1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ጤናሰሜን አሜሪካ

በአሜሪካ የሚገኘው ወገኔ የኢትዮጵያውያን ማኀበር ድጋፍ ለኢትዮጵያውያን ችግረኞች

ዓርብ፣ ሰኔ 7 2016

ወገኔ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግረኛ ቤተሰቦችን ከድህነት ለማውጣት እያገዘ መሆኑን ዐስታወቀ ። ኢትዮጵያ ውስጥ በድህነት የሚኖሩ ቤተሰቦችን ሕይወት በስልጠና እና በትምህርት ድጋፍ በመቀየር ራሳቸው እንዲችሉ በማገዝ ላይ እንደሚገኝ በአሜሪካ የሚገኘው ወገኔ የኢትዮጵያውያን ማኀበር ገለጸ።

https://p.dw.com/p/4h0VQ
USA Wegene Fundraising in Washington DC
ምስል Fafi photography

«በወገኔ» ለችግረኞት ባሉበት ቦታ የሚደረገው ድጋፍ

ወገኔ፤  ኢትዮጵያ ውስጥ ችግረኛ ቤተሰቦችን ከድህነት ለማውጣት እያገዘ መሆኑን ዐስታወቀ ።ኢትዮጵያ ውስጥ በድህነት የሚኖሩ ቤተሰቦችን ሕይወት በስልጠና እና በትምህርት ድጋፍ በመቀየር ራሳቸው እንዲችሉ በማገዝ ላይ እንደሚገኝ በአሜሪካ የሚገኘው ወገኔ የኢትዮጵያውያን ማኀበር ገለጸ። ማኀበሩ በ24 ዓመታት ጉዞው፣ ከ65  በላይ ቤተሰቦችን ከድህነት ቀንበር በማላቀቅ ራሳቸውን ማገዝ እንዲችሉ ማድረጉን ገልጧል ። አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ የወገኔ ድጋፍ  ተጠቃሚዎችም፣ በማኀበሩ እገዛ፣ ከዝቅተኛ ሕይወት ወጥተው ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በማስተዳደር ላይ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

ወገኔ፤ እንደጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር በ 2000 በዋሽንግተን ዲሲ  ተቋቁሞ፣ኢትዮጵያ ውስጥ ቤተሰቦችን ከድህነት ለማውጣት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን የሚያካሂድ  የግብረ ስናይ ማኀበር መሆኑን የማኀበሩ መስራችና ፕሬዚዳንት የሆኑት ወይዘሮ ኒኒ ለገሰ አመልክተዋል።

ለችግረኞት ባሉበት ቦታ የሚደረገው ድጋፍ

ማኀበሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የድህነት አዙሪት ለማስቀረት፣  ችግረኛ ቤተሰቦች በራሳቸው ቤትና አካባቢ የስልጠና እና ትምህርት  እንዲሁም የአነስተኛ ንግድ ስጦታዎች ድጋፍ ያደርጋል።

ስለማኀበሩ የድጋፍ ዓይነቶች ወይዘሮ ኒኒ፣የማኀበሩን አጠቃላይ ዓላማ በተመለከተ የሚከተለውን ብለዋል።

በኮሜዲያን እሸቱ መለሰ
በኮሜዲያን እሸቱ መለሰ አማካኝነት፣ "ማን እንደ ሃገር"የተሰኘ እስታንዳፕ ኮሜዲ በቀረበበት በዚህ መድረክ ላይ፣ ከአንድ ሺህ አንድ መቶ በላይ ተመልካቾች ታድመውበታልምስል Fafi photography

"ዋና መሰረታዊ ችግር መፈታት ያለበት ብለን ያመነው፣ የቤተሰብ መዋቅር እንዳይላላ በጣም ዝቅተኛ የሕይወት ደረጃ ያሉ ቤተሰቦችን እንዳለ እንደ ቤተሰብ አቅፈን፣ባሉበት ሁኔታ ስንጀምር በእርግጥ ከጎዳና ተዳዳሪ ቤተሰቦች ነው የጀመርነው። እነሱን አቅፈን እናቶችን በስራ ማጎልበት ራስን በራስ ለመቻል ብቃት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ልጆቹን ደግሞ ከልጅነት ጀምሮ ኮትኩቶ ጥሩ ትምህርት በማግኘት እና በተቻለ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡልን፣ ዩኒቨርስቲ ገብተው ደግሞ በአንድ ዲግሪ ተመርቀው፣ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ከፍ ብሎ፣ የችግርን ቀንብር ሰብረዉ ራሳቸውን ረድተው ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ የሚያደርግ ድርጅት ነው።"

እንደ ወይዘሮ ኒኒ ገለጻ፣ወገኔ የኢትዮጵያውያን ማኀበር እስካሁን ድረስ ወደ 880 የሚሆኑ ወጣቶችን እና 167 ቤተሰቦች አቅፎ በመርዳት ላይ የሚገኝ ነው።

ከድህነት ቀንበር የላቀቁ ቤተሰቦች

ማኀበሩ አዲስ አበባ ውስጥ በሚያካሄደው እንቅስቃሴ፣ በ 24 ዓመታት ጉዞው ያስመዘግበው ውጤት፣ እስከ 65 በላይ የሆኑ ቤተሰቦችን ከድህነት ቀንበር ያላቀቀ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ አስረድተዋል።

" ከ65 በላይ የሆኑ ቤተሰቦችን በ24 ዓመታት ጉዟችን፣ከድህነት ቀንበር አላቀን፣ በራሳቸው የመተዳደር ልጆቻቸው ከዩኒቨርስቲ ተመርቀውላቸው በጥሩ ሁኔታ እነሱም የራሳቸውን ቤተሰብ በማገዝና ፣ኅብረተሰቡ ጋር ተደባልቁ የህብረተሰቡ አገልጋይ እንዲሆኑ ያደረገ ድርጅት ነው።

የማኀበሩ ተጠቃሚዎች ምን ይላሉ?

ወይዘሮ ሙሉ ተሰማ አዲስ አበባ ውስጥ ነዋሪ ሲሆኑ፣በማኀበሩ ስለተደረገላቸው ድጋፍ በስልክ ጠይቀናቸው ነበር። " ወገኔ ኢትዮጵያ ማለት ለእኔ፣ በ1983 ከኤርትራ  ተፈናቅዬ ስኖር ነበር።ሦስት ልጆች አሉኝ። ሁለቱንም አንደኛው ከአራተኛ ሌላኛው ከሦስተኛ ክፍል ጀምሮ ሴቷ እንኳን አሁን ዘጠነኛ ናት። አስተምረውልኛል። አስተምረው ትልቁ ሁለቱም በኢንጂነሪንግ ነው የተመረቁት።"

የወገኔ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ
የወገኔ የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰብ እንቅስቃሴምስል Fafi photography

ሌላ ስሜ አይጠቅስ ያለ አስተያየት ስጪ በበኩሉ፣ በማኀበሩ በተደረገለት ድጋፍ የሕግ ትምህርቱን አጠናቅቆ በዐቃቤ ሕግ ባለሞያነት እየሰራ መሆኑን ገልጾልናል።  እርሱ እንደሚለው፣ ወገኔ የኢትዮጵያን ማኀበር የሰራውን ያህል አልተነገረለትም።

"ወገኔ ማለት ራሳቸውን ደብቀው የሚንቀሳቀሱ፣ እስከዛሬ ድረስ ለሕዝብ የሚያገለግሉ ያልታወቅላቸው ህዝብ ያልተረዳቸው፣ ብዙ ዜጎችን አስተምሮ ለተለያዩ ቁም ነገሮች አብቅቷል፣ እያበቃም ነው።"

 ማህበሩ ለሚካሄደው ለዚሁ የበጎ አድራጎት ስራ በቅርቡ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር አካሂዷል።  በኮሜዲያን እሸቱ መለስ አማካኝነት፣ "ማን እንደ ሃገር"የተሰኘ እስታንዳፕ ኮሜዲ በቀረበበት በዚህ መድረክ ላይ፣ ከ አንድ ሺህ አንድ መቶ በላይ ተመልካቾች ታድመውበታል።

ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሠ