ታላቁ የአፍሪቃ ሩጫ በአሌክሳንደሪያ፤ቨርጂኒያ
እሑድ፣ ጥቅምት 3 2017ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ/ ግራንድ አፍሪካን ረን/ በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በሁለተኛው ቅዳሜ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የሚካሄድ፣የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የመዝናኛ ሩጫ ነው። የታላቁ አፍሪካ ሩጫ መስራችና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ጋሻው አብዛ "አብሮነት መሻል ነው" በሚል መርዕ ትላንት የተካሄደው ይኸው ዝግጅት፣ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማቀራረብ ረገድ ጉልዕ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
"ከሩጫም በላይ ነው፤ማኀበረሰባችንን ማገናኘት፣ ኢትዮጵያ የምትታወቀው በአትሌቲክስ ስፖርት ነውና፣ እንደ መሰባሰቢያ መድረክ አገልግሎ፣ ሁላችንም ተሰብስበን በዓላችንን የምናከብርበት፣ በስራ ዓለም ደግሞ ብዙ አንገናኝም፣ብዙ ኢትዮጵያኖች አለንና መገናኘት የምንችልበት መድረክ ሆኖ፣ በተለይም እንዲህ እንቁ የሆኑ አትሌቶቻችንም ዕንቁ የሆኑ የማኀበረሰባችን አካሎችና በአርቱም በኪነጥበብም ዙሪያ፣ ብርቅዬ አትሌቶች ጋር ቅዳሜ አብሮ ማሳለፍ መቻሉ ትልቅ ነገር ነው።"
በአሜሪካ የሚገኘው ወገኔ የኢትዮጵያውያን ማኀበር ድጋፍ ለኢትዮጵያውያን ችግረኞች
በስፖርቱ ዘርፍ፣ የማራቱን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነችው አትሌት ትዕግስት አሰፋ እና ሌሎች እውቅ የዓለም ሻምፒዮና አትሌቶች በዝግጅቱ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል።
የበጎ አድራጎት ድጋፍ
ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ባዘጋጃቸው ሁነቶች ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ አድርጓል።
ዘንድሮም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግረኛ ቤተሰቦችን ከድህነት ለማውጣት ለሚንቀሳቀሰው፣"ወገኔ የኢትዮጵያዊያን ማኀበር" ድጋፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር መካኼዱን፣የማኀበሩ መስራችና ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ኒኒ ለገሰ ለዶቸ ቨለ ተናግረዋል።
ችግረኛ ቤተሰቦችን ለመደገፍ የተነሳው ወገኔ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ
"ግራንድ አፍሪካን ረን፣ዘንድሮ ወገኔን ስለመረጠ፣ የድጋፍ አጋር አድርጎን ሩጫው ላይ ወገኔ ደግሞ የወጣት ክበብ አባሎቻችንን አንቀሳቅሰን፣ደጋፊዎቻችንን አንቀሳቅሰን፣ሯጮች የአቅማቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ተመቻችቶልናል።"
የአፍሪቃ ኢምፓክት ሽልማት
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከጎዳና ላይ ሩጫው ጎን ለጎን፣ኖቫ ኮኔክሽንስ የሚያዘጋጀው፣ የጎርጎሮሣዊው 2024 አፍሪካ ኢምፓክት ሽልማት በዛሬው ዕለት ይካሄዳል።
ይህ ዓመታዊ የዕውቅና ሽልማት፣ በአሜሪካና በአፍሪቃ በሙያቸው ታላቅ ስራ የሰሩ ግለሰቦችን ለማክበር የሚዘጋጅ ሲሆን፣በዓመቱ በስፖርት፣በስነ ጥበብ እና በሥራ ፈጠራ ዘርፎች ለማኀበረሰባቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦና ለለውጥ ላደረጉ፣ የላቀ ተሳትፎ የሚሸለሙበት መድረክ ነው።
“ገበታ ለወገኔ” በስዊዘርላን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ተሳትፎ
ዘንድሮ በጋዜጠኝነት፣አንጋፋዋ ጋዜጠኛ መአዛ ብሩ፣ በስነጥበብ ዘርፍ ድምፃዊት አስቴር አወቀ፣በስፖርቱ ዘርፍ የማራቶንና እና የአምስት ሺህ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቶች አትሌት ትዕግስት አሰፋ እና ጉዳፍ ጸጋዬ፣በንግድ ዘርፍ ደግሞ ርብቃ ኃይሌ ተሸላሚ ይሆናሉ ተብሏል።
ባለፉት አምስት የታላቁ የአፍሪቃ ሩጫ ዝግጅቶች፣የኢትዮጵያ ብርቅዬ አትሌቶች፣ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ስለሺ ስህን፣ ሚልዮን ወልዴና ሌሎችም በክብር እንግድነት መገኘታቸውን፣ ኖቫ ኮኔክሽንስ ለዶይቸ ቨለ ከላከው ጋዜጣዊ መግለጫ ለመረዳት ተችሏል።
ታሪኩ ኃይሉ
እሸቴ በቀለ