ተሰማ ስልክ ቢደወልም ስብሰባ ላይ ሥለመሆናቸው በአጭር የጹሑፍ መልክት ከመግለጻቸው በስተቀር አሳቸውን አግኝቶ ማነጋገር ባለመቻሉ የዞኑን አስተያት ማካተት አልተቻለም፡፡

Äthiopien Gurage Streik
ከወራት በፊት ጉራጌ ዞን ውስጥ የተካሄደው ተቃውሞምስል privat

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ አምስት ዞኖችና እንድ ልዩ ወረዳን በማካተት የሚመሠረተው አዲስ ክልላዊ መንግሥት አካል እንዲሆን የቀረበለትን ጥያቄ በአብላጫ ድምፅ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ወሳኔውን ተከትሎ የዞኑ አስተዳዳሪን ጨምሮ በርካታ አመራሮች  ከኃላፊነታቸው ሲነሱ ከፊሎቹ ለእሥር መዳረጋቸው የሚታወቅ ነው ፡፡

ምክር ቤቱ ቀደምሲል በክላስተር ላለመደራጀት ያሳለፈውን ውሳኔ መንግሥት ዳግም ሊያስመክርበት ነው የሚሉ መረጃዎች መሠራጫታቸውን ተከትሎ በተለይ በወልቂጤ ከተማ ይህን የሚቃወም በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ባለፈው ዓርብ መካሄዱ ይታወቃል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ